የምስራቅና የምዕራቡ ዓለም አገራት ተፅዕኖ የሚያሳርፉባቸውን አገራት ለመሻማት የእጅ አዙር ጦርነት ከጀመሩ ግማሽ ምዕተ ዓመት ተቆጥሯል። ቀዝቃዛው ጦርነት በመባል የሚታወቀውን ይህን ፍልሚያቸውን እንደቀደሙት ኹለት የዓለም ጦርነቶች በቀጥታ ላለማድረግ ተማምለው ጭፍራ እየፈለጉ ያጋድላሉ። የኃያላኑ ሽኩቻ ሲያይል አቅመ ደካማ አገሮች ላይ ወላፈኑ የማይታይ ድብቅ ረመጥ ያስከትላል። አንዳንዴም ሲበርድ ደግሞ ቁር ያለው ቀዝቃዛ ማዕቀብ እያስጣለ አገራትን ውርጭ እያስመታ የኖረ አሁንም ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሒደት ነው።
1950ዎቹ መጨረሻ ገደማ፣ የፈረንሳዩ ቻርለስ ደጎል ከእንግዲህ በቀጥታ ቅኝ መግዛታችንን ለምን አናቆምም፣ ራሳቸውን ከፋፍለን አውሮፓ ሆነን ፍላጎታችንን እናሳካለን ብሎ በማሳመኑ፣ ምዕራባውያኑ ተስማምተው አገራቱን የለቀቁ መስለው የድብቅ ጭቆናውን የጀመሩበት ወቅት ነበር። የአንዳንድ አገራት መሪዎች አንታዘዝም ብለው ሲያስቸግሩዋቸው ሕዝባቸውን አነሳስተው አመጽ በማቀጣጠል አስወግደዋቸዋል።
ኬኔት ካውንዳ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ክዋሚ ንክሩማ፣ ፓትሪስ ሉሙምባንና፣ ቶማስ ሳንካራን የመሳሰሉትን በገዛ ዜጎቻቸው ሲያስገድሉና መፈንቅለ መንግሥት ሲያካሂዱባቸው ኖረዋል። እነጋዳፊንና ሳዳምን የመሳሰሉ ሊያሳምጹባቸው ያልቻሉዋቸውን ራሳቸው በተለያየ ሰበብ እየገቡ ከሩቅም ሆነው አውድመዋቸዋል። እነሙጋቤንና ፊደል ካስትሮን የመሳሰለ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን ለማስወገድ ደጋግመው ሞክረው አልሳካ ቢላቸው በኢኮኖሚ ከማሽመድመድ አልተቆጠቡም።
በድሃ አገሮች ላይ በተለይም በደቡብ አሜሪካና አፍሪካ አገራት ላይ ተፅዕኗቸው ገደብ እንዳይኖረው ለማድረግ በርካታ ግፎችን ፈጽመዋል። እንደበርሊኑ ጉባኤ ለመስማማት ስግብግብነታቸው ስላልፈቀደላቸውም፣ እርስ በርሳቸው መሻኮት የጀመሩት ገና ከመነሻው ኹሉንም ልጠቅልል ያለችውን ጀርመንን አሸንፈው እንዳበቁ ነበር። ዋና ከተማዋን ሳይቀር ለኹለት ከፍለው የዓለም አገራትን ሳይቀር ከጎን ለማሰለፍ በሚል ከመዳፋቸው ስር ለማድረግ ሲራወጡ ጦርም ሲያስዘምቱ 40 አመታትን ከቆዩ በኋላ፣ ከፋፍለው ሲገዙዋቸው የነበሩት በጋራ በማመጻቸው ቀዝቃዛው ጦርነት ቆመ ተብሎ ነበር። እውነታው ግን አሁንም ተዋንያንን እየቀየረ መቀጠሉን በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህ አይነት የኃያላኑ መሳሪያ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ዳግም አገርሽቶ ወደ አገራችን እንዳይገባ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።
