የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሻንግቼንግ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በደብረብርሃን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሶስት ሼዶችን ለማከራየት የውል ስምምነት ፈፀመ

0
680

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሻንግቼንግ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በደብረብርሃን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሶስት ሼዶችን ለማከራየት የውል ስምምነት መፈፀሙን አስታወቀ፡፡

የሼድ ኪራይ ውሉን ለማካሄድ የሚያስችለውን የውል ስምምነት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እና የሻንግቼንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ካንዲ ተፈራርመዋል፡፡

ሻንግቼንግ በጋርመንት እና ቴክስታይል ዘርፍ የተሰማራ የቻይና ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በደብረብርሃን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ስራ ለመጀመር ዛሬ የኪራይ ውል ስምምነት የፈፀመው የቻይናው ኩባንያ ኢንቨስትመንቱን በ3.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

ኩባንያው በደብረብርሃን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሶስት ሼዶችን ተከራይቶ ስራ ለመጀመር የውል ስምምነት በመፈፀሙ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ኩባንያው ከስራ ዕድል ፈጠራ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከውጪ ምንዛሬ አኳያ የሚያስገኘው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሻንግቼንግ በጋርመንት ዘርፍ ስራውን ሲጀምር ከ2500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የተነገረ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ የስራ ዕድል ፈጠራው እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ምርቶቹን ሙሉ በሙሉ ለጃፓን ለአውሮፓ እና ለሰሜን አሜሪካ አገራት ገበያ እንደሚያቀርብ መገለጹን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here