ዝክረ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ

0
1246

ሀጫሉ ሁንዴሳ ከእናቱ ጉደቱ ሆራ እና ከአባቱ ሁንዴሳ ቦንሳ በ1976 ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምተገኘው አምቦ ከተማ ተወለደ።ትውልዱ እና እድገቱ አምቦ ከተማ የሆነው ሀጫሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዘቃ በጣም ይወድ ነበር።ሙሉ ትኩረቱ ሙዚቃ ላይ ብቻ የነበረው ሀጫሉ በአስራዎቹ እድሜው ላይ እያለ እንኳን የበርካቶችን ስሜት የሚኮረኩሩ ሙዚቃዎችን ይጫወት ነበር። ሀጫሉ በ1995 የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውና ተወዳጅ የሆኑ የኦሮሞ የትግል ሙዚቃዎችን በማቀንቀኑ የተነሳ ለአምስት አመት ያህል ለእስር ተዳርጎ ነበር።

በመታሰሩ ምክንያት የዘፋኝነት ህልሙን ያላቋረጠው ሀጫሉ፣ ይልቁንም ብሶበት በአጭር ጊዜ ውስጥ በኦሮምኛ ተናጋሪው እና በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነለትን ‘ሳኚ ሞቲ’ የተሰኘውን አልበሙን አቀረበ። የዚህ አልበም የሙዚቃ ስብስቦች አብዛኛዎቹ ግጥሞችና ዜማዎች ሀጫሉ በእስር ላይ እያለ የሠራቸው እንደነበሩ ይነገራል። ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አሜሪካ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለማቅረብ በሄደበት ጊዜ ኹለተኛውንና “ዋኤ ኬኛ” ማለትም “የእኛ ጉዳይ” የሚል ትርጉም ያለውን የሙዚቃ ሥራውን አሳተመ።
በወቅቱ የሙዚቃ ሥራው አማዞን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመሸጥ ከፍ ያለ ትኩረትን አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ የሀጫሉ ተወዳጅነትም የበለጠ እየተጠናከረ መጣ።

ከአመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት ሀጫሉ ያወጣው ‘ማላን ጂራ’ የተሰኘው ነጠላ ሙዚቃው ከፍተኛ ተወዳጅነትን ከማትረፍ አልፎ በወቅቱ ለነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መነቃቂያ በመሆኖ አገልግሎ ነበር። ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበረው የ36 ዓመቱ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ ሰኔ 22/2012 አዲስ አበባ ውስጥ በተፈጸመበት ጥቃት ህይወቱ አልፏል። የሙዚቀኛውን ሞት ተከትሎ በተነሳ ግርግር የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ በርካታ ንብረትም ወድሟል።በሂደቱም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና የማሕበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ለእስር ተዳርገዋል።

የሀጫሉ መሞት ሊያሳካቸው አስቧቸው የነበሩ ህልሞቹን አብሮ ይዞ አልሞተም የምትለው የአርቲስቱ ባለቤት ፋንቱ ደምሴ፣ ዓላማውን ለማሳካት ባሳለፍነው ሰኞ በህይወት እያለ የሰራውን የሙዚቃ ሥራ አስመርቃለች። በዕለቱ የአርቲስቱ ሦስተኛ የሙዚቃ አልበም ምርቃትና የአንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም በስከይላይት ሆቴል ተካሂዷል። በተለያየ ዝግጅት በታጀበው መርሃ-ግብር ላይ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና በርካታ የጥበብ አፍቃሪያን ታድመዋል። በመርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፋንቱ “ሀጫሉ በህይወት ቢለይም ትውስታውና ሥራዎቹ ህያው ናቸው” ብለዋል።

ከአርቲስቱ ህልፈት በኋላ ከቤተሰቡ ጎን ሆነው በተለያየ መልኩ ድጋፍ ላደረጉ ኹሉ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም የአርቲስቱን ስም ባልተገባ መንገድ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ወላጅ አባት ሁንዴሳ ቦንሳ በበኩላቸው፣ “ሀጫሉ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ልጅ ነው” ብለዋል። “የልጄ ገዳዮች ሕግ ፊት ቀርበው ፍትህ እንዲያገኙ ሁሉም እንደየኃይማኖቱ ጸሎት ያድርግልኝ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። በዕለቱ የተመረቀው የሙዚቃ ሥራ አርቲስቱ በህይወት እያለ ያዘጋጀው ሲሆን፣ ‘ማል መሊሳ’ በሚል ርዕስ ታትሞ ለአድማጭ እና ለአድናቂዎቹ ቀርቧል።

