ለውጥ ከራስ ይጀመር!

0
467

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እናቴ ብቻዋን ነው ያሳደገችን፤ እኔን ጨምሮ እህትና ወንድሜን። ለዚህ የእናትነት አገልግሎቷ አንድም ቀን ሒሳብ ጠይቃ አታውቅም። በእኛ በልጆቿ ስም ያፈሰሰችው ላብ፤ ለሆድ እንጀራ ሳይሆን ለመንፈስ እርካታን ብቻ ያገኘችበት ነው። ሲጠቃለል እናትነት ሠርተው የማይበሉበት የአገልግሎት ዓይነት ውስጥ ይካተታል።

በጥቅሉ ወላጅነት ወይም አሳዳጊነት እንዲያ አይደለ?
እንደምናውቀው ደግሞ «በድካም ብላ» ተብሏል፤ አዳም። መሬትን እንዲቆፍር፤ አርሶ አጭዶ፤ በላቡ እንዲበላ ከፈጣሪው ታዝዟል። ነገሩ ያኔ ለአዳም ተባለ እንጂ…አሁን ከእልፍ ዓመታት በኋላ…አዳሜም ሔዋኔም ጥራ ግራ በላቧ ካልሆነ መብላት የሚታሰብ አይደለም።

እነዚህ ሁለት ሥራዎች፤ አንዱ በአደባባይ አንዱ በጓዳ የሚከወኑ ናቸው። ወላጅ በቤት ልጁን ሰው አድርጎ ይሠራል፤ ውጪ ደግሞ ለሆድ ማሟያውን ይሰበስባል። እኔን ግርም የሚለኝ ግን፤ የአደባባዩ ሥራ ተከብሮ የጓዳና የማጀቱ አገልግሎት የመናቁ ነገር ነው። አዎን! አደባባይ መዋልና ባለሥልጣን መሆን ጥሩ ነው፤ ግን ሙሉ ጊዜን ለቤተሰብ ሰጥቶ ቤትን ከመምራት ይበልጣል ማለት አይደለም።

ለልጆቿ ስትል የምትወደውን ሥራዋን «ይቆየኝ» ያለች እናት አውቃለሁ። ልጆችዋን የተሻለ እውቀትና ማንነት ሰጥቶ ማሳደግን ስለመረጠችና ራስ ወዳድ ስላልሆነች፤ ተቀጥራ ከምታገኘውና ከምታስገኘው ትርፍ አብልጣ ለአገር የሚተርፍ ሰው ለማበርከት ፈለገች። ለዚህች እናት ከአንድ ሚኒስትር የላቀ ክብር አለኝ። ደግሞም የትኛውም ሙያ ላይ በመልካምነት የሚያገለግል ሚኒስትር እንዲህ ካለች እናት የተወለደ ነው።

የጥፋቱ ሁሉ መነሻ የሚመስለኝ እንደውም ይህ የቤቱን ሥራ መናቅ ነው። አደባባዩን እያደመቅን ቤቱን ችላ ካልነውማ፤ አሳመርን ያልነውን የሚያበላሸው ከገዛ ቤታችን የሚወጣው ነው። ይህ ወንድ ወይም ሴት ሆኖ የመፈጠር ጉዳይ አይደለም። ሰው ሆኖ ስለመሠረቱት ቤተሰብ ኃላፊነትን መውሰድ ነው።

አንድ አባት «ቤት ሆኜ የልጆቼን ዕድገት መከታተል እፈልጋለሁ» ቢልስ? ባለቤቱ የምታመጣው ገቢ ለኑሮ ከበቃቸው፤ ቤተሰብ የሚያህልን ተቋም ጊዜ ሰጥቶ ቢንከባከብ ክብሩ ስለምን ይቀንሳል? ነገሩን አልን እንጂ፤ በዚህ ጊዜ ኑሮው እንኳን አንድ ሰው ለብቻ ሙሉ ቤተሰብ ዘምቶበትም ቀላል አልሆነም።

አትጠራጠሩ፤ በአገራችን በየጊዜው የምንሰማው ደስ የማይል የሰዎች ድርጊት፤ ከተሳሳተ ስርዓተ ትምህርት የመጣ አይደለም፤ ከተዘናጋ ቤተሰብ፣ አደባባዩን እንጂ ቤቱን ከናቀ ማህበረሰብ ነው። ምንጭ ሀይቅና ባህርን አያክልም፤ ግን መሠረታቸው እርሱ ነው። አገርም የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። ቤተሰብ አገርን አያክልም፤ አንድ ሰው ብቻውን አገር አይባልም፤ ግን አገርን የሚሞላና ከፍ የሚያደርግ እያንዳንዱ ቤተሰብ ወይም እያንዳንዱ ሰው ነው። እናም እንላለን፤ ክብር ቤታቸውና ቤተሰባቸውን ለሚያከብሩ እናቶች።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here