መነሻ ገጽዜናወቅታዊሰለሞን ባረጋ - አዲሱ ሻምፒዮን

ሰለሞን ባረጋ – አዲሱ ሻምፒዮን

ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር:: የሰውነት ማጎልመሻ መምህሩ ወደሜዳ ወሰዱት:: ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ሩጫ እንዲወዳደር፤ አላቅማማም:: መምህሩ ናቸውና ካሸነፈ ቢያንስ “ጎበዝ!” ይሉታል:: “ማርክ ለማግኘት ብዬ ተስማማሁ እንጂ ሩጫ ጉዳዬ አልነበረም:: እስከዚያ ጊዜ ድረስ የእኔ ምኞት እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር” ይላል ሰለሞን ያንን አጋጣሚ አስታውሶ:: መምህሩ ትንሹ ልጅ ሲሮጥ ተመለከቱት:: አንዳች የተለየ ተሰጥኦ እንደተመለከቱ እርግጠኛ ሆነዋል:: ይሄ አጋጣሚ የወደፊቱን የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሕይወት መስመር ጠቋሚ ሆነ::

የገበሬ ልጅ ነው። ተወልዶ ያደገውም በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ውስጥ በምትገኘው ጌታ ወረዳ ነው። ከእናቱ ሰውዳ ሽፋ እና አባቱ ባረጋ ሽፍታጋ በተጨማሪ በሦስት እህቶች እና አራት ወንድሞች ተከብቦ አድጓል:: ሰለሞን ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከመኖሪያው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በሚጠይቀው ቋንጤ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ድንቅ አትሌቶች ጋር የሚያመሳስለው የትምህርት ቤት ምልልስ ሕይወቱ ነው:: “ረፈድ አድርጌ ስወጣ በሰዓቴ ለመድረስ መሮጥ ነበረብኝ። ፈጣን እርምጃና ሩጫ እየቀላቀልኩ ከ30-45 ደቂቃ ይፈጅብኝ ነበር” ይላል፣ አሁን ወደ ታላቅነት እየተጓዘ የሚገኘው የ21 ዓመቱ ሰለሞን።

መምህሩ እንደቀልድ ከጏደኞቹ አወዳድረው የተመለከቱትን ልጅ አልተውትም:: የትምህርት ቤቶች ውድድር በመጣ ጊዜ ኹሉ እርሱ በቡድኑ መካተቱን ማረጋገጥ ዋነኛ ሥራቸው ሆነ:: ብዙም ሳይቆይ ከትምህርት ቤቱ አልፎ ወረዳውን እንዲወክል ዕምነት ተጣለበት:: በ2005 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ለሚካሄድ የስፖርት ውድድር ወረዳውን የሚወክሉ ስፖርተኞች ሲመለመሉ ሰለሞን ኹለተኛ ሰው ሆኖ ተመረጠ።

ይሁን እንጂ ሕልሙን የሚያጨልም ዜና ተነገረው። ወረዳውን ለመወከል የሚችሉ እና ኑሯቸውንም ውድድሩ በሚካሄድበት የወልቂጤ ከተማ ያደረጉ የጌታ አካባቢ ልጆች መኖራቸው ሲታወቅ የሰለሞን ዕድል ለእነሱ ተሰጠ። ምክንያት? የትራንስፖርትና የምግብ ወጪ ለመቀነስ:: “ሀዘኔ ከባድ ነበር። በተለይ ስፖርተኞቹ ምሳ ምናምን ተጋብዘው በመኪና ተጭነው ባንዲራ እያውለበለቡ ከወረዳችን በሕዝብ ሲሸኙ ሳይ እጅግ ስሜቴ ተጎዳ” ይላል ሰለሞን የልጅነት ልቡን የሰበረውን ያንን አጋጣሚ ሲተርክ:: “ግን ደግሞ እልህ ያዘኝ። በርትቼ ሰርቼ ለሚቀጥለው ዓመት ዕድሌን ልሞክር ወሰንኩ። ወረዳዬን ወክዬ ወልቂጤ ላይ ልወዳደር::”

