የውሃ ትራንስፖርትን ማስፋፋት እና የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው የኢፌድሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ።
ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አካላት በለምለሚቷና የበረሀዋ ገነት በምትባለዋ በጋምቤላ ክልል በመገኘት በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የቀድሞ የጀልባ ማቆሚያ ግንባታንና የጋምቤላ ከተማ መናኸሪያን ጎብኝተዋል።
በሚኒስትሯ የተመራዉ ቡድን ጋምቤላ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጅሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ጋምቤላ እንደገቡ በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የቀድሞ የጀልባ ማቆሚያ ግንባታና የጋምቤላ ከተማ መናኸሪያን የጎበኙ ሲሆን በክልሉ ውስጥ በቅድመ ግንባታ፣ በግንባታና በጥገና ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም እና ቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ከክቡር አቶ ኡሞድ ኡጅሉንና የክልሉ ካቢኔ አባላት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ተደርጓል።
ሚኒስትሯ በጋምቤላ ብ/ክ/መንግስት የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በቀጣይ 10 ዓመት የትራንስፖርት ዘርፍ መሪ የልማት ዕቅድ የውሃ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት እና ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪያዎችን በመገንባት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚል ቃል የተጀመረዉን ኢትዮጵያን እናልብስ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በማስቀጠል በጋምቤላ ክልል ችግኞችን በመትከልም አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ሥራ መስራታቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።







