ከራያ ቆቦ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎች የመጠለያ ዕጥረት እንዳጋጠማቸው ገለጹ

0
749

የፌደራል መንግሥት የወሰደውን የተኩስ አቁም ስምምነት ምክንያት በማድረግ እንደገና ያንሰራራዉ ሕወሓት እያካሄደዉ ባለዉ የጥቃት ዘመቻ በአማራ ክልል ከራያ ቆቦ ተፈናቅለዉ በወልድያ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለመጠለያ ችግር ሰለባ መሆናቸዉን ተናገሩ።

የተፈናቀሉጽ ዜጎች ወደ ወልድያ ማቅናታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩ ሲሆን፣ አክለውም “ሰሞኑን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ተከትሎ የአጥቂዉ ቡደን የቆቦ ከተማን ባልጠበቅነዉ ቅጽበት በመቆጣጠሩ፣ ከሚሰነዘርብን ጥቃት ሕይወታችንን ለማዳን መቀየሪያ ልብስ እንኳን ሳንይዝ በብዛት በመዉጣታችን የቤት ኪራይ ከመወደዱም በተጨማሪ ባለመገኘቱ ምክንያት፣ ሕጻናትን ጨምሮ በባዶ ሜዳ ላይ እየተሰቃየን ነው” ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት፣ ቀድመው የወጡት የተወሰኑ ተፈናቃዮች በኪራይ ቤትና በወልዲያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጠለል ዕድል ቢያገኙም፣ ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች ግን በየመንገዱና በየበረንዳዉ በዝናብና በብርድ እየተንገላቱ እንደሆነ ነው።
ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ካካፈሉ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ የሆነው ዓላዛር አዳነ “ቤተሰቦቼ የት እንዳሉ አላውቅም፤ እኔ ግን የእነርሱንና የእኔን ጨምሮ ሰባት ህጻናት ይዤ ወልድያ ከተማ እገኛለሁ። አሁን የያዝኩትን ትንሽ ብር በመጨረሴና የቤት ኪራይ ባለማግኘቴ በዚህ አጥንትን በሚሰብር ብርድ ለጋ ህጻናትን ታቅፌ ውሎና አዳሬ በረንዳ ላይ ነዉ’’ ሲል ይደመጣል።

በወልድያ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ በቂ የሆነ የመጠለያ ፣ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ባለማግኘታችን የመከራ ገፈት ቀማሾች ሆነናል ነዉ ያሉት።
“ያለንበት ጊዜ የክረምት ወቅት በመሆኑ እንኳን ጨቅላ ሕጻናት፣ ለዘመናት ብዙ ግፍ ያሰተናገድዉ የእኛ የትልልቆቹ አካልም እየደረሰብን ያለዉን እንግልት መቋቋም አቀበት ሆኖበታል” ያሉት ዜጎች፣ ሠላምን የሚፈልግ በሠላም የመኖር ነጻነት አለውና ወደየ ሰፈራችን እንመለስ ዘንድ እንሻለን ሲሉ ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮቹ አያይዘዉም፣ የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እንዲደረግልን እንሻለን ያሉ ሲሆን፣ አሁን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ የመከላከያ ሠራዊቱንና የአማራ ልዩ ኃይል ተጠናክሮ በማን አለብኝነት ከቀያችን አፈናቅሎ ጥቃት እያደረሰብን ያለዉን የሕወሓት ቡድንን በማስታገስና ጸጥታን በማስፈን ወደየ ቤታችን ይመልሰን ዘንድ የመንግሥትን ትዕዛዝ በአፋጣኝ እንጠብቃለን ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የተፈናቃዮችን ቅሬታ ይዛ የተፈናቃዮችን ጊዜያዊ እንቅስቃሴ ለመከታተል ተቋቁሟል የተባለውን ኮሚቴ የሎጅስቲክስ አስተባባሪ ኤርሚያስ አለባቸውን ለማነጋገር ብትሞክርም ጉዳዩን ካዳመጡ ብኋላ ምላሽ ሳይስጡ ስልክ በመዝጋታቸው እና በተደጋጋሚ ሲደወልም ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሽ ማገኘት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here