በባህርዳር ከተማ የሚኖሩ የቀድሞ ምልስ ሰራዊት አባላት የተደረገውን የክተት ዘመቻ ለመቀላቀል አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡
ከዚህ በፊት የሀገርን ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ቆይተው እና ግዳጃቸውን አጠናቀው በመመለስበ ባህርዳር በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ የቀድሞ የመከላከያና ልዩ ኃይል አባላት በክልላችን ብሎም በሀገራችን የተጋረጠውን ውስጣዊና ውጫዊ ወረራ ለመከላከል በክልሉ መንግስት የተደረገውን የክተት ዘመቻ በደስታ ተቀብለው መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት በትግራይ ክልል አጎራባች የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በትህነግ የግፍ አገዛዝ ውስጥ በመቆየታቸውና በኖሩበት ክልል እንደባይተዋር ተቆጥረው ቦታቸውን ፣ልማታቸውንም ሆነ ሀብታቸውን ለዘመናት ተነጥቀው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በተደረገው ፍትህ የማስፈን ተግባር የተመለሰላቸውን የማንነት ጥያቄ ለመቀልበስ ህወሓት እየታተረ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ጀግናው የመከላከያም ሆነ የልዩ ኃይልና ሚሊሻ እያደረገ ያለው የሀገርን ክብር የማስጠበቅ ተጋድሎ በድል እንዲጠናቀቅ የሁላችንም አጋርነት አስፈላጊ በመሆኑ የክልሉ መንግስት የክተት ጥሪ ማስተላለፉን መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዛሬው ዕለትም የባህርዳር ከተማ ምልስ ሰራዊት አባሎቻችን ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላም ማስከበር ግንባር ለመሄድ በመወሰናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በድል እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን ገልፀውና የሀገር ክብር መገለጫ ሰንደቅዓላማ አስረክበው ሸኝተዋቸዋል፡፡






