6ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ የማወክና ሂደቱን የማስተጓጎል ተግባር የፈፀሙ ግለሰቦች ተቀጡ

0
459

6ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ የማወክና ሂደቱን የማስተጓጎል ተግባር የፈፀሙ ግለሰቦች የገንዘብ እና የእስር ቅጣት እንደተላለፈባቸው ተገለፀ።

ይህ የተባለው ከ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መ/ቤት ዐቃቤ ህግ አቶ ደለለኝ ብሩ ከጀርመን ድምፅ ሬድዮ (DW) ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።

አቃቢ ህጉ እንደገለፁት ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ድህረ-ምርጫ ሊፈፀሙ የሚችሉ ምርጫ ነክ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ በመደበኛዉ የምርመራና ክስ ሂደት መሄዱ ለጉዳዮች ወቅታዊና አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት አንፃር መዘግየት እንዳይፈጠር በየደረጃዉ ባሉ መዋቅሮች ለዚሁ ዓላማ መርማሪ ፖሊሶችና ዐቃቤያን ህግ ተሰይመዉ አስፈላጊዉ ስልጠና ከተሰጣቸዉ በኋላ ወደተግባር ገብተዉ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ወደህግ አካላት የሚመጡት በፓርቲዎች የጋራ ፎረም ሊፈቱ ያልቻሉ ጉዳዮች ሲሆኑ በነበረዉ የምርጫ ሂደት ከክልሉ 10 ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ 115 ጉዳዮች ሪፖርት ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የተፈፀሙ የህግ ጥሰቶችን በተመለከተ እንዳብራሩት አብዛኞቹ ወንጀሎች የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት የያዙ ፖስተሮችን መቅደድ፣ የምርጫ ቅስቀሳን ማስተጓጎል፣ በምርጫ ጣቢያ ሁከት መፍጠርና የመሳሰሉት መሆናቸዉን ጠቅሰዋል፡፡

ከቀረቡት 115 ጉዳዮች መካከል በ73ቱ ላይ የጥፋተኝነት ዉሳኔ የተላለፈባቸዉ ሲሆን የተፈፀሙት የህግ ጥሰቶች ቀላልና በአብዛኛዉ ደንብ መተላለፍ በመሆናቸዉ ፍ/ቤት የአጥፊዎችን ሁኔታም ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከ200 ብር እስከ 2,500 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮና ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም 15 መዝገቦች በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ፣ ቀሪ ጉዳዮች ማስረጃ ባለመገኘቱ ምርመራ የተቋረጠባቸዉና በፓርቲዎች የጋራ ፎረም መታየት ሲኖርባቸዉ የመጡ በመሆናቸዉ የተመለሱ መሆናቸዉን መግለፃቸውን ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here