ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ህወሓት በከፈተው ጦርነት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግር ላይ እንደሚገኙ ቢናገሩም በመንግሥት በኩል በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ተናገሩ።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከሳምንት በፊት በቆቦ ከተማ በሰነዘረው ወረራ ምክንያት ከቆቦና አካባቢው ተፈናቅለው በወልዲያና መርሳ ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችን ጨምሮ የወልዲያና የመርሳ ኗሪዎች ወደ ደሴ ለመሰደድ ተገደዋል። አሁን ተፈናቅለው በሚኖሩበት በደሴና በኮምቦልቻ ከተማ የጸጥታ ችግር ባይገጥማቸውም ከተጋረጠባቸው የኑሮ ውድነት ግን ማምለጥ እንዳልቻሉ ነው ተፈናቃዮቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ከህወሓት ጥቃት ለማምለጥ ከአላማጣ፣ቆቦ፣ ወልዲያና መርሳ ወደ ደሴ የገቡ ተፈናቃች ብዛት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ በደሴ ከተማ የምግብና የአልጋ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው አዲስ ማለዳ ከተፈናቃዮች ማረጋገጥ የቻለችው።
ተፈናቃዮች እንደተናገሩት ከሆነ፣ በደሴ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ ማሕበረሰቦች ቢኖሩም፣ ይህን ዕድል ያላገኙ እና ለአልጋ ከ1400 ብር በላይ መክፍል ያልቻሉ ዜጎች ጎዳና ላይ ለመኖር ተገደዋል። “በደሴ ከተማ ንግድ ባንክ አካባቢ ጥበቃዎችን እንዲያስጠጉን ብንጠይቅም ጥበቃዎቹ ካደረባቸው ሥጋት አንጻር ሊያስተናግዱን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ውሎና አዳራችንን መንገድ ዳር ላይ ማድረግ ግድ ሆኖብናል” ሲሉ ነው የተናገሩት።
ሕፃናትን አዝለው የተፈናቀሉ እናቶች በበኩላቸው፣ ሕፃናቱ ብርዱን የመቋቋም አቅም እንዳላገኙና እነርሱን ለማጥባት የሚያስችል በቂ ምግብ እያገኙ አለመሆናቸውን ነው የተናገሩት። ተፈናቃዮቹ አያይዘውም የክረምት ወቅት መሆኑን ተከትሎ ያለ መጠለያ መኖር እንደከበዳቸውም ነው የገለጹት።
ተፈናቃዮቹ፣ “ምግብ ለመግዛትና ቤት ተከራይቶ ለመኖር ብር ያስፈልጋል፤ ንብረታችንን ሜዳ ላይ ትተን ነው የመጣነው። ፍልሰቱን ተከትሎ የተከሰተው የትራንስፖርት እጥረትና መወደድም የነበረንን ብር እንድንጨርስ ስላስገደደን በችግር ውስጥ እንገኛለን። ለጊዜው መንግሥት የቻለውን ዕርዳታ እንዲያደርግልን እንሻለን’’ ብለዋል።
አዲስ ማለዳ በአካል ካነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች መካከል ድንበሩ ዝናቤ የተባለው፣ ህወሓት በወልዲያ ከተማ ስታዲየምና ጎንደር በር ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ላይ ከባድ መሳሪያ በማስወንጨፉ ማሕበረሰቡ ወደ ደሴ ከተማ መፈናቀሉን ነው የገለጸው። ድንበሩ አያይዞም በወልዲያና በመርሳ ኣካባቢ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ የሞት አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉና ትራንስፖርት በመዘጋጋቱ ምክንያት ከከተማው ለመውጣት አስቸጋሪ ሁኔታ መኖሩን ነው ያስረዳው።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላኛው የአዲስ ማለዳ ምንጭ በአሸባሪነት ከተፈረጀው የህወሓት ቡድን ተልከው ወደ መርሳ ከተማ የመጡ ግለሰቦች መርዛማ መርፌ በመውጋት በሰዎች ሕይወት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሏል።
በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች “የመከላከያ ሠራዊቱ ጥቃቱን እየመከተልን አይደለም፤ ከቆቦ ጀምረን እየተገፋን እዚህ ደርሰናል። የነገ ዕጣ ፈንታችን ምንድን ነው? እኛ የምንፈልገው መንግሥት ለጊዜው የመጠለያና የምግብ ዕርዳታ እንዲያደርግልን እና ለፍጻሜው ደግሞ የአጥቂውን ኃይል በማስታገስ ወደየቤታችን እንዲመልሰን ነው” በማለት ተናገረዋል።
በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ከሳምንት በፊት የቆቦ ከተማን ተቆጣጥሮ በዜጎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ የራሱን የከተማ አስተዳደር ማቋቋሙና ከንቲባ መሾሙ ይታወሳል።
ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013