ብዙም ሳይቆይ በዚያው ዓመት መጨረሻ ትንሹ ልጅ መልካም ዜና ሰማ:: በአካባቢው የአትሌቶች ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ሊቋቋም እንደሆነ ተነገረ:: ሰለሞን ተደሰተ:: በፕሮጀክቱ ተካተተ:: ሳይቆይ በፕሮጀክቶች ውድድር የመሳተፍ እድል ተፈጠረለት:: ይሄ ራሱን ለማሳየት ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ ያወቀው ሰለሞን በ1500ሜትር ተወዳድሮ ኹለተኛ ሲወጣ፣ በ3000ሜትር አሸነፈ። በውጤቱ መሰረት ጉራጌ ዞንን ወክሎ ወደ ሐዋሳ አመራ። ከወልቂጤው ውድድር ሲቀር የተሰበረ ልቡ ተነሳሳ:: በክልሉ ዋና ከተማም በተመሳሳይ ርቀቶች ተወዳድሮ አስደሳች ውጤት አገኘ። ሌሎች በሮች ተከፈቱለት:: በመቀጠል ለክልሎች የፕሮጀክቶች ውድድር ደቡብን ወክሎ ሻሸመኔ ተገኘ።

“ሻሸመኔ 1500ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ በባዶ እግሬ ሮጥኩ። ምክንያቱም እኔ በጫማ ሩጫ አልለመደኩም። እግሬ ቆሰለ። ዶክተሩ አይቶኝ ጫማ እንድጠቀም አበረታታኝ። አንገራገርኩ:: በጫማ ከሮጥኩ ግር ስለሚለኝ የምሸነፍ መሰለኝ:: ´የቡድኑ ዶክተር አበረታታኝ:: ግድ የለም ይህንን አድርገህ ሩጥና ካልተመቸህ ታወልቀዋለህ´ አለኝ። ሳላምንበት ተጫማሁት:: አልወደድኩትም ነበር:: ቀስ እያልኩ ለመድኩት። በጫማ ሮጬ በ 1500ሜትር አራተኛ ሆንኩ። በ3000ሜትር ኹለተኛ ደረጃን አገኘሁ። ከዚህ በኋላ የመጀመሪያ ክለቤን አገኘሁ። ለደቡብ ፖሊስ ፈረምኩ።”

የሰለሞን ዕድገት ይበልጥ ፈጠነ:: ደቡብ ፖሊስን ተቀላቅሎ ብዙ ሳይቆይ ለብሔራዊ ቡድን ተጠራ። በ2007 ዓ.ም. በአሰላ በተካሄደው የወጣቶች ሻምፒዮና በ5000ሜትር አሸነፈ። በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄድ ውድድር ለመሳተፍ ተዘጋጅ ተባለ:: ከተዘጋጀ በኋላ በቪዛ ችግር ጉዞው ሳይሳካለት ቀረ።

“በዚያ ጉዞ ብዙ ተሰቃይቻለሁ። ሳይሳካ ሲቀርም አልቅሻለሁ” ይላል ወጣቱ። ፈተናው አላበቃም:: ወዲያው ፖላንድ ውስጥ ለሚካሄድ ውድድር ለመሳተፍ እድል አግኝቶ የጉዞ ሒደቱን ሲጀምር ደግሞ ሌላ ችግር ገጠመው:: ለቪዛው የሚያስፈልጉት ሰነዶቹ ጠፉ። ከቀናት በኋላ ኹሉም ዶክመንቱ ተገኘ። ለካ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሔዱት የቡድን ጓዶኞቹ ቀላቅለው ወስደውበት ነበር። በአውሮፓዊቷ አገር በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና አሸነፈ። ይሄኔ ሰለሞን ለመጀመሪያ ጊዜ ማናጀር ኖረው። ደግሞ ወደ ጣሊያን ሔደ:: እዚያም በ5000ሜትር ድል አደረገ:: የተለያዩ የውጪ ጉዞዎች አድርጎ ሦስት አገር አቋራጭ ውድድሮችን አሸነፈ:: በኢትዮጵያ ሻምፒዮናም ሦስተኛ ወጣ። የሰለሞን የልጅ ልብ ሞቀች::

