አዋሽ እና ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ለኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ብድር ሊያቀርቡ ነው

0
1131

ኮርፖሬሽኑ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ወደ ኹለቱ ባንኮች ይዞራል

አዋሽ ባንክ እና ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለሚያከናውናቸው የቢዝነስ ሥራዎች የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የፕሮጀክት ብድር ሊያቀርቡ ነው። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባሳለፍነው ጥቅምት 2013 ለ18 የኢትዮጵያ ባንኮች አብሮ ለመስራት ጥያቄ ማቅረቡን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። በዚሁ መሰረት በኮርፖሬሽኑ ጥሪ ከቀረበላቸው ባንኮች መካከል በወቅቱ 13 ባንኮች ምላሽ መስጠታቸው ተገልጿል። ከ13ቱ ባንኮች መካከል ስድስቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በአካልና በደብዳቤ ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ በመጨረሻ አዋሽ ባንክ እና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ መስፈርቱን አሟልተው ስለተገኙ ለኮርፖሬሽኑ ብድር ለማቅረብ ተስማምተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ዝርዝር መስፈርቶችን አዘጋጅቶ ባንኮቹን ያወዳደረ ሲሆን፣ በዋናነት ለኮርፖሬሽኑ የሚቀርቡ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ፕሮጀክቶች ብድር፣ በልዩ ሒሳብ አካውንት ኮርፖሬሽኑ ከሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ላይ የሚገኝ ልዩ ጥቅምና ለኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የሚቀርቡ የተለያዩ የብድር አይነቶች ናቸው። ለኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ባንኮቹ ከሚያቀርቧቸው ብድሮች መካከል የቤት መግዣ፣ የመኪና መግዣ፣ የህክምና፣የጋብቻ እና የእቃ መግዣ ብድርና ሌሎች ብድሮች እንደሆኑ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አዲሱ ማሞ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ባንኮቹ እና ኮርፖሬሽኑ በተስማሙት አጋርነት መሰረት ለኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የሚቀርበው የብድር አገልግሎት ለሠራተኞች ምቹ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የሠራተኞች መነቃቃትና ምርታማነትን ለማሳድግ ብሎም የሠራተኞችን ፍልሰት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
ኮርፖሬሽኑ ከኹለቱ ባንኮች የብድር አገልግሎት ለማግኘትና በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምንት ሰኔ 17/2013 ተፈራርሟል። በስምምነቱ መሰረት ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውናቸው የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ፕሮጀክት ብድር፣ የኮርፖሬሽኑን የገንዘብ አቅም ለማሳደግና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማስፈጸም ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።

ኮርፖሬሽኑ ከባንኮቹ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ሥርዓት የፈጠረው ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባትና ከማስተዳደተር በተጨማሪ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እና ተያያዥ አግልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር አጋር ሊሆኑ የሚችሉ የአገር ውስጥና የውጭ ገንዘብ ተቋማት ጋር መሥራት በማስፈለጉ ነው ተብሏል።

ኮርፖሬሽኑ ከአዋሽ ባንክ እና ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቱን ተከትሎ፣ ኮርፖሬሽኑ የሚያንቀሳቅሰውን ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ኹለቱ ባንኮች እንደሚያዛውር የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ኮርፖሬሽኑ በአብዛኛው በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ በማንቀሳቀስ የተሻለ አቅም ስላለው፣ አብረው ለመሥራት ለተስማሙት ባንኮች የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። ባንኮቹ በኮርፖሬሽኑ በኩል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን የገንዘብ እንቅስቃሴ የመሳብ እድል እንደሚፈጥርላቸውም ተመላክቷል።

ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚሰጣቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማስተዳደርና እና የፈሳሽ ቆሻሻ ውኃ ማከም አገልግሎት በተጨማሪ፣ ግንባታቸው ተጠናቆ በአልሚ ባለሀብቶች ከተያዙ የማምረቻ ህንፃዎች ኪራይ በዓመት 24 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኛል። ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ድረስ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርጓል። ኮርፖሬሽኑ እስካሁን 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያስገነባ ሲሆን፣ 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ጀምረዋል። ሥራ በጀመሩት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ100 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በማስያዝ ወደ ምርት እንዲገቡ አድርጌያለሁ ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here