በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታና የመንግስትን አቋም አንዳንድ ዓለም አቀፍ አካላት መረዳትና መቀበል እንደተሳናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ።
ቃል አቀባዩ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታና የመንግስትን አቋም አንዳንድ ዓለም አቀፍ አካላት መረዳትና መቀበል እንደተሳናቸው ገልፀዋል።
የህወሓት ቡድን ህጻናትን በጦር ግንባር የማሰለፉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ደንታ የሌለው መሆኑን ማሳያ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ቡድኑ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፎች በአግባቡ እነዳይደርሱ በማስተጓጎል የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።
አምባሳደር ዲና አክለውም መንግስት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ህወሓት ግን ውሳኔ አለማክበሩን አንስተው፥ ይህ ድርጊቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲረዳና ቡድኑ እርቃኑን እንዲቀር ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ከሁለተኛው የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫም ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን አስረድተተዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት በታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከሙሌቱ ጋር ተያይዞም በሶስትዮሽ ድርድሩ መሰረት ለሁሉም ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች ደብዳቤ እንዲደርስ መደረጉን የገለፁት ቃል አቀባዩ መንግስት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ አሁንም ጠንካራ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን የገለፁት ቃል አቀባዩ ጉዳዩን በደቡብ አፍሪካ ካለው የአገሪቱ ኤምባሲ ጋር በመሆን እየተከታተልን ነው ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውና በህክምና ላይ ያሉ ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።



