የክተት ዐዋጅ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ

0
1217

በትግራይ ክልል በፌደራል መንግሥትና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ከቃላት ጦርንት ወደ ኃይል ጦርነት መቀየሩን ተከትሎ፣ ለስምንት ወራት የዘለቅ ፍልሚያ ከተደረገ ብኋላ የፌደራል ምንግሥት ሰኔ 21/2013 ጀምሮ የተናጠል ተኩስ አቁም ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መነሻነት መካላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ በመውጣቱ ሕወሓት እራሱን አደራጅቶ በአማራ እና በአፋር ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ጥቃት ፈጽሟል፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት ጥቃት መፈጸሙን እና የተደራጀ ጦርንት በክልሉ ላይ መክፈቱ ተከትሎ፣ የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው፡፡ የዐዋጁን አንድምታ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የታሪክና የወታደራዊ ባለሙዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝንት የተፈረጀው ሕወሓት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት የክተት አዋጅ ጥሪ አድርጓል። በትግራይ ክልል ጥቀምት 24/2013 በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ሕወሓት ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በማግስቱ የተጀመረው የሕወሓትና የፌደራል መንግሥት ፍልሚያ ከስንምንት ወራት ቆይታ በኋላ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ለ15 ቀን ያክል የተረጋጋ ቢመስልም ዳግመኛ አገርሽቷል።

የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው። የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣት ለሕወሓት የዝግጅት ጊዜ እንደፈጠረለት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሕወሓት ለ15 ቀን ዝግጅት ካደረገ በኋላ በአማራና አፋር ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ጥቃት መፈጸሙን የኹለቱ ክልሎችና የፌደራል መንግሥት ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ዐዋጅ ጥሪ ያስተላለፈው በሽብርተኝንት የተፈረጀውን የሕወሓትን ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፣ ጥቃቱን ለመመከት የተደራጀ ኃይል እንደሚስፈልግ በማመኑ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። የክተት ዐዋጅ ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር ሲሆኑ፣ በክተት ዐዋጅ ጥሪያቸው ላይ “በክልሉ ውስጥ ማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሳሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ይክተት” ብለዋል።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን በመግለጽ፣ ሕዝቡ ተደራጅቶ እንዲመክት ጥሪ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ በክተት አዋጅ ጥሪያቸው “ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው” ብለዋል።

ርዕሰ-መስተዳደሩ፣ ጥሪያቸው ላይ የተጀመረው ዕርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና፣ የክተት ጥሪው አማራንና ኢትዮጵያን የመታደግ ጥሪ መሆኑን ጠቁመዋል። ሕወሓት አገር የማፍረስ ዓላማ እንዳለው የገለጹት አገኘሁ፣ አገር የማፈረስ ዓላማ ያለውን ኃይል በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል ብለዋል።

የዐዋጅ ጥሪውን ተከትሎ ከክልሉና ከክልሉ ውጪ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እያቀኑ መሆኑን ከሰሞኑ እንቅስቃሴ መታዘብ ይቻላል። ከክልሉ ወደ ግንባር ከሚዘምተው ሕዝብ በተጨማሪ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ በፈቃዳቸው የክተት ጥሪውን የተቀበሉ ወጣቶች ወደ ጦር ግንባር እያመሩ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ሌላኛው የክተት ዐዋጅ ጥሪውን የሚያጠናክር መግለጫ የሰጡት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ “የአማራ ሕዝብ ኹሉም ፋኖ ነው፣ ኹሉም አርበኛ ነው፣ በዚህ ትግል የማይሳተፍ የአማራ ሕዝብ በፍጹም አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል። የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ሕወሓት የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

