በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማስቆም ፣ ሞትና መፈናቀልን ለማስቀረትና ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ትዕዛዝ ኮማንድ ፖስት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩና ከፍተኛ ውጤትም እንደተመዘገበባቸው የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ ገለፁ።
ከነዚህ ውጤቶች መካከልም የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የሠላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እንደሚገኝበትም ተናግረዋል።
የተሃድሶ ስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ እንደተናገሩት ፣ ከአሁን በኋላ በዞኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት አንድም ሰው ሊሞት አይገባውም ፤ ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ጊዜ ያበቃል ፤ ታጣቂዎች የሠላምና የልማት ኃይል መሆን ይጠበቅባችኋልም ብለዋል።
ለዚህ ስራ መሳካት የአማራ ፣ የኦሮሚያ እና የቤኒንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደጋፊ አመራሮችና የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና የፀጥታ አካላት ለዞኑ ሠላም የፀጥታ ኃይሉ መስዋዕትነት ከፍለዋል ፤ ክብር ይገባቸዋል ፤ ሁሌም እንዘክራቸዋለን በማለት ተናግረዋል።
የቤኒንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ር/መስተዳደር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው ፣ የክልሉ መንግስት ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረው ፣ በቀጣይነትም የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው ፣ መተከል ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተምሳሌት ነች ፡፡ ላለፈው ስህተት ይቅር በመባባል ለሰላም ልንቆም እና እንደዚህ አይነት ድርጊት ዳግም እንዳይፈጠር በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።
ኮማንድ ፖስቱ የሰላም አማራጩን ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ማዕከል የገቡ ከ 1ሺ600 በላይ ታጣቂዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁም ተገልጿል።
ሰልጣኞቹ ባወጡት ባለ 13 ነጥብ የአቋም መግለጫ ፣ የበደልንው ህዝባችንን ይቅርታ እንጠይቃለን የልማት ኃይል ሆነንም እንክሳለን ማለታቸውን ከኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።






