ክልሎች የተጣመሩበት “የሕልውና ዘመቻ” ውጤት ያመጣ ይሆን?

0
1163

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በፌደራል መንግሥት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል ከኹለት ዓመት ኩርፊያና የቃላት ጦርነት በኋላ ጥቅምት 24/2013 ወደ ጦርነት መቀየሩን ተከትሎ፣ ለስምንት ወራት በትግራይ ሲደረግ የነበረው ፍልሚያ ከ15 ቀናት እረፍት በኋላ ዳግም አገርሽቷል።

በሕወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል ለስምንት ወራት የዘለቀው “የሕግ ማስከበር እርምጃ” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምንት እንዲደረግ የፌደራል መንግሥቱን ጠየቀ መባሉን ተከትሎ፣ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከሰኔ 21/2013 ጀምሮ በፌደራል መንግሥት ታውጆ ነበር።

የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁን ተከትሎ በትግራይ ክልል ተሰማርቶ የነበረው መከላከያ አካባቢውን ለቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው። በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተኩስ አቁም በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት ሊቀበለው ባለመቻሉ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል አጎራባች ድንበሮች ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

መከላከያ ትግራይን ለቆ በመውጣቱ ሕወሓት እራሱን ለማደራጀት እድል እንዳገኘ የፖለቲካና ወታደራዊ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሽብርተኝንት የተፈረጀው ሕወሓት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የክልሎች ልዩ ሀይል ተጣምረው ወደ ሰሜን አቅንተዋል።
ሕወሓት እራሱን ለማደራጀት እድል ማግኘቱ እና ክልሎች የተጣመሩበት “የህልውና ዘመቻ” የተደራጀና የአካበቢውን መልክዐ ምድር ካለመረዳት ጋር በተገናኘ ዳግም ያገረሸው ጦርንነት ወደ ተራዘመ ጦርነት ሊመራ እንደሚችል ባለሙያዎች ጠቁመዋል። የአዲስ ማለዳ መርሻ ጥሩነህ ጉዳዩን የአዲስ ማለዳ ዘ ሐተታ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል፣ በፌደራል መንግሥትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል ጥቅምት 24/2013 የተጀመረው የኃይል ፍልሚያ፣ በአጭር ጊዜ ይቋጫል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጅ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ከቃላት ጦርነት ወደ ጠብመንጃ የተቀየረው ፍልሚያ በተጠበቀው ልክ በአጭር ጊዜ እልባት ማግኘት አልቻልም።

ከማዕከላዊ መንግሥት ግንኙነቱን አቋርጦ በራሱ ፈቃድ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሕወሓት፣ ጥቅምት 24/2013 በሰሜን ዕዝ መካላከያ ሠራዊት ላይ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት የተጀመረው የተኩስ ልውውጥ ለስምንት ወራት ከዘለቀ ብኋላ አዲስና ያልተጠበቀ ውሳኔ በፌደራል መንግሥቱ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

በሕወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል ለስምንት ወራት የዘለቀው “የሕግ ማስከበር እርምጃ” ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተናጠል የተኩስ አቁም እንዲደረግ የፌደራል መንግሥቱን መጠየቁን ተከትሎ፣ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከሰኔ 21/2013 ጀምሮ በፌደራል መንግሥት ታውጆ ነበር።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፣ ትግራይን በጊዜያዊነት እያስተዳደረ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በትግራይ ክልል በተለያዩ አከባቢውች ተሰማርቶ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

ክልሉን ያስተዳደር የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደርና መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት እራሱን እንደ አዲስ በማደራጀት ለዳግም ጦርነት እራሱን እያዘጋጀ እንደነበር በተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች ሲዘገብ ሰንብቷል።
በትግራይ ክልል የነበረው መካላከያ ሠራዊት መውጣቱን ተከትሎ፣ ለትግራይ ችግር እልባት የሚያስገኝ አዲስ መንገድ ይከፈት ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር የሳምንት ትውስታ ነው። ይሁን እንጅ የተናጠል ተኩስ አቁም ከታወጀ በ15 ቀን ልዩነት በሽብርተኛነት የተፈረጀው ሕወሓት እራሱን በማደራጀት አዋሳኝ በሆነው በአማራ ክልል ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ክልል መንግሥት ሐምሌ 6/2013 ባወጣው መገለጫ አሳወቀ።