በአማራና በአፋር ክልል የሚያደርሰው ጥቃት ተጠናክሮ እንደቀጠለ የተነገረለት ሕወሓት፣ ጦርነት ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ ንጹሐንን እየገደለ፣ በየደረሰበት ንብረት እየዘረፈ እንደሆነ አብርሃም ጠቁመዋል። አብርሃም አክለውም ሕወሓት የአማራና የአፋርን ሕዝብ እያጎሳቆለ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በርዕሰ መስተዳደሩ የተጠራውን የክተት ጥሪ ተቀብለው የአማራ ወጣቶችና የዘመኑ አርበኞች ወደየ ማዕከሉ እየገቡ ነው። ወጣቶች በከፍተኛ ወኔ እየተነቃነቁ ነው። ወጣቶች ለሕልውና ዘመቻው ራሳቸውን እያዘጋጁ መሆኑን የጠቆሙት አብርሃም፣ ትግሉ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ሕወሓትን የማጥፋትና ኢትዮጵያን እንደ አገር የማስቀጠል ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የክተት ዐዋጅ ምንድን ነው?
የክተት ዐዋጅ በዋናነት በጦርነት ጊዜ ሕዝባዊ ሠራዊትን መጥሪያና መመልመያ እንዲሁም በፈቃደኝነት ወደ ጦር ሠራዊት ማዝመቻ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ክተት ማለት ለራስ መዋጋት መሆኑን የታሪክ ባለሙያ አበባው አያሌው ይገልጻሉ። ባለሙያው ክተትን ሲያብራሩ “ክተት ማለት ለመንግሥት ወይም ለማንም መዋገት ሳይሆን፣ ለራስ መዋጋት ነው” ብለውታል። የክተት ዐዋጅን ተከትሎ ለጦርነት የሚሰለፍ ማንኛውም ሰው የሚዋጋው የራሱን መብት ለማስከበርና ሊያጠፋው የመጣ ጠላቱን የሚከላከልበት የትግል ስልት ነው ብለውታል። የክተት ዐዋጅ ዘመቻ ስለራስ እና ስለ አገር ሕልውና መዋደቅ መሆኑን አበባው አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የክተት ዐዋጅ ሲባል፣ ወደ ጦር ግንባር የሚዘምተው አካል የራስን ትጥቅ እና ስንቅ በመጠቀም ጦር ግንባር መዝመት እንደሆነ አበባው ጠቁመዋል። በጥቅሉ ዐዋጁ ዘማቹ የሚዋጋው ለመንግሥት ብሎ ሳይሆን ለራሱ መሆኑንና መንግሥትን ሳይጠብቁ የራስን ትጥቅና ስንቅ ይዞ መዝመት መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ለዘማች ቤተሰብ የሚደረግ እንክብካቤና የዘማቹን ሥራ መሥራት አንዱ የክትት አዋጅ አካል እንደሆነ የሚጠቅሱት አበባው፣ በዚህ ወቅት የዘማችን ቤተሰብ መደገፍና ሥራዎችን መሸፈን ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። የክተት አዋጅ በጦር ግንባር ከመሰለፍ በተጨማሪ ከኋላ ደጀን ሆኖ በቂ የስንቅ ዝግጅት ማዘጋጀትና ማገዝ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ክትት ዐዋጅ ታሪክ
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በጦርነት ወቅት የክትት ጥሪ ዐዋጅ ማወጇን የታሪክ ባለሙያዎች ይገልጿሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ የክትት ዐዋጅ ታሪክ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች የታወጁ እንደሆኑ ያስታውሳሉ።

አዲስ ማለዳ ኢትዮጵያ ምን አይነት የክትት ዐዋጅ ታሪክ እንዳላት የታሪክ ተመራማሪና መምህር የሆኑትን አበባው አያሌውን ጠይቃለች። አበባው እንደሚሉት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በገጠሟት የውጭ ወራራዎች የክተት ዐዋጅ አውጃለች። የመጀመሪያ የክትት ዐዋጅ በኢትዮጵያ ታሪክ የታወጀው ቱርክ ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረገችው ጦርነት በ17ኛው መቶ ከፍለ ዘመን እንደሆነ አበባው አስታውሰዋል። በወቅቱ በታወጀው የክተት ዐዋጁ መሰረት “ክትት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ተብሎ ሕዝቡ መዝመቱን ጠቁመዋል።

አበባው በኹለተኛነት የሚያነሱት የክተት አዋጅ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማለትም በፄ ዮሐንስ ዘመን፣ ግብጽ ኢትዮጵያን ለመውረር በተነሳችብት ወቅት፣ አፄ ዮሐንስ የዘመኑን ጦር አስተባብረው የዘመቱበት የክተት ጥሪ እንደነበር ጠቁመዋል። በወቅቱ የነበረው የክተት ዐዋጅ ኹሉንም የአገሪቱን ከፍል ያካተተ ባይሆንም ቀላል የሚባል የክተት ዘመቻ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

ሌላኛው በኢትዮጵያ ታሪክ “ወርቃማው የክተት ዐዋጅ” ተብሎ የሚጠራው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣችበት ጊዜ በ1888 በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የታወጀው የክተት ዐዋጅ ነበር። በወቅቱ አፄ ምኒልክ አውጀውት የነበረው የክትት ዐዋጅ “ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፤ሃገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህም ብሞት ሞት የሁሉ ነውና ለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ ልዑል እግዚአብሄር አሳፍሮኝ አያውቅም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት ልዑል እግዚአብሄር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቸ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።

አሁን ግን በልዑል እግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። አሁንም ጉልበት ካለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅ፣ ለሚስትህና ለኃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፤ እግዝዕትነ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻየም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ” የሚል ነበር።
የአድዋ ክትት ከሌላው የተለየ የሚደርገው፣ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ተገዝተው ኢትዮጵያ በክትት ዐዋጁ ትልቅ የሚባል ጦር በማሸነፏና የኢትዮጵያ ኩራት መሆኑን እንደሆነ አበባው ገልጸዋል። አበባው አክለውም በአድዋ ዘማች ቤተሰብ የመንከባከብ፣ አዝመራ የመሰብሰብና የጸሎት ተግባራት ይከናወኑ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሌላኛው የክተት ዐዋጅ በሱማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በዚያድ ባሬ ዘመነ መንግሥት በተደረገው ጦርነት የታወጀ ሲሆን፣ በወቅቱ ደርግ ሱማሊያ ኢትዮጵያን ለመውጋት በተንቀሳቀሰችበት ጊዜ በአቀረበው የክትት ዐዋጅ መሰረት በአንድ ወር ውስጥ ትልቅ ጦር የተፈጠረበት እንደነበር አበባው አስታውሰዋል። በወቅቱ የነበረው ጦርነት በክተት ዐዋጁ መሰረት በተደራጀው ጦር ውጤታማ ትግል መደረጉን አስታውሰዋል።

