ጦርነቱ ዕወቅት፣መርህና ሕዝብን ያማከለ ይሁን!

0
875

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥለው ካለፉ በርካታ ውጊያዎችና ጦርነቶች መካከል ዘንድሮ የተጀመረው የሰሜኑ ጦርነት ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ ይነገራል። በቀደመው ዘመን ተሸናፊ ወገን በአንድ ውጊያ መሸነፉን የሚያምንበትና ሕዝብ እንዳያልቅ ወታደሮቹም ቢሆኑ ከድተው ለአሸናፊው የሚገቡበት ነበር። የጦር መሳሪያዎቹ ጅምላ ጨራሽ ባልነበሩበት በቀደመው ዘመን ውጊያዎች ተራዝመው የጦርነትን ማብቂያ አያራዝሙም ነበር። አንዱ አሸንፎ ሲያባር፣ ሌላ ጊዜ ተሸናፊው አድፍጦ ሲበቀልና ድሃው ወታደር የሚያስብለት ጠፍቶ በተከታታይ ሲረግፍ አይሰማም ነበር። ይልቁንም ያልተጻፈ ወታደራዊ ሕጋችን እንደሚያዘው ከምሽቱ 11 ሰዓት በኋላ ወታደሮች የማይሸሹ ከሆነ መሪዎቹ ጭፍራዎቻቸው እንዳያልቁባቸው ራሳቸው ለመሸሽ ይገደዱ ነበር።

የዘንድሮ ውጊያዎች ግን ቅድሚያ ለወታደሩ የሚያስብለት አዋጊ ባለመኖሩ ከሩቁ ግባና ውጣ እየተባለ ሲታዘዝ ሄዶ ይሞታል። ከባድ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የተያዘ ገዢ መሬትም ለፖለቲካ ድል ሲባል እንዲለቀቅ ይወሰናል። በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ለታዘዘው ዓላማ ሲል የወደቀው ወታደር ደመከልብ ሆኖ ቤተሰቡም ያለጧሪ ቀባሪ ይቀራል። በተለይ ወታደራዊ የዕዝ ሰንሠለቱ የማያውቀውና የተደረገለትን ጥሪ ሰምቶ ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተሰልፎ ጦርሜዳ የሚቀረው ቀባሪ እንኳን ስለማግኘቱ እርግጠኛ የማይኮንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

ዓለም አቀፍ የጦር ሕግ ለጦር መሳሪያ ሻጮች የሚስማማ ተደርጎ እንደተቀረጸ የሚናገሩ ምሁራን ለመገዳደልም ወግ ሊኖር ይገባል ቢሉም፣ ጦርነት ሕዝብ እየተፈራረቀ እንዲተላለቅ የሚያደርግ መሆን እንደሌለበት ይስማማሉ። ለምሳሌ ሕጉ፣ ከፓራሹት የሚወርዱ መሬት ረግጠው ሊገሉህ እስኪተኩሱ ጠብቅ ይላል። ‹የተመቸ ጊዜህን አሳልፈህ እስኪመቸው ጠብቅ› የሚል ሕግ ተመጣጣኝ ሆነው እንዲተላለቁ የሚፈልግ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም። ተመጣጣኝ ኃይልን ተጠቀሙ የሚለው ሌላው ግራ አጋቢ ፅንሰ-ሐሳብ ለጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲመች ተብሎ የገባ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የጦርነት አስከፊነትን የሚጠራጠር ባይኖርም፣ አፋጣኝ ዕርምጃ የሚወስድና ድልን በቶሎ የሚጎናጸፍ ሲኮነን የሚታይበት ጊዜም አለ። ለምሳሌ፣ የስሪላንካ መንግሥት ለዓመታት ያስቸገሩትን ታሚል ታይገሮች ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ከቦ በደመሰሰበት ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ደርሶበት ነበር። የውግዘቱ መነሻ ታሚሎች ጥሩ ሥራ ሠርተዋል ተብሎ ባይሆንም፣ የማሪያም መንገድ የምንለው አይነት መሽሎኪያ ተሰጥቷቸው አገግመው እንዲነሱና መልሰው እንዲራኮቱ ይመስል ነበር።

