በኦሮሚያ ክልል ይመሰረታል የተባለው የሽግግር መንግሥት ተቀባይነት የለውም ተባለ

0
856

ኦነግ እና ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት እናቋቁማለን ማለታቸው ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ገለጸ። ወደ ሥልጣን መምጣት እና መንግሥት መመስረት የሚቻለው በምርጫ ብቻ ነው ያሉት የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ ናቸው። ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው የክልሉ ሕዝብ ብቻ ነው። እንደእሳቸው አባባል ኦነግም ሆነ ኦፌኮ መንግሥት ለመመስረት የሕዝብን ድምጽ የማግኘት ግዴታ አለባቸው።
ኹለቱ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደምም ቢሆን የፈለጉትን መንግሥት ሲያቋቁሙ፣ ሲሽሩ፣ ሲጥሉ እና ሲያነሱ የመጡበት ልምድ መሆኑን የገለጹት የቢሮው ኃላፊ አዲስ ነገር ሊፈጥሩ ስለማይችሉ ለክልሉ ስጋት አይሆኑም ብለዋል። የሕዝብ አብላጫ ድምጽ ባላገኙበት ሁኔታ “ለክልሉ ሕዝብ እንቆማለን፤ የክልሉ ሕዝብ ተጨቁኗል” በማለት አመጽ ለማስነሳት እና የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ማሰብ ቅዥት ነው። ሕዝቡ ሰላም እንዳያገኝ እና እንዳይረጋጋ ኦነግ እና ኦፌኮ እየሠሩ መሆናቸውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። የክልሉ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው ያሉት የቢሮው ኃላፊ፣ ይህንንም ሰላም ማምጣት እና ማረጋገጥ የሚቻለው ሕዝቡ በመረጠው መንግሥት ሲተዳደር ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ይህንንም እውን ለማድረግ 6ኛዉ አገር አቀፍ ምርጫ በክልሉ በሰላማዊ መንገድ ተከናውኖ መጠናቀቁን ገልጸው፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሸናፊው ፓርቲ ተለይቶ መንግሥት እስኪቋቋም እየተጠበቀ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህ ውጪ ሕገ-መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው ከምርጫ ውጪ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እና በአቋራጭ ሥልጣን ለመቆናጠጥ ማሰብ በራሱ ወንጀል ነው። ይህን መሰል ተግባር መፈጸም፣ ይበጀኛል ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ በነቂስ የወጣውን ሕዝብ መናቅ ማለት እንደሆነም አስረድተዋል።
ክልሉ አሁን ባለበት ሁኔታ ምንም አይነት የሽግግር መንግሥት አያስፈልገውም ያሉት ጌታቸው፣ ይህን በመጣስ የሚመጣ ማንኛውም የሽግግር ሐሳብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ኦነግ እና ኦፌኮ በበኩላቸው 6ኛዉ አገራዊ ምርጫ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን እና በኦሮሚያ ክልል ምርጫዉ የዉድድር ሳይሆን የብቻ ግልቢያ ነበር ሲሉ ተቃውመዋል።

ፓርቲዎቹ ባወጡጥ መግለጫ፣ ምርጫው የኦሮሞ ፓርቲዎች፣ ኦነግና ኦፌኮ፣ ተገፍተዉ የወጡበት ከዚያም ባለፈ አመራሮቻቸዉ፣ አበላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸዉ ጭምር በእስር ላይ ሆነዉ የተካሄደ ነበር ብለዋል። በምርጫው ሂደት የእነዚህ ኹለት ፓርቲዎች ቢሮዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ መዘጋታቸውን እና ፓርቲዎቹ የምርጫው ሂደት ፍትሐዊ እንዲሆን የተቻላቸዉን ሁሉ ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰዋል። ቅቡልነት የሌለው ምርጫ መፍትሄ እንደማይሆን በመጠቆም፣ መፍትሄው ከኹሉም ተቋማትና ፓርቲዎች የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም የሚል ሀሳብ አስቀምጠዋል።

አክለውም ሕዝቡ የሚወክሉትን በሕግ እሰኪመርጥና የራሱን ቅቡል መንግሥት አስኪያቋቁም ድረስ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምለት ይፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም፣ ኦነግና ኦፌኮ አሁን ያለዉን የአገሪቱን ፖለቲካ በጥልቀት ካጤኑና ከመረመሩ በኋላ ከምሁራንና ከሰፊዉ ሕዝብ ጋር በመወያየት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት(ኦብክሽመ) አቋቁመዋል ሲሉ ባወጡት የሽግግር መንግሥት አዋጅ አስፍረዋል። በመግለጫቸው የሕዝብ መንግሥት በሕዝብ ይሁንታ፣ በሕግና በምርጫ እሰኪመሰረት ድረስ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሟል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here