የተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች 29 ሚሊየን ዶላር አልከፈለም

0
571

የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን በማሰማራት ኢትዮጵያ ማግኘት የነበረባትን 29 ሚሊየን ዶላር የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት የሚጠበቅባቸውን ባለመዋጣታቸው የተነሳ የተባበሩት መንግስታት መክፈል እንዳልቻለ የድርጅቱ መረጃ አመላከተ።
የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን በማሰማራት ከሁሉም ዓለም አገራት ከፍተኛውን ቁጥር የያዘችው ኢትዮጰያ ወደ 11ሺሕ ወታደሮቿን ያሰማራች ሲሆን እስከ መስከረም 2011 ድረስ ለወታደሮችና ለአገሪቷ ሊከፈላቸው የሚገባ ክፍያ እንዳልተፈፀመ ታውቋል።
በጥር 10/2011 የወጣው የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የተባበሩት መንግሥታት አንቶኒዮ ጉተረስ ‹‹ከአባል አገራት በተለያዩ አገራት ሰላም ለማስከበር ማወጣት የነበረባቸው ወደ ሁለት ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዳልተሰበሰበ›› ገልፀው ነበር።
በተለይም በዶናልድ ትራምፕ የምትመራው አሜሪካ አንድ ሦስተኛው ገንዘብ እንደምታወጣ የሚጠበቅ ሲሆን አገሪቷ ለውጭ አገራት የምታደርገውን ድጋፍ እቀንሳለው ማለቷን ተከትሎ ተቋሙ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ተሰግቷል። እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ወደ 221 ሚሊየን ዶላር ሰላም ላስከበሩ አገራት ያልከፈለው የተባበሩት መንግሥታት፤ ‹‹እንደ አሜሪካ ያሉ አንድ አራተኛ የሰላም ማስከበር ወጪን የሚሸፈኑ አገራት በቶሎ የሚጠበቅባቸውን ካልከፈሉ የገንዘብ ችግር ውስጥ ተቋሙ ሊገባ እንደሚችል›› ጉተረስ ገልጸዋል።
እያንዳንዱ የተባበሩት መንግሥታት አባል ለድርጅቱ መደበኛ በጀት እንዲሁም ለሰላማዊ አስከባሪ ኃይሎችን ለማሰማራት አባል አገሩ ካለው አጠቃላይ ምርት እና የነፍስ ወከፍ ገቢ ማዋጣት አለበት። ለምሳሌ ያህል ከዓለም ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት አሜሪካ 22 በመቶ የሚሆነውን የሰላም አስከባሪ በጀቱ መዋጮ ማድረግ ይጠበቅባታል።
ነገር ግን አባል አገራት ያለባቸውን መዋጮ በወቅቱ ስለማይከፍሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ወታደሮቻቸውን ለሰላም አስከባሪነት የላኩ ክፍያቸውን በወቅቱ እንደማያገኙ ማወቅ ተችሏል። በተለይም አሜሪካ እስከ ጥቅምት 2011 ድረስ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ እንዳለከፈለች የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
የተባበሩት መንግሥታት በወቅቱ ክፍያውን ለሰላም አስከባሪ አገራት ባለመክፈሉም እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገራት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ያላቸው ተሳትፎዋቸው እንደቀነሰ ታውቋል። ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ መንገድ እንዳይከተሉ ተሰግቷል።
የተባበሩት መንግስታት ለእያንዳንዱ ሰላም አስከባሪ ወታደር በወር እስከ 1,400 ዶላር ይከፍላል። ይህ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ 50 ዶላር በታች አገራትን የበለጠ ተሳትፏቸው እንዲጨምር እንዳደረገ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በተጨማሪም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ አገሮች የሰላም አስከባሪ ኃይልን እንደ ተፅዕኖ መሳሪያዎች አድርገው ይጠቀማሉ ይህም አገሪቱን ሀላፊነቷን በአካባቢያዊ ሁኔታ እንድትገነባ እና ምስሏን ለማሻሻል እንደረዳት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ቀደም ሲል ኮንጎ ነጻ ከወጣችበት ማግስት አገሪቱን የማረጋጋት ስራ ላይ ከመሳተፍ ጀምሮ፣ በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋና በላይቤሪያው የርስበርስ ጦርነት ላይ የሰላም አስከባሪ ሃይል በመላክ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።
በቅርቡም የመከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ሚኒስቴር የስድስት ወር ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት የአገር መከላከያ ሠራዊት በዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል ሲሉ ምክትል ኢታማጆር ሹም ብርሃኑ ጁላ ገልፀው ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በዳርፉርና በአቢዬ በሂደት የሚሰማሩ ተጨማሪ አባላት በሁርሶ ማሰልጠኛ ሥልጠናቸውን ጨርሰው በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ፤ ከሰላም ማስከበር የሠራዊት ምደባ ጋር በተያያዘ ባቀረበበት ወቅት ከሠራዊቱ በኩል ቅሬታ እንዳለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተነስቶ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here