የመከላከያ ሠራዊቱን አቅም የበለጠ ለማጠናከር በመከላከያ ቴክኖሎጂ እና ልምድ ከፍተኛ አቅም ካላቸው ፈረንሳይና ጣልያን መንግሥታት ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው ተባለ።
ከሥልጠና እና ልምድ ልውውጥ ጋር በተያያዘ የካበተ ልምድ ካላቸው ፈረንሳይ እና ጣልያን አገራት ጋር በትብብር መሥራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤው ከፈረንሳይ እና ከጣልያን መንግሥታት ጋር በተናጠል የተደረገው የመከለላከያ ትብብር ስምምነት አስመልክቶ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ ባጸደቀበት ወቅት፣ ስምምነቶቹ ከአገራቱ ጋር በሰው ኃይል ስልጠና ፣ በወታደራዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፣ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት እገዛ የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል፡፡ የአገራቱንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ባገናዘበ መልኩ በወታደራዊ ትብብሮች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥሩም ናቸው መባሉ ተሰምቷል።
በአገራቱ ስምምነት ላይ የላኪው አገር አውሮፕላኖች በተቀባዩ አገር የአየር ክልል ውስጥ መብረር እና ማረፍ እንዲችሉ፣ እንዲሁም መርከቦች መልህቃቸውን እንዲጥሉ ላኪው አገር በጠየቀ ጊዜ ተቀባዩ አገር በቅን መንፈስ እንዲያመቻች የተመላከተ ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ከፈረንሳይ ጋር የተደረገው የመከላከያ ስምምነት 28 አንቀጾችን የያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከጣሊያን ጋር የተደረገው ስምምነት የመከላከያ ቁሳቁሶች ምርትና ግዥ፣ ምርምር፣ ፖሊሲ እና ቴክኒክ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ልምድ ልውውጥ ማድረግን ያጠቃልላል ያሉት አምባሳደር መስፍን፣ ከፈረንሳይ ጋር የተደረገው ስምምነት ደግሞ ላኪው አገር ሌሎች ቁሳቁሶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶች ወደተቀባዩ አገር ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ እና ይዞ እንዲወጣ ይፈቅዳል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ስምምነቶቹ ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈረሙ ሲሆን፣ ከየአገራቱ ጋር የተደረጉ ውይይቶች እና ጠቃሚ ሃሳቦችን ለማካተት በተደረገ ጥረት ወቅቱን ጠብቆ አሁን ላይ እንዲጸድቅ ተደርጓል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ናቸው፡፡ አምባሳደሯ አያይዘውም ስምምነቶቹ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይጋፋ መልኩ በእኩልነት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013