የአማራ ክልል መንግሥት መግለጫ ሕወሓት “የኢትዮጵያ ፌዲራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሰረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል” በማለት ተፈጸመ ያለውን ጥቃት ግልጾት ነበር።

“የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መሆኑን ነው። ስለሆነም ትግላችን ለሕዝባችን ሕልውናና ለአገር ሉዓላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲል ክልሉ በመግለጫው ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት “ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት በኹሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ አረመኔና ጨካኝ ቡድን መሆኑ እንዲታወቅና ኹሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከሕልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና ከዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ኹሉን አቀፍ ትግል የሕልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሕይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል” ብሎም ነበር።

የአማራ ክልል በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በሕወሓት የተፈጸመበትን ጥቃት በመግለጽ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ፣ የክልል መንግሥታት ልዩ ኃይላቸውን ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለማሰማራት መወሰናቸው የሚታወስ ነው። የአማራ ክልል መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የኦሮሚያ ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የጋምቤላ፣ የሱማሌ፣ የቤኒሻንጉል፣ የሐረሪና የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይላቸውን ሕወሓትን ለመዋጋት አሰማርተዋል።

የየክልሎቹ ልዩ ኃይል ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እያቀና ባለበት እና በትግራይና በአማራ ክልል አጎራባች አከባቢዎች “የሕልውና ዘመቻ” ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት፣ ሕወሓት በአፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎችም ጥቃት መፈጸሙ ተሰማ።
የአፋር ክልል መንግሥት ሐምሌ 10/2013 ባወጣው መግለጫ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በአፋር ሕዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን ማሳወቁ የሚታወስ ነው። ክልሉ በመግለጫው ሕወሓት አድማሱን ወደ አፋር ክልል በማስፋት የአፋር አርብቶ አደር ሕዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን ገልጿል።

የትግራይ ችግር ውልደት
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በሕወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ ክስተት ነበር። ሕወሓት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን መምጣት ከጅምሩ የተቀበለዉ ቢመስልም፣ የኋላኋላ ግን እያፈገፈገ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በፈጠሩት አዲስ የመነቃቃት ወኔ፣ መላዉ አገሪቷን እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ አዲስ መንገድ በሚያስተዋዉቁበት ጊዜ መቀሌ ላይ ጥሩ የሚባል አቀባበል አግኝተዉ ነበር። ይሁን እንጅ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አስተዳደር የሚያደርጋቸዉ የተቋማትና የአመራር ለዉጥ በሕወሓት በኩል ቅሬታን የፈጠረ ሂደት ነበር።

በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል የተፈጠረዉ የልዩነት ጎራ ከመነሻዉ ጀምሮ ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥር እየሰፋ መጣ። በኹለቱ ኃይሎች መካከል የታየዉ የልዮነት ጎራ ጉልቶ እንዲታይ የሚደርጉ ሁነቶችም ተከሰቱ።
የሕወሓት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በልዩነት እየተጓተቱ የመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ ያደረጉ ዋና ዋና ክስተቶችን ስናስታዉስ፣ ትግራይ ዉስጥ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ማዕከል እንዲንቀሳቀስ የፌደራል መንግስቱ ፍላጓት ቢኖርም ከሕወሓት በኩል ጦሩ ከትግራይ እንዳይወጣ ክልከላ ተደርጎ ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ከመቀሌ አንዳያልፍ ሲታገድ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

