በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከኹለት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የነበሩት ኢሳያስ ዳኘው የዋስትና መብታቸው ታገደ። ጉዳያቸውን የሚከታተለው የፌድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 6/2011 ተጠርጣሪው በ100 ሺሕ ብር ዋስ እንዲወጡ ትእዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ነው።
ለዋስትናው መታገድ እንደምክንያት የተነሳውም ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ የክስ መመስረቻ ቀን መጠየቁ እንደሆነም ተነግሯል። ይህን ተከትሎም የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ማገዱ ተነግሯል፤ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት እንደሚገኙም ታውቋል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ከያዙት መርማሪ ፖሊስ እንዳረጋገጠችው በተጠርጣሪው ላይ ጥር 7 መቃወሚያ በማቅረብ ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመራቱን ታውቋል።
ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መቃወሚያ በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማጠናከር ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሰፊ መከራከሪያ ነጥቦችን ለችሎቱ አቅርቦ እንደነበር ይታወቋል። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪውን በሚመለከት በመርማሪ ፖሊስ የሚቀርቡ የሰነድ ማስረጃዎችን አለመኖራቸውን ከግምት በማስገባትና የሚቀርቡ ማስረጃዎች ተመሳሳይነት ያላቸው እንዲሁም የተጠርጣሪውን ወንጀል መፈጸም በሚገባ አያመላክቱም በማለት የዋስትና መብት መስጠቱ ይታወቃል።
ተጠርጣሪው በተለይም በሱማሌ ክልልና በባሌ ዞን የሞባይልና ሲዲኤምኤ ማማ ተከላ ጨረታ በማውጣት አወዳድረው መስጠት ሲገባቸው ከሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ከሆኑትና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት ከሚገኙት ወንድማቸው ክንፈ ደኘው (ሜጀር ጀነራል) ጋር በጥቅም በመተሳሰር 2 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺሕ ብር በላይ በማውጣት ከሜቴክ ጋር ሕጋዊ ያልሆነ ውል ገብተዋል በማለት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል።
ተጠርጣሪው በበኩላቸው የማማ ተከላ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ላይ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ኮንትራቱ ለሜቴክ እንደተሰጠ በመግለጽ “የተከናወነው ውልም መስሪያ ቤቱን የሚመለከት እንጂ እኔ ለብቻዬ ያደረኩት ምንም ነገር የለም” በማለት መከራከራቸው አይዘነጋም። እንዲሁም እሳቸው የሚመሩትን ሥራ በተመለከተ ሕጋዊ በሆነ የውል ስምምነት ላይ በመመስረት ከሜቴክ ጋር ውል መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ በጠበቆቻቸው በኩል ሲያስረዱ ቆይተዋል። በተጨማሪም የኢትዮ-ቴለኮም ማኔጅመንት በፍራንስ ቴሌኮም ሲተካ ቀድሞ የነበረው አስተዳደር ከ 10 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆኑ የሥራ ውሎችን ማሻሻልና መዋዋል ስለሚፈቅድ ይህም መሥሪያቤቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ሥራዎችን እንዳከናወኑም ማስረዳታቸው ይታወቃል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የተጠርጣሪ ጠበቆችና ተጠርጣሪው የዋስ መብት እንዲፈቀድላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የተጠርጣሪው የዋስትና መብት በተመለከተና ዕገዳው ላይ ምላሽ ለመስጠት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጥር 27 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011