ራሺያና አሜሪካ ጎራ አስለይተውን ከአቅማችን በላይ እያስታጠቁን ድሃ ያደረጉበት የደርግና የወያኔ ጦርነት ያበቃ ቢመስልም፣ አሁንም በረዶ ሰርቶ ከነበረበት አንስተው እሳት ላይ ሲጥዱት ይታያል። ሕወሓቶችን ለዚህ ያበቁት ምዕራባውያን፣ መዳከማቸውን ማየት አልዋጥ ብሏቸው ነፍሳቸውን ለማትረፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። በአንፃሩ አሜሪካ ሕወሓትን ለመደገፍ መወሰኗን ያዩ ራሺያና ቱርክን የመሳሰሉ ተቀናቃኞቿ፣ መንግሥትን እንደግፍ እያሉ ውጊያውን ዓለም ዐቀፍ ጦርነት ለማድረግ ቋምጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆኑ ሕወሓቶች ማንኛችሁንም አንፈልግም ቢሉ እንደ አይ ኤስ ጥምረት ፈጥረው በጋራ ኹለቱንም እንደሚያስወግዱ የብዙዎች ዕምነት ነው። ይህ አይነት ክስተት ሊፈጠር ይችላል ብሎ ለነሱ ታዛዥ ሆኖ ወንድም ለወንድም ከመጋደል፣ አንድ ሆነን በጋራ የመጣውን ብንቀበል እንደሚሻል የሚያምኑም በርካቶች ናቸው። አሸከር ሆኖ ከመኖር ድሃ ሆኖ ከነክብር መኖርን አባቶቻችን የኖሩበት ከመሆኑ በላይ፣ ተዋርዶ ቀስ በቀስ ከመሞት የጀግና ሞት እንደሚሻል ለማንም መንገር አያስፈልግም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕወሓቶች ጦርነቱ አድማሱ እንዲሰፋና አጋዦች እንዲገቡ በሚል አስመራን ማጥቃታቸውን ጨምሮ የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ ተግባር ላይ ተሳትፈው እንደነበር ግልጽ ነው። የኤርትራ ጦር ውጊያው ላይ መግባቱን ተከትሎ የጠበቁት ባለመሆኑ ጩኸታቸውን በቻሉት መንገድ ሲያሰሙ ነበር። መንግሥትም ድሮንን የመሳሰሉ የጦር ግብዓቶችን በውሰትም ይሁን በሌላ መንገድ ከተቀናቃኝ ወገኖች ማግኘቱን አንዳንዶች ቢደግፉትም የተወሰኑት ተቃውመውታል።
ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀው ጋር ተደራደሩ በሚል እነሱም ድጋፍ እንዳያደርጉና የሶሪያና የየመንን ቁርሾ እኛም ላይ ለማስፋፋት የጓጉ በርካቶች እንዳይሳካላቸው ጉዳዩ በጥንቃቄ መያዝ እንደሚያስፈልገው በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
ወንድም ከወንድሙ ሲጣላ ጎረቤቶች ጎራ ለይተው የሚያባብሱት ከሆነ የኹለቱንም መጥፋት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ለጸቡ ማስኬጃ ብለው በሚያደርጉት አስተዋፅኦ የሚጠቀሙ ከሆነም እንዲበርድ እንደማይፈልጉ ሊታወቅ ይገባል። ሲሆን ሲሆን፣ ጠላት ያደረጉን እርስ በርሳቸው እንዲጣሉ እያማረጡ ማቆየት እንጂ፣ አንዳችን ብናሸንፍ እንኳን ኹሉም ደስተኛ እንደማይሆኑ ግልጽ ነው። ይህ አይነት የተልዕኮ ጦርነት ብሶት እየፈጠረና ቂም እያስቋጠረ ስለሚዘልቅ ማብቂያ እንደማይኖረው አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።
“የሰው ወርቅ አያደምቅ” እንደሚባለው ሩቅ ባለ ጉልበተኛ ድጋፍ ተማምነን የቅርባችንን የምንጨቁንበት ጊዜ ማብቃቱን ልንረዳ ይገባል። ቴክኖሎጂ በመጠቀበትና መረጃ በፍጥነት በሚደርስበት በዚህ ዘመን አጭበርብሮ መግዛት እንደሚከብድም ሊታወቅ ግድ ይላል።
በሌላ በኩል፣ “ከምዕራባውያኑ ተጣልተን ምን ይውጠናል፤ ራሳችንን ችለን መኖር አንችልም፤ ወይ ከምስራቁ ዓለም ካልተጠጋን” እያሉ የሥነ-ልቦናውን ጦርነት ገና ሳይጀመር በዝረራ ተሸንፈው ሌላውም እጁን እንዲሰጥ የሚያደርጉ ከዚህ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ኹልጊዜ በጭቆናና በእርዳታ ተጠፍረን የሌላን ፍላጎት እያሟላን ከመኖር፣ አንዴ ቆርጦልን የሚከፈለውን ዋጋ ተጋግዘን በመክፈል ለልጆቻችን እዳንና የባርነት ቀንበርን ባናስረክብ መልካም ነው።