የልዩነት ጎራዉ እያደገ በመጣበት ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የኢትዮጽያን ፖለቲካ በቀዳሚነት የሚዘዉሩትን ጅርጅቶች አክስሞ ወደ አንድ ለማምጣት ውጥን በያዘበት ጊዜ ሕወሓት ውሕደቱን አልተቀበለም ነበር። ኢህአዴግን ከመሰረቱት እና የአድራጊ ፈጣሪ ሚናን ከፊት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሲዘውር የቆየው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) ብልጽግና የተባለውን ውህድ ፓርቲ ሳይቀላቀል ቀረ። ከውሕድ ፓርቲነት እራሱን ያገለለው ሕወሓት ተቃዋሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ። ይህ ምናልባትም በውሕድ ፓርቲው ብልጽግና እና በተቃዋሚው ሕወሓት መካካል ትልቅ ልዩነት የፈጠረ ክስተት እንደሆነ ይታመናል።

የኢሕአዴግ ክስመትና የብልጽግና ውልደት ሕወሓትን ከቀደሙት ጊዜያት በላይ ወደ መቀሌ እንዲከትም እና የተናጠል ሐሳብ እንዲያራምድ እንዳደረገው የሚታወስ ነው። ሕዳር 11/2012 ከሕወሓት ውጪ በተደረገ የያኔው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክር ቤቱ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፣ ሕዳር 21 ውሕደቱን የተቀበሉት ፓርቲዎች ተፈራርመው ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ። ሕዳር 24 ፓርቲው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ አቅርቦ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ 15/2012 ለብልጽግና ፓርቲ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የሕወሓትና የፌደራል መንግሥቱ የልዩነት ጎራ ከነበረበት ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ይሄውም የዓለምን እጆች ያሸማቀቀው ኮቪድ-19 ሲሆን፣ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስትኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ ነበር። ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጠየቁን ተከትሎ ነበር ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው።

የሕገ-መንግሥት ትርጉምን እና ምርጫ መራዘምን በወቅቱ አምርሮ የተቃወመው ሕወሓት፣ የራሱን ክልላዊ የተናጠል አካሄድ መከተል ጀምሮ ነበር። ይሄውም ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ኮቪድ-19 እያለም በመደበኛ ጊዜው አካሂዳለሁ በማለት የክልሉን ምርጫ አስፈጻሚ አዋቅሮ ምርጫ አካሄደ።

ሕወሓት በፌደራሉ መንግስት ሕገ-ወጥ ነው የተባለውን ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 በይፋ በማካሄድ ማሽነፉን አበሰረ። ማሽነፉን ተከትሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልል መንግሥት ሆኖ እንደሚቆይ በይፋ አወጀ። ከመስከረም 25/2012 በኋላም የፌደራል መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና እንደሌለው በመግለጽ፣ ለፌደራል መንግሥት ተገዢ እንደማይሆን አስታወቀ።

በዚህ መካከል የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ሕገ-ወጥ የተባለውን ምርጫ በማካሄዱ ሕገ-ወጥ ቡድን እንደሆነ በማወጅ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን በጀት በወረዳዎችና በክፍለ ከተሞች ደረጃ እንደሚያሰራጭ አስታወቀ።
የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ለክልሉ መዋቅር እንደማይሰጥ ከወሰነበት ቀን ጀምሮ፣ ሕወሓት የፌደራል መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት አንዳወጀ እንቆጥረዋለን በማለት ከውይይት ይልቅ ወደ ጦርነት የሚመሩ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ ነበር።

ሕወሓት ጳጉሜ 4/2012 ባካሄደው ክልላዊ ምርጫ አሸነፍኩ ማለቱን ተከትሎ፣ የወቅቱ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ሰኞ ጥቅምት 23/2013 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ለተፈጠረው ልዩነት የመጨረሻ አማራጭ እንደ ሕዝብ መዋጋት መሆኑን በይፋ ተናግረው ነበር።

ይህ በሆነ በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2013 ሌሊት በትግራይ ክልል መቀመጫ፣ መቀሌ ላይ ያልታሰበ እና መላ ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ ድርጊት ተፈጽሞ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 25/2013 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው አረዱ።
በማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተሰማው ዜና “ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል” የሚል ነበር። ሕወሓት ያልተፈለገ ጦርነት መጀመሩን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ መከላከያ በአካባቢው ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ ትዕዛዝ መሰጠቱን ገልጸው ነበር። በቃላት ጦርነት የገነነው የኹለቱ ኃይሎች ልዩነት ከጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ ወደኃይል ተቀይሯል።

