ምርጫውን ለማደናቀፍ የተጠነሰሱ ሴራዎች እንደነበሩ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ምርጫው በአብዛኛው በሰላም የተጠናቀቀ ቢሆንም በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ሕዝቡ ድምጽ እንዳይሰጥ ለመረበሽ ሙከራ ተደርጎ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄላን አብዲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊነቱን መወጣቱን የተናገሩት ኃላፊው፣ በተወሰኑ የዞኑ ወረዳ አካባቢዎች ሕዝቡ ድምጽ እንዳይሰጥ ለመረበሽ ተሞክሮ እንደነበርና ችግሩን ለመቆጣጠር በአፋጣኝ ክትትልና እርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል።

ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ድምጽ እንዳይሰጥ ሲረብሹ የነበሩ የኦነግ ሸኔ ቡድን አባላት በተወሰኑ የጸጥታ ክፍሉ አባላት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ያሉት ጄላን፣ በአጸፋውም ፖሊስ እርምጃ በመውሰድ ሴራውን ማክሸፍ መቻሉን አንስተዋል። አያይዘውም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የምርጫውን ሂደት ለማስተጓጎል መሳሪያ ይዞ የመንቀሳቀስ ሁኔታ እንደተስተዋለ ጠቅሰው፣ ይህንንም ያደረጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከምርጫው ጋር ተያይዞ አንድ የፖሊስ አባል መገደሉን አንስተው፣ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው በመሄድ በስፍራው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ለማስገደድ መሞከራቸውንና በወቅቱ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ የፖሊስ አባሉ ህይወት ሊያልፍ መቻሉ ታውቋል ብለዋል።

ጥቃቱን ስለፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነትና ቁጥራቸው በተመለከተ ያሉት ነገር የሌለ ሲሆን፣ ዝርዝሩ በቀጣይ ምርመራ ተጣርቶ የሚገለጥ መሆኑን አመልክተዋል። በምርጫው ወቅት ተስተውለዋል ያሏቸውን ችግሮች ሲያብራሩ፣ በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም መንዝ ቀበሌ ላይ የምርጫ ቁሳቁስ ባለበት አካባቢ ዋና አስተዳዳሪው የጸጥታ ኃይሎችን እራት ልጋብዛችሁ በማለት ከስፍራው ዞር እንዲሉ ካደረገ በኋላ የምርጫ ቁሳቁስ የተቀመጠበትን ቤት በመክፈት ቁሳቁሱን ከውሃ ጉዳጓድ ውስጥ ጨምሮ ተሰውሯል።

በዚሁ ግለሰብ ላይ በተደረገ ክትትል ዋና አስተዳዳሪው ከተሰወረበት መያዙን እና የምርጫ ቁሳቁሶቹ ከጉድጓድ ወጥተው ምርጫው በሰላም መከናወኑን አብራርተዋል። ዋና አስተዳዳሪው ፍርድ ቤት መቅረቡን ገልጸው፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጣ የፖሊስ ባልደረባም በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 15 ዞኖች መካከል በዘጠኝ ዞኖች ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ባልተፈቀደበት ጊዜና አካባቢ ሲቀሰቅሱ የነበሩ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ብልጽግናን ጨምሮ፣ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል። በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የጸጥታ ስጋት እንዳይፈጠር በተለይም ከውስጥ እና ከውጪ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመመከት ከክልሎች እና ከኹለቱ ከተማ መስተዳድሮች ጋር በጋራ ሲሰራበት መቆየቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊው አመልክተዋል።

ከዚህ ባሻገር ከደህንነት እና ጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እንዚህን መሰል እኩይ ተግባራትን ለመከላከል በቅድመ ምርጫ፣ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ የአንድ ወር የኦፕሬሽን ሥራ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።
በብዙዎች ዘንድ ስጋት ባጠላበት የድህረ ምርጫ ወቅት በተቀናጀ ኃይል ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመመከት የፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ከተማ፣ እና የክልል ፖሊስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የተካሄደው ምርጫ የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው በሰላም መፈጸሙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here