ይህ አልበም 14 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን፣300 ሺሕ ቅጂ ታትሞ በመጀመሪያ ዙር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአውታር እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ላይ ቀርቧል ሲል የሀጫሉ ሁንዴሳ የቅርብ ወዳጁ የሆነው እንዲሁም የቪዲዮ ፕሮዳክሽን ሥራዎች ላይ የተሰማራው አመንሲሳ ኢፋ ገልጿል። የሂራ ፒክቸርስ ሠራተኛ የሆነው አመንሲሳ፣ ሚሊን ጂራ የሚለውን ቪዲዮ ከሀጫሉ ጋር በጋራ የሠሩ ሲሆን የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝተዋል። ቤተሰቦቹ አስኪጽናኑ ድረስ እንደ ሙዚቃ ባለሙያ የሠራቸው ነጠላ ስራዎች ከስቱዲዮ ተሰርቀው እንዳይሰራጩ የማሰባሰብ እና የማደራጀት ሥራ ሲሠራ እንደቆዩ አመንሲሳ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በተለያየ ጊዜ ስቱዲዮ ገብቶ የሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከሠራቸው ውስጥ ኹለት በቅርብ ተሰርቀው የወጡ ነጠላ ዜማዎችን ጨምሮ 14 የዘፈን ሥራዎችን አሰባስቦ ማስተሪነግ በማስተካከል ለማውጣት መቻሉ ተገልጿል። አማዞንን ጨምሮ በርካታ በውጭ ሀገር መተግበር የሚችሉ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ላይ ስራዎቹን ለማሰራጨት ተችሏል። ይህ አዲስ አልበም በተለያዩ የአለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች የተለቀቀ ሲሆን አይ ቱን(I-Tune) በተሰኘው መተግበሪያ ላይ በአንድ ቀን ቶፕ 40 የሙዚቃ አልበም ውስጥ መግባት ችሏል።

‹‹ማል መሊሳ›› ማለት‹‹ መፍትሄው ምንድነው›› ማለት ሲሆን፣ ርዕሱ የተመረጠውም በ2ኛ አልበሙ ላይ ‹‹ዋኤ ኬኛ››(የእኛ ጉዳይ) የሚል መጠሪያ የነበረውን ሊያስቀጥል የሚችል ሀሳብመሆኑን መነሻ በማድረግ እንደሆነ አመንሲሳ ይናገራል። የሀጫሉ ባለቤት አልበሙ ተሳክቶ በአንድ ዓመት የተጣበበ ጊዜ ውስጥ እንዲደርስ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የገለጸው አመንሲሳ፣ ወደፊት ሀጫሉ እንዳይረሳ ለማድረግ በስሙ የሚቋቋመውን ፋውንዴሽን ለማጠናከር እና ሥራዎቹን በቪዲዮ ለመሥራት ታቅዷል። ‹‹ሀጫሉ ማለት የአንድ ብሔር ተወላጅ ወይም የአንድ ቤተሰብ ልጅ አይደለም።የመላው ኢትዮጵያውያን ነው›› የሚሉት የሀጫሉ ሁንዴሳ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ደረጀ በለጠ ናቸው።

በግል ንግድ የሚተዳደሩት ደረጀ ከዚህ በፊት ከሱማሌ ክልል የኦሮሞ ተወላጆች ሲፈናቀሉ ከጓደኞቹ እና ሀጫሉ ጋር በመሆን 11 በሬ ገዝተው ለተፈናቃዮች እርዳታ ያደረጉ ናቸው። እንደ ደረጀ ገለጻ ከሆነ ሀጫሉን ማጣት አንድ ትልቅ ሀዘን መሆኑ ይታወቃል።የሱን ሞት ተከትሎ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞተው ነበር።ይህ ደግሞ የመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ሀዘን እንዲሆን አድርጓል። ሀዘኑ በዚህ ብቻ አላበቃም የሚሉት ደረጀ፣ አሟሟቱን በተመለከተ ደግሞ ምንም አይነት መረጃ አለመውጣቱ ሀዘናችን እንዲበረታ አድረጓል ብለዋል።
‹‹የሀጫሉ ዘፈኖች በመላው ዓለም ተደማጭ ናቸው።ይህ ደግሞ የዓለም ሕዝቦች ምንም እንኳን ቋንቋውን ባይረዱት ሙዚቃውን ሲያጣጥሙት እንመለከታለን።ሀጫሉን ማጣታችን በጣም ልብ የሚሰብር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ አሟሟቱ ከኹሉም በላይ ሀዘናችንን አብዝቶታል።ይህንን ሁሉ ሀዘን እንዳይበረታብን ገዳዮቹ በግልጽ የተፈረጁበትን ሁኔታ አላየንም›› ሲል ደረጀ ገልጿል።

እውነቱ እስከአሁን ሳይወጣ እየተሸፋፈነ መቆየቱ ሀዘናቸውን እያባባሰው እንደሚገኝ የሚናገሩት ደረጀ፣ ተያዙ የተባሉት ወንጀለኞች ትክክለኛነት እና የተወሰዱ እርምጃዎችን ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባል ይላል።የሀጫሉ አሟሟት እና ገዳዮቹ አለመያዛቸው በቀጣይ ለአገር የሚጠቅሙ ወጣቶች ማንነታቸው በማይታወቅ ሰዎች ቢገደሉ ትኩረት ሊያጣ ስለሚችል እንደ አገር ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያስገባናል ብለዋል። ‹‹ሀጫሉ ማለት ሰውን የሚያከብር፣ደግ እና ፍቅር ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ ቢሆንም ለሚንቁት ሰዎች ደግሞ በጣም አደገኛ ሰው ነው›› ሲሉ ደረጀ ሀጫሉን ይገልጹታል።

