በሱማሌ ክልል ንግድ ባንክ ከ20ሺሕ ብር በታች መላክ አትችሉም በማለቱ ቅሬታ ቀረበበት

በሱማሌ ክልል ቶጎ ጫሌ አካባቢ የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ከ20ሺሕ ብር በታች መላክ አትችሉም በመባላቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናገሩ። በአካባቢው የሚገኙ ቅሬታ አቅራቢዎች ፣ ከሰኔ 28/2013 ጀምሮ በክልሉ ከሚገኝ ንግድ ባንክ ወደ አዲስ አበባ ከ20ሺሕ ብር በታች ገንዘብ መላክ አትችሉም መባላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ የተነገረን ነገር የለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ከቶጎ ጫሌ ወደ አዲስ አበባ ገንዘብ ማስተላለፍ አልቻልንም ብለዋል። እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሆነ ቶጎ ጫሌ አካባቢ የዶላር ምንዛሬ በስፋት ስለሚካሄድ ወደ አዲስ አበባ ገንዘብ የሚላከው ዶላር ከተመነዘረ በኋላ በመሆኑ ላኪዎች ከመነዘሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ተቸግረዋል።

በሱማሌ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ብር በእጃቸው ይዘው ባይገኙ እንኳን አቅራቢያቸው በሚገኝ የገንዘብ አይነት መገበያየት እንደሚችሉ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የያዙትን ብር ለፈለጉት ወገን ማስተላለፍ መብት መሆኑ እየታወቀ ከአቅም በላይ የሚጠይቅ የገንዘብ መጠን ካላስገባህ ማለት ሕገ-ወጥ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ መምህር የሆነው ረዳት ፕሮፌሰር ተኬ አለሙ ገልጿል። እንደ ተኬ ገለጻ ከሆነ ማንኛውም ግለሰብ ገንዘቡን በፈለገበት መንገድ መጠቀም እየቻለ እንደዚህ አይነት እገዳ አግባብነት የሌለው ነው ሲል ተችቷል።

ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ ከ20ሺሕ ብር በታች አታስተላልፉም የሚል አዲስ መመሪያ ማውጣት በራሱ ባንኩን ተጠያቂ እንደሚያደረግው ነው ተኬ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳው። ይህ በሚሆንበት ወቅት እያንዳንዱ ግለሰብ በያዘው ገንዘብ እምነት ያጣል ይላለ ተኬ። ይህ ተግባር ዛሬ በሱማሌ ክልል ያለ ይመስላል እንጂ ቀስ በቀስ ወደ ከተማ በመግባት የከተማ ውስጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል ሲል ስጋቱንም ጨምሮ ገልጿል። ይህ ተግባር ማንኛውም ግለሰብ የያዘውን ገንዘብ በሚፈልገው መንገድ የማይጠቀም ከሆነ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ እንዲጠቀም ይገፋፋዋል። በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትን ሊቀንስ ይችላል ሲል አስረድቷል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የክልሉ ኃላፊዎች፣ በአሁኑ ሰዓት በምን ምክንያት ይህ አገልግሎት እየተተገበረ መሆኑን ሊረዱ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። የግለሰቦችን ቅሬታ ባንኩ በተገቢው መንገድ መፍታት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ብትሞክርም ባንኩ መረጃ እንዳልደረሰው በመግለጽ ኦፊሴላዊ ሐሳብ ማግኘት አልቻለችም። እንደ ባንኩ ምንጮች መረጃ ከሆነ ከ20 ሺሕ ብር በታች መላክ አትችሉም የሚል ሕግ የለም። ምናልባት ችግሩ ከሲስተም ብልሽት ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ከባንኩ ምንጮች ተሰምቷል። ገንዘብ የማስተላለፍ ገደቡ ግን የባንኩ አሠራር አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ማንኛውም ሰው በባንኩ ያስቀመጠውን ብር በየትኛውም ቅርንጫፍ ማንቀሳቀስ የሚችል ሲሆን፣ ማንኛውምንም አካል ባንኩ የመገደብ መብት የለውም ሲሉ የንግድ ባንክ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here