ብልጭ ብሎ የጠፋው አዲስ ተስፋ
የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ ለትግራይ ችግር አዲስ የተስፋ መንገድ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት እንደነበር የሚታወስ ነው። የተኩስ አቁም አዋጁ ከአገር እስከ ውጭ አድናቆት ያገኘ ውሳኔ ነበር። በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫናዎች መበርታታቸውም የሚታወስ ነው።

የተናጠል ተኩስ አቁሙ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለማርገብ የተወሰነ ፋታ የሰጠ ነበር። ይሁን እንጅ በፌደራል መንግሥት በኩል የተወሰነው የተኩስ አቁም ስምምንት በሕወሓት በኩል ምንም ፍላጎት አልታየበትም። በዚህም በ15 ቀን ልዩነት ውስጥ ሕወሓት ለትግራይ ክልል አጎራባች በሆኑት በአማራና በአፋር ክልል ድንበሮች ላይ ጦርነት ከፍቷል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁምና የመከላከያ ከትግራይ መውጣት ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ብዙዎች ይገልጻሉ። በደርግ ዘመነ መንግሥት ከሕወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት የደርግ ሰራዊት ሆነው፣ ከተራ ተዋጊነት ከስከ ጦር መሪነት የተሳተፉት ሻለቃ ጌነትነት ገ/እግዚአብሄር የመከላከያ ሠራዊት ትግራይ ለቆ መውጣቱ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ተገቢ ውሳኔ እንደነበር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ ተገቢ መሆኑን የሚገልጹት ሻለቃ ጌትነት፣ መከላከያ ሠራዊት በወቅቱ የተጠቀመው ስልት ወታደራዊ ማፈግፈግ እንደሆነ ጠቁመዋል። መካለከያ ያደረገው ማፈግፈግ(አከባቢውን መልቀቅ) ከጀርባ ከሚደርስብት ጉዳት አንጻር ነው ብለውታል። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት ደርግ ከህወሓት ጋር በተዋጋበት ጊዜ በትግራይ ክልል የጦር መሪ ሆነው የገጠማቸውን በማስታወስ ነው።

ሻለቃ ጌትነት በወቅቱ የገጠማቸውን እንደሚስታውሱት ከሆነ፣ ደርግ ከሕወሓት ጋር በትግራይ ክልል በተዋጋበት ጊዜ ከጀርባው የሚወጋው ከሕዝብ ውስጥ የሚወጣ ኃይል እንደነበረ ነው። በዚህም የደርግ ሠራዊት ቦታውን ለቆ ለማፈግፍግ ይገደድ እንደነበር አስታውሰዋል። ሻለቃው አክለውም በትግራይ ያለውን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከህወሓት በላይ የሚያውቀው የለም ይላሉ። በመሆኑም በትግራይ ምድር ሕወሓትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት መከላከያ አስቸጋሪ ሆኖበት እንደከረመ ያምናሉ።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ዳምጠው ተሰማ(ረ/ፕ) በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በትግራይ ክልል የተደረገው የተናጠል ተኩስ አቁም በሳይንሱ መሰረት ከታየ ተኩስ ይቆማል እንጅ ሠራዊት አካባቢውን ለቆ ይወጣል ማለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ መከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው በኹለት ምክንያች እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ። የመጀመሪያው ምክንያት በክልሉ የተከሰተው የሰብዓዊ ቀውስ መሻሻል እንዲያሳይ ሲሆን፣ ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ የዓለም ዐቀፍ ተጽኖ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ መከላከያውን እንዲያስወጣ ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት የዓለም ዐቀፉ ተጽኖ መሆኑን የሚገልጹት ዳምጠው፣ የመከላከያ ሠራዊት በተደረገው የተኩስ አቁም አዋጅ ትግራይን ለቆ መውጣቱ ለህወሓት ዳግም መደራጀት አድል ፈጥሯል ይላሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕወሓት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ባስተላለፉት መግለጫ “ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፣ ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል። ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የዕርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ስንል በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል። ሰላም የተወሰነ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ ዕድል ነው” ብለዋል።

