በአዲስ አበባ ለአካለ መጠን ያልደረሰና ገና ሶስት አመት ከስድስት ወር የሆነውን ህጻን ልጅ በመጥለፍ የተከሰሰው ግለሰብ በጽኑ እስራት መቀጣቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ።
በ1996ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 589/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ ዳንኤል ተሾመ በፈጸመው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን በመጥለፍ ወንጀል ተከሶ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቧል፡፡
ተከሳሽ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን በሀይል አፍኖ ለመውሰድ በማሰብ ጥቅምት 07/2012 በግምት ከጥዋቱ 3፡00 ስዓት ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ እድሜው ሶስት አመት ከስድስት ወር የሆነ ህጻን አልፈርድ መሀመድ ‹‹ከረሜላ እገዛልሀለሁ›› ብሎ በማታለል መውሰዱ ተገልጿል።
ተከሳሹ ህፃኑን ጠልፎ ከወሰደ በኋላም የህጻኑ አባት የሆነውን አቶ መሀመድ አለሙን ስልክ በመደወል ‹‹ልጅህ እኔ ጋ ነው ልታገኘው ከፈለክ 7ሺህ (ሰባት ሺ )ብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስገባ›› በማለት በመደራደር ላይ እያለ በፖሊስ ክትትል ከላይ በተጠቀሰው ዕለት ከቀኑ 11፡00 ስዓት ላይ በመያዙ በፈጸመው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡
ፍ/ቤቱ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ 589/1 ስር በዐቃቤ ህግ በቀረበበት የሰው እና የሰነድ ማሰረጃዎች አማካኝነት ጥፋተኝነቱ በመረጋገጡ ጥፋተኛ ነው ብሎ ነሀሴ 14/2013ዓ.ም በዋለው ችሎት በአራት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ገልጿል፡፡



