የመጀመሪያ ዙር የኮቪድ ክትባት ተከታቢዎች ኹለተኛውን ዙር እየተከተቡ አይደለም ተባለ

0
1244

የመጀመሪያውን ዙር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክትባት የወሰዱ እና ሦስት ወር የሞላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ኹለተኛውን ዙር ክትባት እየወሰዱ እንዳልሆነ በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ዶ/ር መብርሃቱ ማሴቦ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ሲወስዱ ህመም የተሰማቸው ሰዎች በመደናገጣቸው ምክንያት ኹለተኛውን አልከተብም የሚል ስሜት ውስጥ በመግባታቸው ክትባቱን እያገኙ እንዳልሆነ ዶ/ር መብርሃቱ አስረድተዋል።

ቀድሞ ክትባቱን የተከተቡ ግለሰቦች የጎንዮሽ ጉዳት አለው አልወስድም የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው የገለጹት ባለሙያው፣ በመጀመሪያው ዙር መጠነኛ የህመም ስሜት ቢሰማቸውም በኹለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የተለየ ስሜት እንደማይኖራቸው ነው ያብራሩት።

አሁንም ቢሆን እንደ አገር የሚሰጡ ክትባቶች ኹለት አይነት መሆናቸውን ያነሱት ባለሙያው፣ አንደኛው ሲኖ ቫክ የተሰኘው ክትባት ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ከተከተቡ በአራት ሳምንት ልዩነት ውስጥ የሚሰጥ ነው ብለዋል። ኹለተኛው አይነት ክትባት በሶስት ወራት ልዩነት የሚሰጥ የአስትራ ዜኒካ ክትባት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኹለተኛውን ዙር ክትባት ሁሉም ሰው በተመሳሳይ ጊዜ ሊወስድ እንደማይችል አንስተው፣ ሶስት ወር የሞላቸው እና ወረፋቸው የደረሰ ብቻ ሊወስዱ እንደሚችሉ አስረድተዋል። የጤና ሚኒስቴር ይህንን ይበል እንጂ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመጀመሪያውን ዙር ክትባት የተከተቡ ግለሰቦች ኹለተኛውን ዙር ክትባት ለማግኘት ሲሄዱ ጤና ተቋማት እዚህ የለም በማለት ወደ ሌላ ጣቢያ እንደሚልኳቸውና የተባሉት ቦታ ሲሄዱም በመገናኛ ብዙኃን እስኪነገር ጠብቁ በማለት እንደመለሷቸው ክትባቱን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በአንጻሩ የመጀመሪያው ዙር ክትባት በስኬት ቢጠናቀቅም፣ ኹለተኛውን ዙር ክትባት ሕብረተሰቡ እየተከተበ እንዳልሆነ የተናገሩት አስተባባሪው፣ ኹለተኛው ዙር ክትባት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የግድ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል። ይህ ካልሆነ ግን የመጀመሪያው ዙር ክትባት ብቻ ቫይረሱን ለመከላከል አስተማማኝ አይደለም ነው ያሉት። የመጀመሪያው ዙር ክትባት የመከላከል አቅሙ በቂ ባለመሆኑ ይህንን የኹለተኛውን ዙር ክትባት መከተብ አስገዳጅ መሆኑን በሙያዊ ማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።

ይህንንም የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ሌሎች አገራት ተግባራዊ እያደረጉት መሆኑን ገልጸው፣ ክትባቱ የመከላከል አቅሙ የሚጨምረው ኹለቱም ዙር ክትባት ሲወሰድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል። ኹለተኛው ዙር የኮቪድ 19 ክትባት የሚሰጠው የመጀመሪያውን ዙር ወስደው ሶስት ወር ለሞላቸው ለጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሆኑም ተጠቅሷል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም ስጋት መሆኑን ሕብረተሰቡ በሚገባ በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ የመከላከያ መንገዶችን ሳይዘናጋ እንዲተገብር በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ዶ/ር መብርሃቱ ማሴቦ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር 2.2 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮቪድ-19 ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ አስቻለው አባይነህ፣ አምባሳደሮች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በተገኙበት መረከቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here