በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ማህበር ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰበሰበ

0
881

በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ማህበር ከዋሽንግተን የኢፌዴሪ ኤምባሲ ጋር በመተባባር ሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌትን አስመልክቶ ባካሄደው ‘ግድቡ የኔ ነው’ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለፀ።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን በድር ኢትዮጵያ ቢያስተባብረውም ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሂደቱ ውስጥ በመሳተፍ አብሮነታቸውንና አንድነታቸውን ያሳዩበት እንደሆነ ተገልጿል።

በትላንትናው ዕለት በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 100ሺ ዶላር ማሰባሰብ በመቻሉም ሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌትን አስመልክቶ በበድር ኢትዮጵያ እስካሁን የተሰበሰበውን የገንዘብ መጠን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊያደርሰው ችሏል።

በዋሽንግተን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክትም ዳያስፖራው ሲተባበር ምን ማድረግ እንደሚችል ማሳየቱን ገልጸው፣ ዳያስፖራው ከ60 ሚሊዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ብርሃንን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያዩ ምክንያት እየሆነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስም በበኩላቸው በድር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ማሰባሰብ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታና ልባዊ ምስጋናቸውን ለመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች አቅርበዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዳያስፖራውን ማስተባበር እስከተቻለ ድረስ ታላላቅ ግቦችን ጥሎ ማሳካት እንደሚቻል ክስተቱ ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎች የዳያስፖራ አደረጃጀቶችም ተመሳሳይ መርሃ ግብሮችን በመንደፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ሃብት ለማሰባሰብ እንዲነሳሱ የሚያደርግ ተግባር ነው ብለዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ‘ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ’ በሚል በዋሽንግተን በተገኙበት ወቅት ድርጅቱ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን አውስተዋል።

በመድረኩም የበድር ኢትዮጵያ አመራሮችና ደጋፊዎች ለሀገራቸውና ለለውጡ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን አስታውሰው፣ በበድር ኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተሰባሰበው ይህ የአንድ ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የዚያ ተግባራዊ ምላሽ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here