ኤም ብር ከኹሉም ባንኮች ጋር የሚያስተሳስረውን አዲስ ቴክኖሎጂ ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር ሊጀምር ነው። ይህ አገልግሎት በአገሪቱ 14ቱም ባንኮች የሂሳብ ደብተር ያለው ደንበኛ በኤም ብር በኩል መጠቀም የሚያስችለው መሆኑን የኤም ብር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደስታ ባይሳ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው ኤም ብር ላይ ያለ ብር ወደ ባንኮቹ መላክ የሚቻልበት እና ካሉት ባንኮች ወደ ኤም ብር የሚዘዋወርበት መንገድ ነው። ቴክኖሎጂው በዋናነት የገጠሩን ማሕበረሰብ ያገናዘበ ሲሆን፣ ተደራሽነትን ለማስፋት ከማሰብ አንጻር የሚተገበር ነው ተብሏል።
ከተመሠረተ ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም (ኦብቁተ) 400 የሚጠጉ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ የኤም ብር ቴክኖሎጂ የሚተገበርበት የመጀመሪያው ተቋም ነው። ኤም ብር በቀጣይ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ለመሥራት ማቀዱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ባንኮች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አሏቸው። በመሆኑም የኤም ብር ቴክኖሎጂ ይህን በመጠቀም ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ መንገድ የሚከፍት ነው። በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ደንበኞች ምንም ሳይጉላሉ አቅራቢያቸው በሚገኝ ተቋም የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።
ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር የሚደረገው ይህ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ባንኮችን እርስበርስ የሚያስተሳስር እና ደንበኞች ከማንኛውም ቦታ በማንኛውም ጊዜ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉበት አማራጭ ነው ሲሉ ደስታ ተናግረዋል። ‹ኤም ብር› የመጀመሪያው ሞባይል መኒ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 2010 ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው። ኤም ብር ‹የሞባይል ኦፕሬቲንግ ሶፍትዌር ሲስተም› (MOSS ICT) እህት ኩባኒያ ሲሆን፣ ከ6 ብድርና ቁጠባ ተቋሟት ጋር እየሰራ የሚገኝ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰጪ ተቋም ነው። ከእነዚህ ተቋማት አንዱ ኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ነው።
በአይርላንድ ደብሊን ዋና መሥሪያ ቤቱን ያደረገው MOSS ICT በኢትዮጵያ ኤም ብር የሚባለውን ሞባይል መኒ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ ነው። በኤም ብር የሞባይል መኒ ልዩ ልዩ አገልግሎት ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ የሞባይል የአየር ሰዓት መግዛት፣ገንዘብ ማስተላለፍ እና የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም ይቻላል። ኤም ብር በአሁኑ ሰዓት 19ሺሕ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ 1.9 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ እስከ 35 ቢሊዮን ብር ድረስ የሚያስተላልፍ ድርጅት ሆኗል።
የቴክኖሎጂ እድገት ቁሳቁሶችና ዕቃዎች ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ ተቋማዊ መሠረተ ልማት፤ ግልጽ የሆኑ የልማት ግቦች፤ ተስማሚ የሆነ ተቋማዊ ማዕቀፍ፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ ለተቋሞችና ሕጎች ምቹ ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆን እንደሚገባው ደስታ አንሰተዋል።
ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተሻሻለ ጥራትና አቅም በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ነው ደስታ ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት። በመሆኑም የባንኮችን ቴክኖሎጂ ማሳደግ ማለት በቀላሉ ባንኮች በአገልግሎት አሰጣጥ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013



