ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ሰኔ 14/2013 ላይ ማከናዋኗ የኹላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ከዛ በላይ ግን በምርጫ ቦርድ እና በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ተያይዞ በመሔድ ፍትሕን ለማግኘት ሲሞክሩ የታየበት ምርጫ ሆኖ አልፏል፡፡ በቅድመ ምርጫም ሆነ በድሕረ ምረጫ ወቅት ፓርቲዎች ያላቸውን ቅሬታ በፍትሕ አደባባይ አቅርበው ፍትሕን ለማግኘት ፍርድ ቤትን አምነው መሔዳቸው ይሔ ምርጫ ካሳየን መልካም ተሞክሮዎች መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ ሆኖ መነሳት ያለበት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባካሄደችው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በቅድመም ሆነ በድህረ የምርጫ ወቅት አለመግባበት በፈጠሩ ጉዳዮች ላይ ምርጫውን በመራው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የምርጫው ዋና ተዋንያን በሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከውይይትና መግባባት አልፎ በፍርድ ቤት እስከመዳኘት የደረሱ የምርጫ ሒደቶች ተስተውለዋል፡፡ በቅድመ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድና በፓርቲዎች መካከል የነበሩ የፍርድ ቤት ዳኝነቶች አሁንም በድህረ ምርጫ ማግስት ቀጥለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰኔ ወር ያከናወነችው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን ተከትሎ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድሕረ ምርጫ ወቅቶች ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች 74 ክሶች ቀርበው ውሳኔ ማግኘታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት መዓዛ አሸናፊ ባለፈው ሳምንት ላይ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ከነዚህ በምርጫ ሒደቱ ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ወደ ፍረድ ቤት ከመጡ ጉዳዮች መካከል 21 በመጀመሪያ፣ 24 በከፍተኛ እና 29 በጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠቅላላ 74 ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ቀርበው ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ተብሏል፡፡ ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል 22 የወንጀል ሲሆኑ ቀሪ 52 ደግሞ የፍተሓ-ብሔር ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከቀረቡት ክሶች መካከል 57 በቅድመ ምርጫ፣ አራት በምርጫ ወቅት እና 13ቱ ደግሞ በድሕረ ምርጫ ወቅት ወደ ፍርድ ቤቱ የመጡ ጉዳዮች እንደነበሩም መነሳቱ ይታወሳል፡፡
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጀት ከሚያደርግበት ጊዜ ጀምሮ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ቦርዱ ያልተቀበላቸውን ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ አሽናፊ የሆኑበት ሒደት ነበር፡፡
በቅድመ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በነበረው ልዩነት ወደ ፍርድ ቤት ካመሩ ጉዳዮች መካከል፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ባልደራስ) ጉዳይ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ባልደራስ በፍርድ ቤት ዳኝነት እልባት እንዲያገኝ ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው ጉዳይ፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እነ እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ዕጩ ተወዳዳሪ አድርጎ ማቅረቡና ቦርዱ ዕጩነታቸውን አለመቀበሉን ተከለትሎ ነበር፡፡
ምርጫ ቦርድ እስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ የቦርድ አመራሮች በዕጩነት አልመዘግብም ያለው፣ በእስር ላይ ያለ ሰው በዕጩነት መቅረብ አይችልም በማለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም በፍርድ ቤት ለወራት የቆየ ክርክር ካደረገ በኋላ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
በምርጫ ቦርድ ተሸናፊነት የተጠናቀቀው የፍርድ ቤት ክርክር እነ እስክንድር ነጋ በዕጩነት ተመዝግበው በምርጫው ተወዳዳሪ መሆን ችለው ነበር፡፡ በቦርዱና በባልደራስ መካከል የነበረው የፍርድ ቤት ክርክርና ውሳኔ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
አሁን እየታየ ያለው ጉዳይን በአደባባይ ላይ ብቻ ተናግሮና ተድበስብሶ ከመቅረት የወጣ የሚመስለው ይህ አካሄድ፣ ይበልጥ በኹሉም በሚመለከተው ባለድርሻ አካል በኩል ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጥሩ ልምምድ ነው፡በሌላ በኩል፣ ወደ ፍርድ ቤት ደጃፍ ከደረሱ ጉዳዮች መሀል የሆነው በምርጫ ቦርድና በሐረሪ ክልል መካከል በቅድመ ምርጫ ወቅት ፍርድ ቤት ድረስ ሄደው የተሟገቱበት ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡
የሐረሪ ክልል እና ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ክርክር መጀመራቸውን ተከትሎ የክልሉ ምርጫ ሰኔ 14/2013 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሳይካተት መቅረቱ የሚታወስ ጉዳይ ነው፡፡ ቦርድ የሐረሪ ክልል ምርጫ ወደ ጳጉሜ 1/2013 እንዲዛወር የተወሰነው የፍርድ ቤት ክርክሩ ውሳኔ አለማግኘቱን ተከትሎ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ከቅድመ ምርጫ ቀጥሎ በነበረው ሒደት ማለትም በምርጫ ዕለት ለምርጫ ተብለው በተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩ የሚታወስ ነው፡፡ በጊዜያዊነት በተቋቋሙት የምርጫ ፍርድ ቤቶች በርካታ ምርጫ ነክ ጉዳዮች ውሳኔ ማግኘታቸውን ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ተከተሎ በምርጫው ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሒደት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ይዘው ለቦርዱ ያቀረቡ ቢኖሩም፣ በቦርዱ ጉዳያችን በበቂ አልታየም ያሉት ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ቦርዱን ሞግተዋል፤ በመሞገትም ላይ ናቸው፡፡ ይህ ስልጡን የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ገና የዲሞክራሲ ሥርዓትን በመፍጠር ሒደት ደረጃ በመዳሕ ላይ ላለቸው አገር ትልቅ ብርሀን ፈንጣቂ ተስፋ ነው፡፡
የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በተካሄደ በማግስቱ የገጠሟቸውን ችግሮች ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ተገቢ ውሳኔ የማያገኙ ከሆኑ ጉዳዮቹን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ ካስታወቁት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ቀዳሚው ነበር፡፡ ኢዜማ በተለይም በምርጫው ዕለት በርካታ ችግሮች እንደገጠሙት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የገጠሙትን ችግሮች ምርጫ ቦርድ እልባት እንዲሰጥለት በዝርዝር ጥያቄ ማቅረቡን ገልጾ ነበር፡፡
ኢዜማ በምርጫ ቦርድ እልባት የማያገኙ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት እወስዳለሁ ባለው መሰረት፣ አጋጥመውኛል ያላቸውን ችግሮች ይዞ ወደ ፍረድ ቤት ማቅናቱ ይታወሳል፡፡ ኢዜማ ሰኔ 14/2013 ምርጫ ከተካሄደባቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ በ28 ምርጫ ክልሎች ምርጫ እንዲደገም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባቱን ማስታወቁም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ኢዜማ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ያስገባው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የቀረቡለተን ቅሬታዎች እና ማስረጃዎች ሳይገመግም ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ፓርቲው ቦርዱ እልባት የማይሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ፍረድ ቤት እንደሚወስድ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ኤዜማ ቅሬታ አለኝ ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ማስረጃ አስደግፎ አቤቱታውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገባ መሆኑን በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ የኢዜማን ክሶች የተቀበለው ፍርድ ቤቱ ጉዳዮቹን እንደሚመለከት መግለጹን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ኢዜማ ለፍርድ ቤቱ ያስገባው አቤቱታ “ከበቂ በላይ ማስረጃ አቅርቤባቸዋለሁ ያላቸውን 28 የምርጫ ክልሎች የተመለከተ ይሁን እንጂ፣ ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ያቀረበባቸው አጠቃላይ የምርጫ ክልሎች ብዛት 68 መሆናቸውን ፓርቲው አስታውሷል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 መካሄዱን ተከትሎ ምርጫ በተካሄደ ሰሞን ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ቅሬታ፣ የሰው፣ የሰነድ፣ የቪድዮ እና የምስል ማስረጃዎችን ያካተተ እንደሆነም መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ፓርቲው ባቀረበው ቅሬታ በድምጽ አሰጣጥ ሒደት እና በምርጫ ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ተግባራት መፈጸማቸውን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ጠቅሷል፡፡ ኢዜማ በምርጫው ዕለት ተፈጽመዋል ያላቸው ጉድለቶች የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን፣ የምርጫ ዐዋጅን እና ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመሪያዎች በቀጥታ የሚጻረሩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ የፓርቲው አመራሮች ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ በኋላ ለሚዲያዎች በሰጧቸው ቃለ ምልልሶችና በተለያየ መድረኮች ባደረጉትን ንግግር ምርጫው በርካታ ጉድለቶች የታዩበት እንደነበር ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
ኢዜማ በወቅቱ እንዳስታወቀው ከሆነ ፍርድ ቤቱ በፓርቲው የቀረበለትን አቤቱታ የመረመረ ሲሆን፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኹለተኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ባሳለፍነው ሐምሌ 22/2013 ኢዜማ ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ መቀበሉን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቀረበበት ክስ ላይ ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ለሐምሌ 30/2013 ቀጠሮ መሰጠቱን ፓርቲው ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በዕለቱም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢዜማ ላቀረበው አቤቱታ ምላሽ አላቀረበም፡፡ በወቅቱ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ላለማቅረቡ እንደ ምክንያት ያነሳው ለአቤቱታው ምላሽ ለመስጠት የተሰጠው ጊዜ አጭር ነው የሚል ነበር፡፡
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል እስከ ፍርድ ቤት ዳኝነት የሚደርስ ሒደቶች መኖራቸው ዴሞክራሲያዊ ሙከራዎችን የሚያጎለብትና የቦርዱን አቅም የሚያጠናክር እንደሆነ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሜደቅሳ በምርጫው ሒደት ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ የፍርድቤት ክሶችና ክርክሮች የቦርዱን አቅም ለማጎልበትና በዴሞክራሲ የዳበረ ምርጫ ለመለማመድ ዕድል እንደሚፈጥሩ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
እንደነዚህ ያሉ ልምምዶች ክሱን ይዞ ወደፍርድ አደባባይ የሔደውንም ሆኖ ተከሶ የቀረበውንም አካል በማበርታት ረገድ የራሳቸው የሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከምንም በላይ ግን በሚከተላቸው ሕዝብ ላይ የፍረድ ቤት ተዓማኒ ሆኖ መሥራትን ማሳየት ምርጫን አሸንፎ ሥልጣንን ከመያዝ ባለፈ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት የተቋማት ግንባታ ሠፊ ፍላጎት አንጻር ትልቅ የሆነ ጡብ የማስቀመጥ ያህል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እንደነዚህ ያሉ ሒደቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ይታመናል፡፡
እንደነዚህ ያሉ ሒደቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ይታመናል።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013