አፍሪካን በባሕር ውስጥ በሚዘረጋ የፋይበር ኦፕቲክ ገመድ ከአውሮፓ ጋር የማገናኘት እቅድ ያለው 2አፍሪካ የተሰኘው ፕሮጀክት አራት ተጨማሪ ሀገራትን እንደሚያካትት ተገለፀ፡፡
በፕሮጀክቱ የተካተቱት አዲስ ሀገራት ሲሼልስ፣ ኮሞሮስ፣ አንጎላ እና የካናሪ ደሴቶች መሆናቸውን ቴክ ክረንች ዘግቧል፡፡
ይህ ሲጠናቀቅ የዓለማችን ረዥሙ የፋይበር ገመድ ዝርጋታ እንደሚሆን የሚጠበቀው 2አፍሪካ ፕሮጀክት ስራ ሲጀምር 180 ቴራ ባይት በሰከንድ የሚደርስ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
37 ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍነው ፕሮጀክት አፍሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ በ26 ሀገራት 35 መዳረሻዎች እንደሚኖሩት ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
2አፍሪካ በሚል ስያሜ በፌስቡክ እና በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ጥምረት ለአፍሪካ የኢንተርኔት ተደራሽነት የተሻለ አማራጭ ይሰጣል የተባለለት ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2020 ወርሃ ግንቦት ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡



