ረቂቅ አዋጆች ላይ የሚጠሩ የውይይት መድረኮች ተሳታፊ አጥተዋል ተባለ

Views: 313
  • በቂ የሚባል ሰው ባይገኝም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በረቀቀው አዋጅ ላይ ውይይት ተደርጓል

የጸረ ሽብር አዋጁን ለማሻሻል የሕግ፣ ፍትኅና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 03ኅ 2012 የጠራው የሕዝብ ውይይት ላይ ጥሪ ከተደረገላቸው 13 ተቋማት ኹለቱ ብቻ በተገኙበት የተካሔደ ሲሆን በተደጋጋሚ የሕዝብ የውይይት መድረኮች ተሳታፊ በማጣት መሰረዛቸው ታውቋል።

ግንቦት 29/ 2011 ምክር ቤቱ ባካሔደው 42ኛ መደበኛ ስብሰባ የተመራው ረቂቅ አዋጁ ላይም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተገኙለት ተቋማት ሲሆኑ፣ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተለይም የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ሲኮነን የቆየው አዋጁ በማርቀቅ ሒደት ከተደረጉ ስብሰባዎች ከመጀመሪያው በስተቀር ሌሎቹ ዝቅተኛ የተሳታፊ ቁጥርም ያስተናገዱ ነበሩ። በተለይም ከሽብር አዋጁ በተጨማሪ በሌሎች አዋጆች ረቂቅ ዝግጅት ላይ የሚያተኩሩ መድረኮች ዝቅተኛ የተሳታፊ ቁጥር የሚታይ እየሆነ መጥቷል።
በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመወያየት የሕግ፣ ፍትኅና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ያዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማነስ ምክንያት መሰረዙ ይታወሳል። በተመሳሳይም ለውይይቱ ከ15 ተቋማት በላይ በደብዳቤ መጋበዛቸውንና በሚዲያም መጠራታቸውን ያስታወሰው ቋሚ ኮሚቴው፣ በመድረኩ የተገኙት ተሳታፊዎች ብዛት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ለተፈጠረው መስተጓጎል የተገኙትን ተቋማት ይቅርታ በመጠየቅ ስብሰባው እንዲበተን አድርጓል።

ጥቅምት 25/ 2012 የቋሚ ኮሚቴው አዲስ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የተመደቡት ተመስገን ባይሳ (ዶ/ር) የተሻለ ሕግ እንዲወጣ “ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ያልተወያየበት ሕግ ነው’’ የሚባለውን አስተያየት ለማስቀረት ሲባል ስብሰባው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን በመግለፅ ስብሰባው እንዲበተን አድርገዋል።

የፍትኅና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ ሃዱሽ አዛናው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች እየተካሔዱ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ከሚመለከታቸው አካላት ውስጥ በቂ የሚባል ሰው ባይገኝም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በረቀቀው አዋጅ ላይ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ ቀደም አዋጁ ለምን እንዳስፈለገ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተብራራ ሲሆን ኢትዮጵያ በወቅቱ ለሽብር ተግባራት ሰለባ የመሆን እድል እንደነበራት እና በተባበሩት መንግሥታትም ወንጀሉን ለመከላከል የሚተላለፉ ውሳኔዎችን የማስፈፀም ኀላፊነቷን ለመወጣት ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል መሆኑ ተገለጿል።

በአዋጁ ላይ ሲቀርቡ ከነበሩ ትችቶች መካከልም ‹ዜጎችን ያላሳተፈ ነው› የሚል እንደነበረም ለቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ማብራሪያ ኖት ያስረዳል። እንዲሁም ዜጎችን ለማጥቃት በመሣሪያነት ያዋለ እና የዜጎችን መብት የገደበ መሆኑ ስለታመነበት ያንን በሚያሻሽል መልኩ መቀረጹንም ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጌዲዮን አስረድተዋል።

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ተዋቅሮ የሕጉን ቅድመ ማርቀቅ ያካሔደው የሕግና የፍትኅ አማካሪ ጉባኤ፣ የተለያዩ ጥናቶችን አከናውኖ ሕጉን መከለሱንም ጌዲዮን አስረድተዋል።

ረቂቁ ይዟቸው ከመጡ ለውጦች መካከልም ማንኛውም ድርጅት ሽብርተኛ በሚል ለመጥራት የሚቻለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድው ብቻ እንዲሆን መደንገጉ እንደሆነ ተግልጿል። የሽብር ድርጊትን ከሽብር ወንጀል ጋር በሚታይ መስመር ረቂቁ የለየ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም እንደ ሽብር ወንጀል የሚወሰዱት ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማደም እና መደገፍ የሽብር ወንጀልን ለመፈጸም የሚደረጉ ተግባራት በሚል መለየታቸውም ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com