በዚህ መልኩ ፈጣን የሚባል እድገት ያመጣው ሰለሞን ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ የነበረው ጊዜ ይበልጥ ያማረ ሆነለት። ወደ ለንደን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጓዙ ከሳምንታት በፊት በናይሮቢ በተካሄደው ከ18 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና በ3000ሜትር አሸነፈ። በለንደን የ5000 ሜትር ፍጥጫ ድል ባይቀናውም ሙክታር ኢድሪስ ለአገሩ ወርቅ ባመጣበት ውድድር በአምስተኛ ደረጃ አጠናቅቋል። ከለንደን ተመልሶም በአዲስ አበባ በተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10ኪ.ሜ. አንደኛ ወጣ:: በዶሃ ኳታር በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አሸነፈ::

ሰለሞን ወደ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የመጣው በበርካታ ሻምፒዮናዎች እና የግል ውድድሮቹ ብቃቱን አስመስክሮ ነው:: በቅርበት የሚያውቁት እጅግ ትሁት እና የተረጋጋ መሆኑን ይናገራሉ:: በቶኪዮ ከብሔራዊ ቡድሩ የረጅም ርቀት አትሌቶች አሰልጣኞች አንዱ የሆኑት ሀጂ አዲሎ፣ ወጣቱ አትሌት ከችሎታው ሌላ እጅግ በዲስፕሊን የታነፀ እንደሆነ ይመሰክራሉ:: “ባህሪዊ የተለየና ምክር የሚያደምጥ አስተዋይ ልጅ ነው:: ይህም ከማውቃቸው ጥቂት ልዩ ወጣት አትሌቶች አንዱ ይደርገዋል” ይላሉ::

ታዛዥነቱ እና ትህትናው የስኬቱ እንቅፋት እንዳይሆን የሚፈሩለት ሰዎች ነበሩ:: በለንደን እና ዶሃ ኹለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ያስመዘገበው ውጤት ተዳክሞ ወደ ውድድር በመሄዱ የተፈጠረ እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም:: በተለይ በ2017 ወደ ለንደን ከመጏዙ ጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች አገርን ወክሎ በአፍሪካ በተካሄደ ውድድር ላይ እንዲገባ ሲነገረው እርሱም እሺ ብሎ ተሰልፏል:: “ለአገር ተሰለፍ ስባል አለመታዘዝ ትክክል አይደለም” ብሏል ሰለሞን በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳቡን በጊዜው ሲጠየቅ::

በቶኪዮው የ10,000 ሜትር ወርቅ ካሸነፈ በኋላ ድሉ ለእርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ከውጪ አገር ጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ፣ ከእርሱ ይልቅ ለአገሩ ኢትዮጵያ ይለውን ትርጉም ነግሯቸዋል:: “ረጅም ርቀት ሩጫ የእኛ ተደርጎ ይወሰዳል:: ሆኖም በተለይ በኦሊምፒክ በዚህ ርቀት ወርቅ ካሸነፍን ብዙ ጊዜ ሆነን:: ከቀነኒሳ (በቀለ) ድል በኋላ ከእጃችን ወጥቶ ቆይቷል:: እዚህ ቶኪዮ ማሸነፍ ደግሞ ሌላ ልዩ ነገር ነው:: እዚህ ከተማ ታሪክ አለን:: ከአበበ ቢቂላ ጋር አሸንፈናል:: አበበን የምናስታውስበት ሌላ ድል በማግኘታችን በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል::

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ስታዲየም ውድድሩን ካጠናቀቀ በኋላ አበበ የሚታወቅበተን የሰውነት ማፍታቻ እንቅስቅሴዎች በማድረግ የ1964ቱን የማራቶን ድል ሲያወሳ በአለም ዙሪያ ያሉ የአትሌቲክስ ወዳጆች ኹሉ በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ተመልክተውታል:: ከእነዚህ ተመልካቾች መካከል አንዱ በ1964ቱ ኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ቢሊ ሚልስ ነው:: ቢሊ ከውድድሩ ፍፃሜ በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ይሄንን ብሏል:: “ከእንቅልፌ ማልጄ ነቃሁ:: ኢትዮጵያ አሸነፈች!” ሰለሞንን ከኹሉ በፊት አይቶ በአትሌቲክስ የታላቅነት የሕይወት ምዕራፉን የከፈቱለት መምህርም ምናልባት ባሉበት ቦታ ሆነው በልባቸው ይህንን ብለዋል-“አሸነፍን!”


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች