“እናት ለምን ትሙት?”

0
808

በያዝነው ጥር ወር በጤና ሚኒስቴር እየተከበረ ያለውን የጤናማ እናትነት ወርን መነሻ በማድረግ ቤተልሔም ነጋሽ በኢትዮጵያ የእናቶችን ጤና አጠባበቅ ከዓመት ዓመት ብዙ መሻሻሎች መደረጋቸውን በመጥቀስ የበለጠ ውጤት ለማምጣት ግን እንቅፋቶችን ለይቶ ለማስወገድና የተሻለ ጥራት ያለው የእናቶች ጤና አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበቃል ሲሉ ያሳስባሉ።

 

 

ከሦስት ዓመታት በፊት የነበረ መረጃ እንደሚለው በዓለም 5 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተገናኘ ይሞታሉ። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እኤአ በ1980 ከ100 ሺሕ ወሊዶች 422 እናቶች ይሞቱ የነበረ ሲሆን የሞቱ ቁጥር በ2010 እኤአ ወደ 521 ከፍ ብሏል።

በዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ መሠረት ደግሞ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እኤአ ከ1990 እስከ 2013 በተደረገ ቅኝት የእናቶች ሞት አሐዝ በዓለም ደረጃ በ45 በመቶ ቀንሷል። ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ይህ ቁጥር 49 በመቶ ሲሆን በኢትዮጵያ በዚሁ ወቅት የታየው ቅናሽ 38 በመቶ ሲሆን ከዓለምም ሆነ ሰሃራ በታች ካሉ አገራት ሁሉ ዝቅተኛው ነው። ከ43 ሺሕ ሞት ወደ 13 ሺሕ ዝቅ በማለት በአገራችን ከፍተኛ ለውጥ ቢመጣም በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የተቀመጠውን በሦስት አራተኛ የመቀነስ ግብ አላሳካንም።

የኢትዮጵያ የጤና ሳይንስ ጆርናል የሴፕቴምበር 2014 ዕትም ላይ የወጣ በኢትዮጵያ ከዚያ በፊት በነበሩ 30 ዓመታት የነበረውን የእናቶች ሞት ሁኔታ የዳሰሰ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚለው፣ አገራችን በዓለም ላይ ከሚከሰተው የእናቶች ሞት 50 በመቶውን ከሚይዙ የዓለማችን 6 አገሮች (ከእስያ ሕንድ፣ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን፤ ከአፍሪካ ከናይጄሪያና ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ተደምራ) አንዷ ናት። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚረዱ የተለያዩ ፕሮግራሞችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተለይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በልማት አጋሮች ትብብርና የዓለም አገራት ተሳትፎ የተረቀቀው የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች የተሰኘው ዕቅድ እንዲሁም የጤና ሴክተር ልማት ፕሮግራም የእናቶችን ሞት መቀነስን እንደ አንድ ግብ ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተለይ የሚሊኒየሙ የልማት ግብ አምስት ወይም “የእናቶችን ጤና ማሻሻል” በሚለው ሥር የእናቶችን ሞት በ2015 ቢያንስ በ3/4ኛ የመቀነስ ዕቅድ ነበረው።

ግብ አምስት በኢትዮጵያ ሊሳካ ታቅዶ ከነበረባቸው ስትራቴጂዎችም ወሊድ ሁሉ በሠለጠነ አዋላጅ እንዲከናወን ማድረግ፣ ሴቶች በትምህርት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግና በመደበኛ ሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ማድረግ የሚሉ ነበሩ። በተለይ የመጀመሪውን ስትራቴጂ ለመተግበርም ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ በጤናው ዘርፍ የሚታይ ለውጥ እንድታመጣ አግዟል የሚባለው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እኤአ በ2003 ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ለመድረስ እንደ አንድ መንገድ በተለይ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ቤት ለቤት እንዲሰጥ በማድረግ የእናቶችን ሞት መቀነስ ያሉ ዋና ተግባራትን እንዲያከናውኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በመላው አገሪቱ ተሠማርተው ሲሠሩ ቆይተዋል።

በቀድሞው አጠራር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሁን ራሱን እየጠራበት ባለው ሥሙ የጤና ሚኒስቴርም በዚህ ወር የጤናማ እናትነት ወርን በማክበር ላይ ይገኛል።
የዛሬ 13 ዓመት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጤናማ እናትነት ወር “እናት ለምን ትሙት” በሚል መሪ ቃል ሲከበር አገርኛ አባባሉን በመጠቀምም ይሁን የተሳካ ሕዝብ ውስጥ የገባ ዘመቻ በማድረግ ስኬታማ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። ቀጥሎም በየዓመቱ ሲከበር “አንድም እናት በወሊድ ሞት የለባትም”፣ “ሕይወት ለመስጠት ሕይወት ማጣት የለባትም” ወዘተ የሚሉ መሪ ቃሎች ነበሩ። በእርግጥ ከዘመቻዎቹ ባሻገር የጤና ዘርፉን ለማሻሻል ከሚሠሩ ሥራዎች ወሊድን በጤና ተቋማት በነጻ እንዲሰጥ ከማድረግ ጀምሮ ባለሙያዎችን በማሠልጠንና የጤና ተቋማት እንዲገነቡ በማድረግ ብዙ መሻሻሎች ተደርገዋል።

አሁንም ግን ትንሽ የማይባል ቁጥር ያላቸው እናቶች ከወሊድ ጋር በተገናኘ ይሞታሉ። ይህም የሚያመለክተው አሁንም “እናት ለምን ትሙት” ብንልም ከእናቶች ሞት ጋር በተገናኘ አገሮች ሲጠሩ ሥማችን ይነሳል። አሁንም በዚህ ረገድ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን።

ለዚህም ነው የዘንድሮው የጤናማ እናትነት ወር በዓል “በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በባሕር ዳር ከተማ ሲከበር የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) “የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ብዙ መንገድ ተጉዘናል” ካሉ በኋላ፥ በየዓመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት በፊት ከነበረው በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም በዓመት እስከ 13 ሺሕ የሚደርሱ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱ መረጃዎች ስለሚያሳዩ ተጨማሪ ጥረት እና ቀጣይነት ያለው ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።

የእርግዝና ክትትል አለማድረግ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የደም ግፊት ችግርና ሌሎች አደገኛ ምልክቶች ሲኖሩ በወቅቱ አለማወቅ፣ በጤና ተቋማት ባለመውለድ ምክንያት የደም መፍሰስ ሲኖር በአስቸኳይ ድጋፍ አለመገኘት የእናቶች ሞት እንዳይቀንስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

እኤአ በ2011 የወጣው የሕዝብና ጤና ጥናት ግምት መሠረት የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉት እናቶች ከአጠቃላይ ነፍሰጡሮች 41 በመቶ ያህሉ ሲሆኑ በሠለጠነ ባለሙያ የሚወልዱት 14 በመቶ ብቻ ናቸው። በዚሁ ግምትም በኢትዮጵያ ከ100 ሺሕ ወሊዶች መካከል 646 ያህሉ የእናቶችን ሕይወት የተቀጠፉ ናቸው። የጤና ሚኒስትሩ የጤናማ እናቶች ወርን አስመልክቶ እንደተናገሩት ደግሞ ዛሬም 72 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በቤት ውስጥ ይወልዳሉ። ይህ ደግሞ 50 በመቶ ለሆነው የእናቶች ሞት ምክንያት ለሆነው የደም መፍሰስ ያጋልጣል።

ኢትዮጵያ አሁንም በዚህ ረገድ ከተመዘገበው የበለጠ ውጤት ለማምጣት ያላስቻሉትን እንቅፋቶች ለይቶ ለማስወገድና የተሻለ ጥራት ያለው የእናቶች ጤና አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here