‹ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ› በመዘግየታቸው ቅሬታ የተነሳባቸውን መኪኖች ወደ አገር ቤት ማስገባቱን ገለጸ

0
1197

ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ በኦሮሚያ ክልል መኪና ለመግዛት ውል ገብተው የመጀመሪያ ዙር ክፍያ በተንቀሳቃሽ አካውንት ያስገቡ ደንበኞች መኪኖቹን አስገብቶ ለደንበኞቹ ሊያስተላለፍ መሆኑን ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል 500 ግለሰቦች ከኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ እና ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር በኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በኩል መኪና ለመግዛት የመጀመሪያ ከፍያ 300 ሺሕ ብር ቢከፍሉም፣ በገቡት ውል መሰረት መኪና እንዳልቀረበላቸው መኪና ገዥዎቹ ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ በመዘግየታቸው ቅሬታ የቀረበባቸው መኪኖችን አስገብቶ ለደንበኞች ለማስረከብ በሒደት ላይ መሆኑን ገልጾ ነበር። ድርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ማለትም 300 ሺሕ ብር በተንቀሳቃሽ አካውንት ላስገቡ ገዥዎች 45 መኪኖችን ለማስረከብ ሞጆ ደረቅ ወደብ ማስገባቱን የኤል አውቶ ኢንጅነሪን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቀለ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በኹለተኛ ዙር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች 138 መሆናቸውን የገለጹት የኤል አውቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ቀሪዎቹን ተሽከርካሪዎች ለማስገባት ማለቅ ያለባቸው ሒደቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተሽከርካሪ ለመግዛት የመጀመሪያ ዙር ቅድመ ክፍያ የፈጸሙ ደንበኞች በወቅቱ 300 ሺሕ ብር ገቢ ያደረጉት በኹለት አካውንት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። የመጀመሪያ አካውንት ዝግ አካውንት ሲሆን፣ ብሩ እስካሁን እንዳልተንቀሳቀሰ ተናግረዋል። ኹለተኛው አካውንት ተንቀሳቃሽ አካውንት ሲሆን፣ አሁን የገቡ መኪኖች ቅድመ ክፍያቸውን በተንቀሳቃሽ አካውንት ያስገቡ ደንበኞች ናቸው ተብሏል።

በኹለተኛው አካውንት ማለትም በዝግ አካውንት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ የከፈሉ ደንበኞች ብሩን ወደ ተንቀሳቃሽ አካውንት ካላስገቡ መኪኖቹን ማስገባት እንደማይቻል ተገልጿል። አቅራቢው ብሩን ማንቀሳቀስ ካልቻለ ተሽከርካሪዎቹን መግዛት እንደማይችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። አሁን ሞጆ ወደብ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች በተንቀሳቃሽ አካውንት ቅድመ ክፍያ የፈጸሙ ደንበኞች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የተገዙትም በራሳቸው ብር ነው ተብሏል።

ከኤል አውቶ መኪና ለመግዛት ተስማምተው የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ከፈጸሙ 500 ሰዎች መካከል፣ የመጀመሪያ ዙር ከፍያ በተንቀሳቀሳሽ አካውንት ያስገቡ ቀድመው ባስገቡት 300 ሺሕ ብር ላይ 250 ሺሕ ብር በተንቀሳቃሽ አካውንት በማስገባት መኪናቸውን በቅድም ተከተል እንደሚረከቡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

ተሽከርካሪ ለመግዛት ከኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ ጋር ውል የተፈራረሙ ደንበኞች 250 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ በተጨማሪ አስገብተው ተሽከርካሪዎችን እንዲረከቡ ድርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 5/2013 ከኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይ ቢሮ ጋር ባደረገው ውይይት ስምምነት ላይ መደረሱ ተመላክቷል።

ከኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ቅድመ ክፍያ 300 ሺሕ ብር የከፈሉ ደንበኞች፣ 250 ሺሕ ብር ጨምረው በድምሩ 550 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ እንዲከፍሉ ተወስኗል። ተጨማሪ ከፍያ እንዲከፍሉ የተወሰነው አቅራቢውና ገዥዎቹ ውል ሲዋዋሉ ተሸከርካሪዎቹ ከቀረጥ ነጻ ይገባሉ ተብሎ ቢሆንም፣ አሁን ተሸከርካሪዎቹ ቀረጥ ስለተከፈለባቸው ነው ተብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በክልሉ መኪና መግዛት የሚፈልጉና አቅም ያላቸውን ግለሰቦች በመለየት በኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ በኩል መኪና እንዲቀርብላቸው መስማማቱ ይታወቃል። በዚህም የካቲት 5/2013 መኪና መግዛት የሚፈልጉ ግለሰቦች እና ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ የገዥና ሻጭ ውል ተፈራርመው ነበር።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here