አክለውም “ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም” በማለት የተናጠል ተኩስ አቁሙ ውጤት እንደላመጣ ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ የተናጠል ተኩስ አቁሙ ለትግራይ ችግር መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም መሆን አለመቻሉን የሚገልጽ ነው።

የተናጠል ተኩስ አቁም ውጤታማ አለመሆኑን ተክትሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ውጥረቱ እንደ አዲስ ነግሷል። በዚህም ከክልሎች ልዩ ኃይል እስከ ሚሊሻ ወደ “ሕልውና ዘመቻ” እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
የትግራይ ክልል ጉዳይ የተራዘመ ጦርነት ወደ መሆን ያመራ ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች የስምንት ወሩን ጦርነት እንደማሳያ በማንሳት ሲገልጹ ነበር። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሻለቃ ጌትንትም ይህንኑ ሐሳብ ይደግፋሉ። በትግራይ የተካሄደው የስምንት ወር ጦርነት መቋረጡ ተገቢ ቢሆንም አሁን ዳግመኛ የተጀመረው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሚቋጭ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

የተራዘመ ጦርነት ምን ያስከትላል?
የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁ ውጤት አለማምጣትን ተከትሎ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ሕወሓትን ለመፋለም የተሰማራው ከክልሎች የተውጣጣ ልዩ ኃይል ሕወሓትን በማጥቃት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት ኃይሉን እንዲያደራጅ ዕድል ማግኘቱ ለተራዘመ ጦርነት በር የሚከፍት መሆኑን ሻለቃ ጌትነት ይገልጻሉ። አክለውም በክልሉ ያለው የመልክዓ ምድር አቀማምጥ ለምሽግ ውጊያ አመች በመሆኑና ሕወሓት መውጫ መግቢያው ስለሚውቀው አሁን የተጀመረው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

የአጭር ጊዜ ውጊያ በገንዘብም ይሁን በሰው ኃይል ቆጣቢነት ውጤታማ ነው የሚሉት ሻለቃ ጌትነት፣ የተራዘመ ውጊያ በሰው ኃይልም ይሁን በገንዘብ አቅም ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዳምጠው በበኩላቸው፣ በፌደራል መንግሥት በኩል የተወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ዓለም ዐቀፍ ጫናውን ለማለዘብ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ተከትሎ መከላከያ ክልሉን ለቆ መውጣቱ፣ ሕወሓት እንዲደራጅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ዳግም የተጀመረውን “የሕልውና ዘመቻ” አጠናክሮ የተራዘመ ጦርነት እንዳይሆን በተጠናከረና በተደራጀ ስልት መመራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን የተጀመረው “የሕልውና ዘመቻ” የተራዘመ ጦርነት እንዳይሆን የመጀመሪያ ዙር ባሉት ባለፈው በስምንት ወር ከተደረገው ውጊያ የተገኙ ልምዶችን እንደ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል። በአሸባሪነት የተሰየመ ቡድን ሳይከስም ለረዥም ጊዜ የመቆየት ዕድል ካገኘ፣ የአሸባሪነት ስሙ በራሱ እየገነነ ስለሚመጣ ችግር ፈጣሪ ሆኖ የመቀጠል ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል።

አሁን የተጀመረው ውጊያ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ እንደማይሆን የጠቆሙት ሻለቃ ጌትነት በበኩላቸው፣ ከክልሎች የተውጣጣ ልዩ ኃይል መሆኑ በራሱ ውጤታማ ላይሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የሻለቃ ጌትንት ስጋት ከክልሎች በድንገት የተውጣጣ ልዩ ኃይል የውጊያ ስልት መሰረታዊ ሥልጠና በጋራ አለመውሰዱ፣ የቅንጅትና የመናበብ እክል ሊፈጠርበት እና በቋንቋ ያለመግባባትና የአካባቢውን መልክዓ ምድር አቀማመጥ ካለማወቅ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ብሎም በውጊያ ስምሪቱ የሰው ኃይል አቅም ቢኖረውም በአደረጃጀት የተቀናጀ ካልሆነ በአጭር ጊዜ ውጊያውን ማጠናቀቅ ላይችል ይችላል ብለዋል።

የተባባሰው ችግር መፍትሔ
ከኹለት ዓመት የቃላት ጦርንት በኋላ ወደ ኃይል የተቀየረው የትግራይ ክልል ጉዳይ እንዴት እልባት ያግኝ በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች ይቀርባሉ። ይሁን እንጅ የክልሉ ችግር እስካሁን እልባት አላገኘም። ይልቁንም እንደ አዲስ የጋለ ትኩሳት ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህም በትግራይ ክልል የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የባንክ፣ ሰብዓዊ አርዳታና ሌሎችም አገልገሎቶች ተገድበው ይገኛሉ። ለዚህም ምክንያቱ ችግሩ በአጭር ጊዜ እልባት ማግኘት አለመቻሉ ነው።
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዳምጠው(ረ/ፕ) የትግራይን ችግር እልባት ለመስጠት ኹለት መፍትሔዎችን አስቀምጠዋል። የመጀመሪያው አሁን በክልሎች ጥምረትና በመከላከያ ኃይል የተጀመረውን በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ሕወሓትን የማጥቃት እርምጃ በመሪዎቹ ላይ ያነጣጠረና የማያዳግም ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እንደሚሉት፣ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ አጃቢ አድረጎ ኢትዮጵያን ለማሸበር የሚንቀሳቀስ ሕጋዊነቱን ያጣ ቡድን መሆኑን በመገንዘብ ዓላማውን እንዳያሳካ ባለበት መገደብና የትግራይን ሕዝብ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን የሚከተልበት አዝማሚ ሊቀየር የሚችለው መሪዎቹን መቆጣጠርና ማጥፋት ሲቻል መሆኑን ጠቁመዋል። የሕወሓት መሪዎችን መቆጣጠር ከተቻለ ሕዝቡን በሂደት ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ እንደሚቻልም አመላክተዋል።

በኹለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት መፍትሔ ፖለቲካዊ መፍትሔ ነው። በዚህም በሽብርተኝነት ተፈርጆ ሕጋዊነቱን ያጣውን ሕወሓትን በወታደራዊ ኃይል መቆጣጠርና የሽብር ተግባሩን መግታት ከተቻለ፣ ቀጣዩ ፖለቲዊ መፍትሔ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል። ፖለቲካ መፍትሔ የሚሆነው ብሔራዊ መግባባት የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ሌላ ያላየውን ከጀርባ ያለውን ቀልብ እንዲመለከት ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን አንጅ ይህ መሆን የሚችለው የሕወሓት መሪዎችን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ጌትነት በበኩላቸው፣ ለትግራይ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችለው፣ በኃይል የተጀመረውን ነገር በኃይል መጨረስ ወይም፣ ፖለቲካዊ መፍሔ መፈልግ እንደሆነ ጠቁመዋል። በትግራይ ክልል ያለውን መልክዓ ምድር አቀማመጥ በውጊያ መሪነት የሚውቁት ሻለቃ ጌትነት፣ ሕወሓት ከደርግ ጋር ያደርገው ከነበረው ውጊያ ጀምሮ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ አሁን በተጀመረው የኃይል አርምጃ ውጤት ማምጣት ላይቻል ይችላል ይላሉ።
በኃይል እርምጃ የሕወሓት መሪዎችን መያዝ ካልተቻለና በክልሉ የተሰማራው መከላከያ በሕዝብ ከጀርባ የሚወጋ ከሆነ፣ ለችግሩ ፖለቲካ መፍትሔ መፈለግ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here