በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰጥ ሕክምና ከ10 እጥፍ በላይ ዋጋው ጨመረ

በሆስፒታሎች ላይ የተደረገው የሕክምና ዋጋ ጭማሪ ለታካሚዎች ትልቅ ስጋት መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ገለጸዋል

በመንግስት ሆስፒታሎች ላይ ተደርጎ የማይታወቅ እና የታካሚዎችን የገቢ ምንጭ ታሳቢ ያላደረገ ከ10 እጥፍ በላይ የተደረገው የመታከሚያ ክፍያ ጭማሪ፣ ለታካሚዎች ሕይወት ስጋት ሊሆን እንደሚችል በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ሱራፌል አየለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ካርድ ማውጫ 5 ብር ነበር ፣ አሁን 60 ብር ሆኗል ያሉት ባለሙያው፣ ተኝቶ ለመታከም ይጠየቅ የነበረው የአልጋ ክፍያ በቀን ከ10 ብር ወደ 180 ብር አድጓል። የላብራቶሪ እና ሌሎች ወጪዎችም በተመሳሳይ ጨምረዋል ብለዋል።
ሰው ቢታመምም እንደምንም ወረፋ ጠብቆ በሚያገኘው የመንግሥት ቤት ሕክምና ላይ በዚህ የኑሮ ውድነት የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበት፣ ሕይወትን ለማዳን ስጋት ይሆናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

አሁን አብዛኛው ታካሚ በዋጋ ጭማሪው ምክንያት እየተቸገረና ሕክምና አቋርጦ ለመውጣት እየተገደደ ነው ያሉት ባለሙያው፣ አስፈላጊ መድኃኒቶችን ለመግዛት እና ምርመራዎችን ለማድረግ ከባድ ሆኗል ነው ያሉት።
አያይዘውም ሆስፒታሎች ይህን የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራትና ፍጥነቱ ከቀድሞው በተለየ ይጨምራል ወይ የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ያዕቆብ ሰማሀኝ በበኩላቸው፣ በሕክምና አገልግሎቱ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ በፌዴራል ደረጃ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የሕክምና አገልግሎት ጥራት እንዲጨምር ለማድረግ ታስቦ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የዋጋ ጭማሪ የተደረገው ተጠሪነታቸው ለፌዴራል በሆኑ ሀያ አራቱም ሆስፒታሎች መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በክልሎችም በተለያዩ ጊዜያት የዋጋ ማስተካከያ መደረጉን አስታውሰዋል።
በፌዴራል ስር ያሉ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበት የዋጋ መጠን በ1954 ዓ.ም. ገደማ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በተቀመጠው ግምት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በሕክምና አገልግሎት ጥራቱ ላይ የበዙ ቅሬታዎች እንደሚመጡ ያስነሱት አቶ ያዕቆብ ይህንንም ለማሻሻል የጤና ተቋማት ገንዘብ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት አንጻር የሚከፈለው ክፍያ አነስተኛ ነው ያሉት ያዕቆብ፣ መንግሥት ለመድኃኒት የሚወጣውን ወጪ 99 በመቶውን ሲሸፍን፣ ተጠቃሚው ግለሰብ አንድ በመቶውን ብቻ እየከፈለ አገልግሎት ያገኝ እንደነበረም አብራርተዋል።
ይህ የዋጋ ማስተካከያው ለሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ ለማበጀት በቂ ጥናት ተደርጎበት በጤና ሚኒስቴር የተደነገገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የተደረገው ጭማሪ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር አሁንም የሚያንስ ነው ብለዋል።

ምንም እንኳ የዋጋ ጭማሪው ተጠቃሚው ላይ በጊዜያዊነት ተጽእኖ ቢያሳርፍም የተሸለ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ነጻ አገልግሎት የሚሰጥባቸው የሕጻናትና የእናቶች ሕክምና፣ የወሊድ አገልግሎት፣ ኤች አይ ቪ ምርመራ፣ ቲቢ እና የተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ነጻ መሰጠታቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አክለውም የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ምክንያት ሕበረተሰቡ የጤና መድሕን አገልግሎትን በመጠቀም ከሚያወጣው ወጪ ለመታደግ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ኹሉንም ሰው የጤና መድሕን ተጠቃሚ በማድረግ ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው ሲሉ አስረድተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here