“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ሴት አትሌቶችን ያፈራች አገር እንደሆነች ይታወቃል። ነገር ግን በባህል ማሕበረሰባችን ለሴቶች ባለው ደካማ አስተሳሰብ ምክንያት ሌሎች ጠንካራ ሴት አትሌቶችን በብዛት ማፍራት አልተቻለም። በፊት በነበረው የሕብረተሰቡ ወግና ልማድ ምክንያት ሴቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ የላቀ ተሳትፎ ማድረግ አይችሉም ነበር።
ባሁኑ ወቅት የሴቶች በስፖርቱ እንቅስቃሴ ላይ መሳተፋቸው መጠነኛ የሚባል መሻሻሎች ቢኖሩትም፣ እንደ ሌሎች ያደጉ አገራት ግን እንቅስቃሴያቸው እምብዛም ነው። ሴቶች አካላዊ እንቅስቃሴ እና ስፖርትን ተግባራዊ ማድረጋቸው ለተስተካከለ አቋም እና መልካም ጤንነት ይጠቅማል።
በአገራችን በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ተቋማት ሴቶችን ለኦሎምፒክ ብቁ ለማድረግ ያን ያህል አኩሪ ሥራ እየተሠራ ነው ለማለት ይከብዳል። ኢትዮጵያን ወክለው በኦሎምፒክ ደረጃ መሳተፍ የሚችሉ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሴት አትሌቶች በተለያጠዩ የአገራችን ገጠራማ ክፍሎች ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ግን እነዚህን ሴት አትሌቶች የሚያበረታታ አካል አለመኖሩ ያሳዝናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በኦሎምፒክ የምታደርግው የላቀ የሴት አትሌቶች ተሳትፎ ቢበረታታም፣ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም። ዕድል ያገኙ ሴት አትሌቶችም ቢሆኑ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ለስኬት መድረሳቸው ግልጽ ነው። የሕብረተሰቡን መልካም ያልሆነ አስተሳስብ አሸንፈው በመውጣት አገርና ወገናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስጠራታቸው አይዘነጋም።
አገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈችው እ.እ.አ በ1956 ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል። በወቅቱ ሴት አትሌቶቻችን አገራችንን ወክለው ውድድሮችን መካፈል ብሎም ማሸነፋቸው ባይታሰብም፣ ይህን ታሪክ አርገው ያስቀሩ እንቁ ሴት አትሌቶች ግን እ.እ.አ 1992 ጀምሮ ባሉት ዓመታት በውድድር መድረኮች ላይ ተሳታፊ መሆንና ማሸነፍ ችለዋል።
አገራችን ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መድረክ ካስጠሩ ሴት አትሌቶች መካከል ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ፋጡማ ሮባ፣ መሰረት ደፋር፣ አልማዝ አያና እንዲሁም የዲባባ ቤተሰቦች ተጠቃሽ ናቸው። እ.እ.አ. በ1992 በ በባርሴሎና አትሌት ደራርቱ ቱሉ ያስጀመረችው የሴቶች ስፖርታዊ ውድድር አሁን ላይ ላለው የሴቶች የድል ዋጋ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
ይሁን እንጂ ትልቅ አቅም ያላቸውን ሴት አትሌቶች በዋና፣ መሰናክል፣ዱላ ቅብብል እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ሲካፈሉ ማየት ግን የተለመደ ነገር አይደለም። ስለሆነም ተትኪው ትውልድ የተጀመረውን ሴቶችን በስፖርታዊ ውድድሮች የማብቃት ሂደት የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል። ለዚህም ለሴት አትሌቶቻችን በተገቢው መንገድ እውቅና መስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ከኹለት ሳምንት በኋላ በሚደረገው የ 2020 ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሴት አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ይታወቃል። በውድድሩም ሴቶች ለአገራቸው ከፍተኛ ድል የሚያመጡበት መሆኑ አያጠያይቅም።
ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013