የአሜሪካ መንግሥት በእርዳታ ድርጅቱ መሪ ስም የሌላ አገር ወታደርን ለማዘዝ ሲቃጣው ከሰሞኑ ተመልክተናል። “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንደሚባለው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ስር የሰደደ ንቀት ያሳዩበት እንደሆነ፣ ብዙዎች በቀረበው ትዕዛዝ አዘል ሐሳብ ላይ ተመርኩዘው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አንዳንዶች ከምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ለመላቀቅ በምግብ ራሳችንን እስከምንችል አንጣላ የሚል አይነት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ወቅቱ አሜሪካና አጋሮቿ ምንም ቢደረግ ወዳጃቸውን ከማንገስ የማይመለሱበት መሆኑ ታውቆ ራሳችንንም ባንችል አቋማችንን ማወቅ አለባቸው የሚሉ በርካቶች ናቸው።
በአንድ አገር መንግሥት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ጋር ተደራደሩ፣ መሬትም ልቀቁለት የሚል ይዘት ያለው መልዕክታቸውን፣ እነሱ አሸባሪ ብለው የፈረጇቸውን ሲያጠፉ ትዝም እንዳላላቸው የአይ ኤስ የቅርብ ታሪክ ያሳየናል። ሳይመረጡም ሆነ ይሁንታ ሳይሰጣቸው ራሳቸውን የዓለም ፖሊስ አድርገው የሚመለከቱት እነዚህ ጉልበተኛ አገራት፣ ለቀጪም ቀጪ እንዳለው መገንዘብ የተሳናቸው ይመስላል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ነገስታት ከወራሪ ያስጥሉኛል ብለው የተፈራረሟቸው አገራትና አባል የሆኑባቸው ሊግ ኦፍ ኔሽንን የመሳሰሉ ተቋማት ክፉ ጊዜ በመጣ ወቅት አለኝታ በመሆን ፈንታ ይበልጥ የሚጎዳ ውሳኔ ማሳለፋቸው አይዘነጋም። ይህ አሁንም ያለ አስተሳሰብ ሳይወገድ፣ ከሐሳባቸው ይመለሳሉ ይለሳለሳሉ ተብሎ አንድም ነገር ማድረግ ኋላ ላይ ማሳዘኑ አይቀርም። የደገፉትንም ሆነ የተቃወሙትን ለመጉዳት ወደኋላ እንደማይሉ ከሻዕቢያ ታሪክም መረዳት ይቻላል። “ሚስትን ፈልጎ የመጣ ልጅ ቢጨመርለትም አይመለስም” እንደሚባለው ለማንም ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ብቻ አስበው እንደሚንቀሳቀሱ ኹሉም ሊረዳ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በሌላ በኩል፣ ከምናጣው የምዕራባውያኑ ጥቅም ይልቅ እርስ በርሳችን የምንፈጽመውን ዝርፊያና ውድመት ማቆም ብንችል የበለጠ እንደአገር ተጠቃሚ እንደምንሆን የሚናገሩ አሉ። “ፍቅር ካለ አንድ እንጀራ ለብዙ ይበቃል” አንደሚባለው፣ በጦርነት የሚወድመውን አስቀርተን ዝርፊያንና ቅንጦትን ትተን ብንኖር ራሳችንን በአጭር ጊዜ መቻል ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እንተርፋለን። የኃያላኑ አገራት ያልተገራ ጣልቃ ገብነት አገር ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከባድ ስለሚሆን፣ እንደአድዋው አሁንም ከዘመናዊ ባርነት ነጻ የወጣን ምሳሌ እንድንሆን ታሪክ ለመሥራት የተመቻቸልን ጊዜ ላይ መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013



