የኔ ዘመን ኤቨንትስ ያዘጋጀውና ገቢው ለተስፋ አዲስ የበጎ አድራጎት ድርጅት (ታፕኮ) የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መሰናዶ ሐሙስ ነሐሴ 20/2013 በአዳማ ከተማ ኦልያድ ሲኒማ ይካሄዳል ተብሏል።
የካንሰር ሕመምተኛ የሆኑ ይልቁንም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምናቸውን የሚከታተሉ፣ ደጋፊ ለሌላቸው ሕጻናትን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ በበጎ ፈቃደኝነት መሰናዶውን ያዘጋጀው የየኔ ዘመን ኤቨንትስ መሥራቾች መካከል የሆነችው ፉርማዬ ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች።
ቋሚ ድጋፍ ለሌላቸው ለእነዚህ ሕጻናት ገቢ ለማሰባሰብ በተዘጋጀው በዚህ መሰናዶ ላይ ኮሜድያን እሸቱ መለሰን ጨምሮ ከአእምሮ ውቅር (Mind Set) ጋር የተገናኙ ሐሳቦችን የሚያካፍሉና ሥልጠና የሚሰጡ ባለሞያዎች ልዩ ተጋባዥ ናቸው። በዚህ መሠረት ማንያዘዋል እሸቱ፣ ስነወርቅ ታዬ፣ ሜሮን አበበ፣ ነጻነት ዘነበ (ሳይካትሪስት) እንዲሁም ዳንኤል ወዳጆ ይገኛሉ፤ ሐሳቦችንም ያካፍላሉ።
በዝግጅቱ ላይ 650 ሰዎች እንዲታደሙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህ አጋጣሚ ድጋፍ ለማድረግና በመሰናዶው ላይ መታደም ለሚፈልጉ ትኬቱ ፒያሳ ሰባ ደረጃን ወጥተው እንደጨረሱ ጫፍ ላይ በሚገኘው የታፕኮ ቢሮ ይገኛል ተብሏል። ትኬቱን ሰዎች ከፈለጉ ባሉበት እናደርሳለን ያሉት አዘጋጆቹ በ0922470914 የስልክ ቁጥር ደውሉልንም ብለዋል።
በኹለት ወጣቶች የተመሠረተውና መቀመጫውን አዳማ ከተማ ያደረገው የኔ ዘመን ኤቨንትስ፣ ከዚህ ቀደም ለአረጋውያን ድጋፍ ለማድረግ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን መሰናዶ በአዳማ ከተማ ማዘጋጀቱን ፊርማዬ አስታውሳለች።
ተስፋ አዲስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ታፕኮ የካንሰር ሕሙማንና እድሜያቸው ከአንድ ወር ጀምሮ እስከ 16 ዓመት የሆኑ፣ ‹ኬሞቴራፒ› ሕክምና የሚወስዱ ሕጻናትን እንዲሁም አስታማሚ ወላጅና አሳዳጊዎቻቸውን የሚደግፍና በእንክብካቤ የሚይዝ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በ2005 የተመሠረተ ሲሆን፣ ከአራት የመንግሥት ሆስፒታሎች ማለትም ከጥቁር አንበሳ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ጎንደር እንዲሁም አይደር ሆስፒታል የሕጻናት ካንሰር ሕክምና ክፍሎች ጋር በጋራ የሚሠራ ነው።
ድርጅቱ በሳምንት አንድ ቀን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ ውስጥ የካንሰር ሕሙማን ሕጻናት ወላጆችን ለማጽናናት እና ለማበረታታት፣ እንዲሁም እርስ በእርስ ለመተጋገዝና ሐሳብ ለመለዋወጥ በሚያደርጉት መሰባሰብ ነበር የተጀመረው። በዚያ መንገድ እንቅስቃሴውን ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ከተመዘገበ በኋላ ለሕጻናቱ ወላጆች ማኅበራዊ እንዲሁም የሥነልቦና ድጋፍን ይሰጣል።
በተጓዳኝም ለታካሚና አስተማሚዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ባሻገር ታካሚዎች በቀላሉ መድኃኒት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የሚሠራ መሆኑን ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ ከድርጅቱ ሥራ አስኪጅና መሥራቾች መካከል ሳራ ኢብራሂም ጋር ባደረገችው ቆይታ ለመረዳት ችላለች። ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበት ሊድን የሚችል ሲሆን፣ ሕክምናው አምስት እና ስድስት ዓመታት የሚዘልቅ ክትትልን ይፈልጋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013


