ኮዬ ፈጬ ኹለት ፕሮጀክት ተብሎ በሚጠራው ኮንዶሚኒየም ከ50 ሺሕ በላይ የ13ኛ ዙር የቤት ዕድለኞች ቤታቸውን ሳይረከቡ ለኹለት ዓመት ከአምስት ወር በላይ በመቆየታቸው ላልተገባ ወለድ እየተዳረጉ መሆኑን ገለጹ።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሆነ ቤቶቹ መገንባት ከጀመሩት ከሰባት ዓመት በላይ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ቁልፍ አለመረከባቸውን ገልጸዋል።
ባለ ዕድለኞቹ እንደሚሉት፣ የቤቶቹ አብዛኛዎቹ ብሎኮች እስካሁን ተሠርተው ባላለቁበት ሁኔታ፣ የቤቶች ልማት ኤጄንሲ ከንግድ ባንክ ጋር ውል እንዲያስሩ በማድረግ ባልተረከቡት ቤት ያልተገባ ወለድ እየታሰበባቸው እንደሆነ እና ወለዱም ከ9% ወደ 12% ከፍ ማለቱ ችግር ውስጥ እንዳስገባቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው የቤት ባለ ዕድለኛ ላልተገባ ወለድ እየተዳረገ መሆኑን ያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ቤቱን አለመረከብ እንዳለ ሆኖ፣ ያላቸውን ገንዘብ ለባንክ እየከፈሉ መሆኑን ይገልጻሉ።
በተጨማሪም ለቀጣይ ዓመት ልጆቻቸውን የትኛው አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ለመወሰን መቸገራቸውንም ጭምር ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
ኮንዶሚኒየሙን ተመዝግበው ከጠበቁት ረጅም ዓመት ይልቅ ከደረሳቸው በኋላ የጠበቁት ጊዜ ረጅም እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ ወለድ መክፈላቸው መሆኑን ያነሳሉ።
ሀብታሙ ታመነ ባለ3 መኝታ ቤት ከደረሳቸው ባለዕደለኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ ‹‹የቁልፍ መረከቢያ ውል ብንፈጽምም እስካሁን ድረስ ቁልፉ እጃችን አልገባም›› ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሙሉ የቤቱን ክፍያ አጠናቆ ለመክፈል የተሰጠው የ10 ዓመት ጊዜ ወደ 15 ዓመት ከፍ ማለቱ፣ እንዲሁም ወለዱ 12 በመቶ መሆኑ ኪሳራ ውስጥ እያስገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በብሎኮቹ ላይ የመሠረተ ልማቶች ማለትም እንደ መብራት፣ ውኃ እና ኤሌክትሪክ አለመኖር የሲሚኒቶ እጥረት፣ የሠራተኛ አለመገኘት፣ የመተላለፊያ መንገድ ችግር እንዲሁም በተለያዩ ቤቶች ላይ የካሬ ልዩነት መኖሩ፣ ወዘተ. ባለዕድለኞቹ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ናቸው።
ችግሮቹ እንዲፈቱ ለቤቶች ልማት የቢሮ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ዕድለኞቹ ጥያቄ ያቀርቡ ሲሆን፣ ኃላፊዎቹም ቤቶቹን በኹለት ወር ውስጥ አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ገልጸውላቸው ነበር።
ነገር ግን በተባለው ቀን ቤቱ ሳያልቅ በድጋሚ በአዲስ አበባ ከንቲባ ደረጃ የተዋቀረው ቡድን የ40ቀን ዕቅድ ይዞ እስከ ግንቦት 15/2013 ቤቱ የሚያልቅ መሆኑን ቢጠቅስላቸውም እስካሁን ድረስ አለመረከባቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የወለድ መጠኑ ወደ12% ከፍ ማለቱ ቤቱን ሳያገኙ በከፍተኛ ደረጃ ወለድ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ገልጸው። ይሁን እንጂ ባልተረከቡት ቤት የሚከፍሉትን ወለድ የቤቶች ልማት ራሱ መሸፈን ይገባዋል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ጥላሁን ያነጋገረች ሲሆን፣ ችግሮቹን ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የባለ ዕድለኞቹ ጥያቄ ተገቢ እና መጠየቅ ያለበት መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊው፣ ነገሮች ተስተካክለው ቤታቸውን እስኪያገኙ መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ ተረድተው በትዕግስት መጠበቅ ይገባቸዋል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት የመሰረተ ልማት ችግሮቹ ላይ እየተሠራ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
ጥላሁን አያይዘውም ባለ ዕድለኞቹን በትክክል በዚህ ቀን ወደ ቤታቸው ይገባሉ ተብሎ የተወሰነላቸው ቀን አለመኖሩን ጠቁመዋል።
የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ2014 በጀት ዓመት ውስጥ በ20/80 እና በ40/60 ግንባታ ላይ የሚገኙ 139 ሺሕ ቤቶችን ለማጠናቀቅ፣ እንዲሁም በ2012 በጀት ዓመት የተጀመሩ 4 ሺሕ 287 ቤቶች ግንባታን ለማከናወን ማቀዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም 94 ሺሕ 163 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ለማስጀመር አስተዳደሩ በዕቅድ መያዙን የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013