የክትት ዐዋጅ ውጤታማነት
የክተት አዋጅ በኃይል የመጣ ጠላትን በኃይል ብዛት ለመመከት የሚረዳ የአርነት ስልት መሆኑን የዘርፉ ባለሙዎች ይገልጿሉ። ይሁን እንጅ ውጤታማ የሚሆነው በተደራጀ አመራር ሲመራና ቀልጣፋ የሚባል የሎጅስቲክስ አቅርቦት ሲኖር መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ ወታደራዊ ባለሙያ ጠቁመዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው ደርግ ከሕወሓት ጋር 17 ዓመት ባደረገው ጦርንት ከተራ ተዋጊነት እስከ ጦር መሪነት ሚና የነበራቸው ሲሆኑ፣ በደርግ ዘመን የነበረውን ወታደራዊ አደረጃጀት እና በአጭር ጊዜ ስልጠና ወደ ውጊያ ሲሰለፍ የነበረውን ጦር አደረጃጀት ሲያስታውሱ፣ በቅርቡ የታወጀው ክትት ዐዋጅ በአደረጃጀትና በአጭር ስልጠና የታገዘ እንደማይመስል ይናገራሉ። ደርግ ከሶማሊያ ጋርም ይሁን ከሕወሓት ጋር ያደረገው ጦርነት ቀላል የሚባል እንዳልነበር ያስታውሳሉ።

የታሪክ ባለሙያው አበባው በበኩላቸው፣ የክተት ዐዋጅን ተከትሎ ወደ ጦር ግንባር የሚዘምት ተዋጊ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ጥሩ የሚባል የስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት፣ ስልጠናና የተደራጀ አሰላለፍ ያስፈልጋል ይላሉ። የታሪክ ባለሙያው ይህን ያሉት ከዚህ ከቀም ከነበሩት የክትት ዐውጅ ጥሪዎች የታዘቡትን የታሪክ ውጤት በማስታወስ ነው። የተደራጀ ስልጠና እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አበባው፣ ደርግ ከሱማሊያ ጋር በተዋጋበት ጊዜ የነበረውን የአጭር ጊዜ ስልጠና በማንሳት ነው።

ድርግ በወቅቱ ወደ ጦር ግንባር የሚሰለፈውን ሕዝብ ወታደተራዊ ማሰልጠኛ ተቋም በማስገባት፣ የአጭር ጊዜ ውጤታማ ስልጠና ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም ደርግ በአንድ ወር ውስጥ ትልቅ የሚባል ጦር መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው በበኩላቸው፣ ጦርነት የተደራጀና የተቀላጠፈ አመራርና ስልጠና እንደሚያስፈልገው ይገልጻሉ። ባለሙያው በደርግና በሕወሓት የ17 ዓመት ጦርነት በትግራይ ክልል በጦር መሪነት ሲያገልግሉ የገጠማቸውን ሲያስታውሱ፣ መልክዓ-ምድሩ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው። በዚህም ደርግ በአንዳንድ አከባቢዎች አስቸጋሪ መልከዓ-ምድር አቀማመጥ ሲገጥመው ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ይገደድ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ የደርግ ወታደር የተደራጀና ጠንካራ የነበረ ሠራዊት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ባለሙያው በወቅቱ ደርግ የገጠመውን ወታደራዊ ፈተና ሲያስታውሱ አሁን ላይ የአማራ ክልል የክተት ዐዋጅን ተክትሎ ጦር ግንባር እየተሰለፈ ያለው ሕዝባዊ ሰራዊት በተቀናጀ አመራርና ስልጠና ካልታገዝ የዐዋጁ ውጤታማነት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ እንዳይሆን ወደ ጦር ግንባር የሚሰለፈው ሕዝባዊ ሠራዊትን የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የታሪክ ባለሙያው አበባው በበኩላቸው፣ ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በክተት አዋጅ የተሰባሰበ ሠራዊት የሚያደርገው ፍልሚያ በሎጅስቲክስ ማለትም በደረቅ ስንቅ መጠናቀር እንዳለበት ጠቁመዋል። እንዲሁም የተደራጀና ውጤታማ የሆነ ሕዝባዊ ሠራዊት ለመፍጠር የፖሊስ ማሰልጠኛዎች ሠራዊት ማሰልጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በየአከባቢው የሚገኙ የፖሊስ ማሰልጠኛዎች የሠራዊት ማሰልጠኛ ሆነው ወደ ጦር ግንባር የሚሰለፈው ሠራዊት በቂ ስልጠና ካላገኘ የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ላይገኝ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የክተት ዐዋጅ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ጦር ግንባር እየዘመተ ያለው ሕዝብ የሚፋለመው ጥላቱ ከሆነው ከሕወሓት ጋር እንጅ፣ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም የታሪክ ባለሙያው አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here