የሚጣላ ከሌለ ዳኛ እንደማያስፈልገው፣ ሠላም ከሰፈነም የጦር መሳሪያ የሚገዛቸው ስለሌለ ከቻሉ ያባላሉ፣ ካቃታቸው ደግሞ ስጋት እየፈጠሩና ደካማውን እያገዙ ለኹለቱም ወገን እስካፍንጫቸው ያስታጥቃሉ። የሰው ኃይል እንዳይመናመንባቸውም የእስረኛ ልውውጥ እያስደረጉ ጦርነቱን ያራዝማሉ። እንዲህ አይነቶች ምድርንና መንግሥትን ጦር አምጡ እያሉ የሚያሰባብቁ አካላት መቼም ቢሆን ከጎናችን እንደማይቆሙ ታውቆ የውስጥ ጉዳያችንን ያለማንም ጣልቃገብነት ማከናወን እንዳለብን አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። የውጭ ማዕቀብ ተፈርቶ ከዓላማ ዝንፍ መባል እንደሌለበት ቢታመንም፣ የአንድ አገር ዜጎች ጎራ ለይተው የሚፋለሙበት እንደመሆኑ ዱላ አቀባዮች እንዳይጠጉ ኹሉም ለራሱ ሲል መጠንቀቅ አለበት።

ከሶሪያ፣ የመንና ሊቢያ ተምረን ትውልድ የሚፈጅ ተግባር ውስጥ መግባት እንደሌለብን ግልጽ ነው። የኃያላን ጡንቻ መፈታተሻ ላለመሆን ኹሉም የበኩሉን ሊጥር ይገባዋል። አቅም ቢያንስ እንኳን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ፈቅዶ ለትውልድ የሚተርፍ እዳና ውድመት ከማስከተል መሸነፍን በጸጋ መቀበል ቆይቶ አንሰራርቶ ለመነሳትም እድል ይሰጣል። ወድቆ መንፈራገጡ ለመላላጥ ከመዳረጉ ባሻገር፣ በቀላሉ የማይተካ ትውልድን በከንቱ ያሳጣል። ጸንቶ ለማይቀር ክብርና ሐብት ሲባል ወጣትና ሕፃናትን ሳይቀር በጦርነት መማገድ ኋላ ላይ ልጆቻችንን አስጨረሳችሁብን የሚል ከጉያ ውስጥ እንዲነሳ ማድረጉ ሊዘነጋ አይገባም።

አንድ ልጅዋን በስቃይ ወልዳ፣ በዚህ ኑሮ ውድነት እየተንከራተተች አሳድጋ፣ ምንም ጠብ ለማይልላት ነገር አንዲት ድሃ እናት በእርስበርስ ጦርነት ልጇን ስትነጠቅ ጠላት የምታደርገው ሁሌም ልጇን የገደለውን አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለልጇ መዝመት ምክንያት የሆነውን ልትጠላና ገዳዮቹንም ልታደንቅ የምትችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አፄ ቴዎድሮስ ቤተሰቦቿን ጨርሰውባት እሳቸውን ስተከተል ከኖረችው ሴት መማር ይገባል። የአንድ ሰው ነፍስ ደረጃ ሊሰጠው የማይገባ ክቡር እንደሆነ በተለይ የጦር አዛዦች ሊገነዘቡት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ለአገር ለወገን ብሎ ቤተሰቡን ጥሎ መግደልና መሞት አለበት የተባለ ቦታ የዘመተ ግለሰብ ሊሰጠው የሚገባ ክብርና እንክብካቤ መለያየት የለበትም። የሆነ ቡድን አባል ስለሆነ፣ አሊያም ከሆነ አካባቢ ስለመጣ ብቻ ከሌላው ተለይቶ ሊታይ አይገባም። ኹላችንም ያለን ነፍስ፣ የተሸከምነውም ሰውነት እኩል እንደመሆኑ፣ ለኛ ሲል ሊሞትልን የሚዘምት የሚያስፈልገው ነገር ኹሉ ሊሟላለት ይገባል። የይድረስ ይድረስ ብቻ ታስቦ ያለምንም ዝግጅት ሕይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ማጋፈጡ ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር፣ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስከፈሉ የአንዲን ሰው ሕይወት በከንቱ እንድትጠፋ በማድረጋቸው ሠላም ሲመጣ ሕግ ፊት መቅረባቸው አይቀርም። የሕዝብ ሞራል እንዳይሰበርና የተዋጊዎችም ሞራል እንዳይላሽቅ እልህ ውስጥ ከሚያስገባ ድርጊትና ንግግር መቆጠብም ያስፈልጋል።