‹‹አሁን ሀጫሉ ሞቷል። ልጆቹ የሚገባቸውን ኑሮ መኖር አለባቸው። ቤተሰቦቹም ቢሆኑ መሳቀቅ እና የማይገባቸውን ህይወት መኖር የለባቸውም።በርግጥ በአሁኑ ሰዓት በአንድ ግለሰብ አማካይነት የልጆቹ ወጪ ሙሉ በሙሉ ተሸፍኖ እየተማሩ ይገኛሉ። ጓደኞቹም ሆነ አድናቂዎቹ ለሀጫሉ ህይወታቸውን ይሰጣሉ።ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለእውነት የታገለ ነው።እንደዚህ አይነት ትልቅ ሰው ከማጣታችን በፊት የሚሠራውን አገራዊ ሥራ በማየት መንግሥት ከለላ ሊሰጠው ይገባ ነበር›› በማለት ደረጀ ተናግሯል። ደረጀ አክሎም ለሀጫሉ ቤተሰብ ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ ሲሰበሰብ ነበር።በርካታ የሚባሉ አድናቂዎች እና ጓደኞቹ አዋጥተዋል።በሀጫሉ እና ቤተሰቡ ስም ትልቅ ኢንዱስትሪ ይከፈታል ተብሎ ነበር።ነገር ግን ገንዘቡም የት እንደደረሰ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።

መንግሥትም እንደ ኮሚቴ የተቋቋመው አካል የሰበሰበውን ገንዘብ ምን ላይ እንዳዋለው መረዳትና ግልጽ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ይህ ተቋቋመ የተባለው ኮሚቴ እንደገለጸው በሀጫሉ ስም የተሰበሰበው ገንዘብ 141 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ለሀውልት ማሰሪያ እና ለሌሎች አገልግሎቶች በመቀነስ የተቀረውን ገንዘብ በቤተሰቡ አካውንት ማስገባቱን የኮሚቴው አስተባባሪ ዳባ ደበሌ ገልጸዋል። በአልበሙ ምርቃት ቀን የጥበብ ሥራዎችን የሚያግዝና በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ስም የተሰየመ ፋውንዴሽን መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሀውልት ተሰርቶ መጠናቀቁም ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ጥላሁን ወርቁ እንደገለጸው ሀውልቱ ተሰርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች እና ጓደኞች በተገኙበት ይመረቃል ብለዋል። የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሀውልት የተሰራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት መሆኑ ታውቋል። የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አልበም ከሚገኝባቸው መተግበሪያዎች አንዱ አውታር መሆኑ ይታወቃል።አውታር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሙዚቃ መተግበሪያ ሲሆን በሙዚቀኞች የተመሠረተና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ አመት የሆነው ነው።

ላለፉት 50 ዓመታት ያህል የነበረው የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት የባለሙያውን መብት የማያከብር፣ የልፋት ውጤት የማይከፈልበት፣ ከአርቲስቶቹ የበለጠ ነጋዴዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት በመሆኑ አውታር ቀደምት ሥራዎች የሠሩ አርቲስቶችን ጨምሮ የባለቤትነት ጥቅም እንዲያገኙ እና ተጠቃሚውም በተመጣጣኝ ዋጋ እና ፍጥነት መርጦ እንዲገዛ የሚያመቻች ነው ሲል አርቲስት ጆኒ ራጋ ገልጿል። ‹‹ማንኛውም ሥራ ባለቤት እንዳለው ይታወቃል።የሞቱ አርቲስቶችም ቢሆኑ እነሱ ያልፋሉ እንጂ ሥራቸው ህያው ሆኖ ይቀጥላል።ሥራዎቹም ወራሽ ለሆነ አካል ተላልፈው ስለሚሠሩ ከባለቤቱ ጋር በመስማማት ሙዚቃው ወደ አውታር እንዲገባ ተደርጓል›› ሲል ጆኒ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ኦሮሚኛ ቋንቋ በርካታ ተናጋሪ ሕዝብ እንዳለው ይታወቃል።አውታር የተባለው መተግበሪያ ደግሞ በተለያዩ ቋንቋ የተሰሩ ሙዚቃዎችን ለሕዝብ ማድረስ ቀዳሚ ተግባሩ ነው። ሁሉም ሙዚቃዎች በትክክል ለሙዚቃ አድማጩ የሚደርሱበት መንገድ አላገኙም ነበር። ስለዚህ ይህ መተግበሪያ ለኹሉም ሙዚቀኞችና ሙዚቃዎች ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበርከትና ከአድናቂዎች ጋር እንዲገናኙ መንገድ የሚከፍት ነው ሲል ጆኒ ራጋ ይገልጻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here