ምርጫው ስለተዘረፈ የምርጫውን ውጤት በፍፁም አልቀበልም፡-ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

0
772

ምርጫው ስለተዘረፈ ፤ የምርጫውን ውጤት በፍፁም እንደማይቀበለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይህን ያለው የ2013 ምርጫን አጠቃላይ የጥናት/የምርመራ ውጤት አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ግምገማው በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች እና በ21 የምርጫ ክልሎች ላይ የተፈፀመን ሕገ ወጥነት የሚመለከት ሲሆን በፌዴራል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ላይ ተፈፀሙ ስለሚላቸው ጉዳዮች የዳሰሰ እንደሆነ ፓርቲው ገልጿል።

በግምገማ ውጤቱም ባልደራስ ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ስለዘረፉት የዚህን ምርጫ ውጤት በፍፁም እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

ገዥው ፓርቲ በዋና ፈፃሚነት፤ ምርጫ ቦርድ በተባባሪነት ምርጫውን ስለዘረፉት በፍርድ ቤት ከስሻለሁ ሲል የግምገማ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ አሳውቋል፡፡

ፓርቲው አከናወንኩት ባለው የቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በዕጩዎች፣ በፓርቲው በአባላትና በመራጮች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (ስድብ፣ ዛቻ እና እስር) እንደተከናወኑበት ከጥናቱ ውጤት ለመረዳት መቻሉን ገልጿል፡፡

በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምርመራ ግኝቱ አመልክቷል፡፡ ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር መሆኑን ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ብዛት ጋር የማይመጣጠኑ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ተረድተናል ብሏል ፓርቲው፡፡

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው ብዙዎቹ የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን እንደማያውቁ ለመረዳት ተችሏል ተብሏል፡፡

የዚህም ምክንያት የምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል ብቃትን ሳይሆን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ ስለሆነ እንደሆነ የጥናቱ ግኝት ያሳያል ሲል ፓርቲው ገልጿል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here