ድል ከፈጣሪ ነው በሚባልበት አገር በጦር መሳሪያና በብዛቱ የሚተማመን ትውልድ እንደመብዛቱ መተላለቃችን እንደማይቀር የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። አንድ ሐሳብም ሆነ አመለካከት ትክክለኛነቱ የሚታወቀው በዕውቀት ተመስርቶ በሚደረግ ልኬት እንጂ በደጋፊው ብዛትና ጉልበት አይደለም። አሸናፊ የሚያደርገው የቁስም ሆነ የቁጥር ብልጫ መኖሩ ሳይሆን ስለራስ ያለ አመለካከትና የሥነ-ልቦና ዝግጁነት እንደሆነ የጦር መሪዎች ሲናገሩ ይሰማል። ኃይል ከጉልበት ያለውን ልዩነት ለሚያውቅ በዳይ ሳይሆን ተበዳይ ማሸነፉ እንደማይቀር ያውቃል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሆን ተብሎ የውሸት ታሪክ እየፈጠሩ የተበዳይነት መንፈስ መፍጠሩ እስኪታወቅ ኹለቱም ወገኖች እንዲተላለቁ ሊያደርግ ይችላል። በፍልሚያው በቀጥታ የማይሳተፍ ሌላ ሦስተኛ ወገን የተጣሉበትንም ጭምር ለመውረስ ያበቃዋል እንጂ ከሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ኹለቱም የሚያተርፉት በጎ ታሪክም ቢሆን አይኖራቸውም።

“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው አህያ፣ ጅብም ከሞትኩ አይቀር አህያም ጭምር ትጥፋ ካለ ኹለቱም ተበልተው እስኪያልቁ ለጥንብ አንሳ ሲሳይ ይሆናሉ እንጂ፣ ምኞታቸው ተሳክቶ በመሞታቸው ለቀሪ እንስሳትና አራዊት እንኳን የሚጠቅሙበት ዕድል አይኖራቸውም። “ለአንድ ብርቱ ኹለት መድኃኒቱ” የሚለው ብሂል ለጦር ሜዳ ሊያገለግል ቢችልም ቦታና ጊዜን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ይገድቡታል። አንድ የሸመቀን ኃይል ለማስወገድ ለአንዱ 10 ገደማ አጥቂ እንደሚያስፈልግ የጦር ጠበብቶች ይናገራሉ። በዚህ ስሌትም ቢሆን ትግራይንና አማራ ክልልን በመሳሰሉ መልክአ ምድራዊ አቀማመጦች ውስጥ ያለን ሸማቂ በጉልበት ብቻ ለማስወገድ እንደማይቻል የሞከሩት ያውቁታል። ሊሳካ የማይችል ግብ እንደሆነ እያወቁትና ዝም አሉ ላለመባል ህሊናቸውን ሸጠው አላስፈላጊና የማያባራ እልቂት ውስጥ አገሪቷ እንዳያስገቧት የሚመለከታቸው በሙሉ አካሄዳቸውን እንዲያጤኑት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here