ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ፋብሪካዎች መከፋፈል ጀምሮ የነበረው ነዳጅ መቋረጡን የማዕድንና የነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው ከዚህ በፊት ይከፋፈል የነበረው ነዳጅ በሱማሌ ክልል ኦጋዴን ላይ ተገኘ የተባለው ነዳጅ እንደሆነ ገልፀው በጊዜው እንዲከፋፈል የተደረገው ለናሙና የሚወጣው ነዳጅ ከሚቃጠል ጥቅም ላይ እንዲውል በማሰብ ነው ብለዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እንደተገለፀው ሚኒስቴሩ ነዳጅን ለፋብሪካዎችም ሆነ ለንግድ የማከፋፈል ፈቃድ እንደሌለው ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ለገኺዳ ወረዳ ተገኘ ስለተባለው ድፍድፍ ነዳጅ ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው ከዚህ ቀደም በአንድ የእንግሊዝ ኩባንያ ጥናት ተደርጎ ነዳጅ መኖሩ የተረጋገጠ ቢሆንም ኩባንያው ባጋጠመው የገንዘብ እና የቴክኖሎጂ እጥረት ቀጣይ ሥራዎችን መሥራት ባለመቻሉ አቋርጦ መውጣቱን ገልጿል። በዚህም መሠረት የኩባንያውን ሥራ ማቆም ተከትሎ ምን ያህል ክምችት እንዳለ ለማወቅ አለመቻሉን መሥሪያ ቤቱ አስረድቷል። ተያይዞም እንደተገለፀው በአሁኑ ሰዓት መስፈርቱን ለሚያሟላ የትኛዉም ኩባንያ ክፍት መሆኑን ጨምሮ አሳውቋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሱማሌ ክልል ተገኙ የተባሉት የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ በአሁኑ ሰዓት ቅድመ ሁኔታዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጿል።
በዚህም ረገድ ከተፈጥሮ ጋዝ ጋር በተያያዘ የቱቦ ዝርጋታ እየተካሄደ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በድፍድፍ ነዳጅ በኩል ደግሞ ናሙናው እየወጣ ጥናት ተደርጎበት ምን ያህል እምቅ ክምችት እንዳለው ለማወቅ እየተሠራ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። በዚህም መሠረት ካሉብ እና ሂላላ በተባሉ ኹለት የተፈጥሮ ጋዝ ማዉጫ ቦታዎች ከስድስት እስከ ሰባት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ማግኘት መቻሉን ለማወቅ ተችሏል።
ይህንም ተከትሎ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከሱማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነዳጅ ቁፋሮ እና ተጠቃሚነት ዙሪያ ውይይት ያደረገ ሲሆን ከክልሉ መንግሥት ጋርም በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችላቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሚኒስትሩ ጥር 4 እና 5 በቢሾፍቱ ከተማ የፔትሮሊዪም ረቂቅ ሕግና ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሒዷል። ፖሊሲና ሕግ ማውጣት ያስፈለገበት “መንግሥት በዘርፉ ላይ የጣለውን አገራዊ አደራ ለማሳካት ዘርፉ በሕግ እና በፖሊሲ መመራት አለበት” ሲሉ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ኩዋንግ ቱትላም ገልፀዋል። የረቂቅ ሕጉና ፖሊሲው የሚኒስቴሩ ሠራተኞች በተገኙበት ውይይት ከተደረገበት በኋላ መጨመር ያለባቸው ወይም መቀነስ የሚኖርባቸው ተስተካክሎ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንደሚቀርብ ታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011