“ለህወሓት ቡድን ምንም ትዕግስት የለንም፣ ኢትዮጵያን መንካት አይችሉም። የኢትዮጵያ ወጣቶች እያሉ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጫፍ እስከ ጫፍ በተነሳሰበት ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያን ሊያፈራርሱ አይችሉም” ሲሉ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክትር ቀነአ ያደታ አስታወቁ።
ከአዲስ አበባ ከተማ ተውጣጥተው መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ለወሰኑ ወጣቶች በመስቀል አደባባይ ታላቅ ህዝባዊ የሽኝት መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በዚህ የሽኝት መርሃግብር ላይም ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነአ ያደታ ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ በቆየችው አገራቸው ጉዳይ ላይ በፍፁም እንደማይደራደሩ አስታውቀዋል።
የህወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖትና በብሔር በመከፋፈል የእርስ በእርስ ግጭት ሲፈጥር ቆይቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዜጎችን በማሰቃየት ለዘመናት የሰብአዊ መብት ጥስት መፈጸሙንም አስታውሰዋል።
ህወሓት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየችው አገር እንድትዋረድ እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን አይፈቅዱም!” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች እያሉ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጫፍ እስከ ጫፍ በተነሳሰበት በዚህ ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያን ሊያፈራርሱ አይችሉም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
“”ጥያቄያችን፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ነው። ነገር ግን በእርሷ ሉአላዊነትና ህልውና ላይ የመጣን አንታገስም ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ሊዳፈር አይችልም” ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ባለሃብቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ያለ ምንም ዓይነት ልዩነት ለመከላከያ ሠራዊቱ ላደረጉት ድጋፍ የመከላከያ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡



