የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ወደ ትግራይ ክልል የሚልከው የደም አቅርቦት መቋረጡን ገለጸ። ወደ ክልሉ የሚሄድ የትኛውም አይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ለደም አቅርቦቱ ሂደት እንቅፋት መሆኑን ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።
በጤና ተቋማት በህክምና ክትትል ላይ ላሉ ዜጎች እና ግጭት ባሉባቸው ቦታዎች ደም ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ደም እያቀረበ መሆኑን የደም ባንኩ አንስቷል። የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ያረጋል ባንቴ እንደገለጹት፣ ሌሎች አከባቢዎች ላይ የደም አቅርቦቱ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም፣ ለትግራይ ክልል ይቀርብ የነበረው የደም አቅርቦት ግን ተቋርጧል።
መከላከያ ሠራዊቱ ክልሉን ለቆ ከመውጣቱ አስቀድሞ መቐለ በሚገኘው የደም ባንክ ለኹለት ዓመት ያህል የሚያገለግል የደም ክምችት ባንኩ ማቅረቡን የገለጹት ያረጋል፣ አክሱም ላይ ግን እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል። ይሁን እንጅ በተቀሩት የክልሉ አከባቢዎች ላይ ያን ያህል የሚያሰጋ የደም አቅርቦት ችግር ላይኖር እንደሚችል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በክልሉ ውስጥ ባሉ የጤና ተቋማት በህክምና ላይ ላሉ ህሙማን እንዲሁም ለወደፊት ግጭት ከተከሰተ ተጨማሪ የደም አቅርቦት ስለሚያስፈልግ ዜጎች በበጎ ፍቃደኝነት ደም እንዲለግሱ የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።
በግጭቶች እና ጦርነቶች ጉዳት የሚደርስበት ሰው ከበዛ ፍላጎቱ ስለሚጨምር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህ ከሆነም በኢትዮጵያ የማይመከር ቢሆንም የመጨረሻ አማራጭ የሚሆነው የቤተሰብ ምትክ ደም ፈልጎ መጠቀም እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል። ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሙያዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይሄዱ የተደረገ ሲሆን፣ ችግሩ ረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ከሆነ አሳሳቢ እንደሚሆን ገልፀዋል። የመንግስትን አቅጣጫ በመከተል ወደፊት ተግባራዊ የሚሆኑ የሚሻሻሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የአገሪቱን የደም አገልግሎት በማስተባበር በቂና ደህንነቱን የጠበቀ የደም አቅርቦት እንዲኖርና አንድም ዜጋ በደም እጥረት ምከንያት እንዳይሞት ለማድረግ እንደሚሰራ ተነግሯል። እናቶች ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ እስከ ወሊድ ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ በተለያየ ምክንያት የደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው ይችላል። በተለይም በወሊድ ወቅት እስከ አስራ ሁለት ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ በሚገጥም የደም መፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ ብዙዎች ናቸው። ከወሊድ ባሻገር ደግሞ በተለያዩ ግጭቶች ጉዳት ደርሶባቸው ብዙ ደም የሚፈሳቸው ሰዎች ደም ካላገኙ ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ይታወቃል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የደም ማስተላለፍ ሕክምና ትኩረቱን አድርጎ ይሠራ የነበረው ከቤተሰብ ምትክ ደም ተወስዶ በመስጠት ነበር።
ይህም ማለት አንድ ሰው ቢታመምና ለሚሰጠው ሕክምና ደም ቢያስፈልግ ደም የሚሰጠው ዘመድ የግድ ያስፈልገዋል። ቤተሰብ ከሌለው ደግሞ ገንዘብ ይከፍልና ሌላ ሰው እንዲሰጠው ይደረጋል። የደም ማስተላለፍ ህክምና ለረዥም ዓመታት በዚህ መልኩ ሲፈጸም የተለያዩ ችግሮች እንደነበሩበት በተለያዩ ጊዜያት ሲነገርም ተደምጧል። ለባለፉት በርካታ አመታት ደም የሚለገሰው በቤተሰብ ምትክ ስለነበር አቅርቦቱ ውስን በመሆኑ በቂና ደህንነቱ የተጠበቀ ደምም አይገኝም። ከቤተሰብ ምትክ ወይም በግዢ የሚገኘው ደም ብዙ ጊዜ አስተማማኝ እንዳልሆነ ይነገራል። በዚህም ረገድ ለትግራይ ክልል የሚቀርበው የደም አቅርቦት መቋረጡ በዚህ ከቀጠለ በቤተሰብ ምትክ ደም ፈልጎ ለመጠቀም ያስገድዳል ተብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013


