ቢራና አልኮል አምራቾች ሎተሪ አንዳይጠቀሙ ሐሳብ ቀረበ

0
680

የቢራ እና አልኮል አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅም ሆነ ለሌላ ዓላማ ሽልማት እና ሎተሪዎችን እንዳይጠቀሙ በፓርላማ የሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐሳብ ቀረበ። ቋሚ ኮሚቴው ጥር 15 በምግብ እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ሎተሪ እና ሽልማት መብዛቱ ተጠቃሚነትን ስለሚያበረታታ ሊቆም ይገባል ሲል አቋሙን አሳውቋል።

በተለይም አምራች አካላት እና ከተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የተወከሉ የህክምና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶችና ሲቪክ ማኅበራት ክርክር ባካሄዱበት ወቅት ረቂቅ አዋጁ በአልኮል ምርቶች የማስታወቂያ ሰዓት ላይ ባደረገው ገደብና የአልኮል ተጠቃሚዎች የዕድሜ ገደብ ከ18 ወደ 21 እንዲሻሻል መደረጉና ሽልማት እና ዕጣ በምርቶቻቸው ላይ እንዳይጠቀሙ የተነሳው ሐሳብ የቢራና በአልኮል አምራቾች ክፉኛ ተተችቷል።

የሄኒከን ኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ ፍቃዱ በሻህ ባቀረቡት ሐሳብ እንደ ድርጅት ማንም ሰው የአልኮል ተጠቂ እንዳይሆንና ከ18 ዓበታች የሆኑ እንዳይጠጡ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑንና ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኢንቨስትመንት እንዳደረገ፤ ለመቶ ሺዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እንዲሁም 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ግብር እንደሚከፍል ገልጸዋል። ይሁን እንጂ፤ አዲሱ ረቂቅ አዋጅም ሆነ በቋሚ ኮሚቴው የቀረቡት ሐሳቦች የቢራ ኢንዱስትሪውን እና ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሜታ ቢራ ፋብሪካ ተወካይ ባቀረቡት ሐሳብ ቢራ ከመሸጥ በተጨማሪ ስማሽ የሚባል ፕሮጀክት ቀርጸው ታዳጊ ሕጻናት የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እና የማንበብ ባሕላቸውን የተለያዩ እገዛዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
በመቀጠል ከኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ባነሱት ሐሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ 7 ብሔራዊ ቡድኖች እና ከ150 በላይ ክለቦች አሉ ብለዋል። ብሔራዊ ቡድኑን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ከቢራ ፋብሪካዎች በሚገኝ ስፖንሰርሺፕ ዓመታዊ በጀታቸውን እንደሚደጉሙ፤ በተጨማሪም እነዚህ ቢራ ፋብሪካዎች እግር ኳሱን በከፍተኛ ሁኔታ እየረዱ እንደሚገኙ ረቂቅ አዋጁ እንዳይጸድቅ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል፤ በውይይቱ ላይ የተገኙት አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የሳንባ ሀኪም የኢትዮጵያ የሣንባ ባለሙዎች ማህበር ረቂቅ አዋጁን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉት ገልጸው የቢራ ፋብሪካዎች እንደሚሉት ግን ፅንፈኛ እንዳልሆኑ ይልቁኑም ኅብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለው ማኅበራዊ ቀውስ ሊታሰብበት እንደሚገባና ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ እና ወቅታዊ ነው ሲሉ በአጽዕኖት ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በተቃራኒው፤ በአልኮልና ትንባሆ አምራች ድርጅቶች በኩል የተወከሉ ግለሰብ የተደራጀ ˝ፅንፈኛ አካል˝ የቢራ ኢንዱስትሪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር እየሠራ እንደሆነ ገልጸው ይሁንና ይህ ድርጊት አግባብ እንዳልሆነ በማመልከት በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ፣ ሥራ ዕድልና ከፍተኛ የሆነ ግብር እየከፈልን በመሆኑ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በሥራችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድርብናል የሚል አንድምታ ያለውን ሐሳብ አቅርበዋል።

በአንጻሩ ደግሞ ከተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉት ባለሙያዎች ረቂቅ አዋጁ ወቅታዊ እና ኅብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በአግባቡ የዳሠሠ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ቋሚ ኮሚቴው የቢራና አልኮል ማስታወቂያዎች ሙሉ በሙሉ በቴሌቪዥን እና ሬድዮ እንዳይተላለፍ እና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የሽልማት እና ሎተሪ ዕጣዎች ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ እንዳይውሉ የሚለውን ሐሳብ አቅርቦ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here