በዘንድሮ ዓመት ከቡና የውጭ ንግድ ገበያ 907 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለፀ

0
828

በዘንድሮ ዓመት ከቡና የውጭ ንግድ ገበያ 907 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለፀ። ይህም ታሪካዊ ነው ሊባል የሚችል የኤክስፖርት ግኝት መሆኑ ተነግሯል።

ለዚህም የገቢ ማደግ የተጀመሩ አዳዲስ አሰራሮችና የግብይት አማራጮች እንዲሁም ቅንጅታዊ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽዖ ነበራቸው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች፣ ቡና አልሚዎች እንዲሁም ቡና አቅራቢዎች ማህበር ከፍተኛ አመራሮች በዘንድሮው የቡና ኤክስፖርት አፈጻጸም ዙሪያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ፤ ኢትዮጵያ በዘንድሮው 2013 በጀት ዓመት ወደ ውጭ አገራት ከላከችው የቡና ምርቷ ታሪካዊና አስደናቂ ሊባል የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሏንና በአሥራ ሁለት ወራት ውስጥ 248,311.66 ቶን ቡና በመላክ 907.04 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ እንደተገኘ አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በተለይም በባለፉት ስድስት ወራት ለዓለም ገበያ በቀረበው ቡና መጠኑ በጥቂቱ የቀነሰ ቢሆንም፣ ከዋጋ አንፃር ሲታይ ግን ከፍተኛ ጭማሪ የታየበትና በአንድ ቶን ይገኝ ከነበረው 3,100 ዶላር ወደ 3,700 ዶላር ከፍ ማድረግ የተቻለበትና ለዚህም ቡናዎቻችንን በጥራት ማቅረብ መቻሉ፣ ዘመናዊ የግብይት ስርዓቶች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው እና አዳዲስ የግብይት አማራጮች ሥራ በመጀመራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የግብይት አማራጮቹም ህግና ደንብ ተዘጋጅቶላቸው በሚፈጸሙ ውሎች ተግባራዊ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ደሳለኝ ጀና፣ የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሁሴን አምቦ፣ የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንዲሁም አቶ ፈጠነ የኋላሸት የኦሮሚያ ቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝደንት እንዳስረዱት ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር በቅንጅት መስራታቸው ለዚህ ውጤት እንዳበቃቸው የተናገሩ ሲሆን በተለይም አሁን የተጀመረው የቡና ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉ ለቡናው የውጭ ምንዛሬ እድገት ጉልህ ሚና እንደነበረውና የአርሶ አደሩም ሆነ በየደረጃው የሚገኘው ተዋናይ የድካሙ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

ለወደፊቱም ይህንኑ ተቀናጅቶ የመስራት ባህላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አጽንዖት መስጠታቸውን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለማወቅ ተችሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here