የሸገር ዳቦን ከፋብሪካው ተረክበው ለሕብረተሰቡ በማከፋፋል ላይ የተሠማሩ ኢንተርፕራይዞች ዳቦውን ለሕብረተሰቡ በአግባቡ እያደረሱ አለመሆኑን ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩ የሸገር ዳቦ ተጠቃሚዎች አስታውቀዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደተናገሩት፣ ኢንተርፕራይዞቹ ከሚረከቡት ዳቦ ውስጥ ጥቂቱን ብቻ በማከፋፋል የተቀረውን ለነጋዴዎች እና ለራሳቸው ማከፋፈያውን ተጠግተው ለሚሠሩ የሻይና ምግብ መሸጫዎች በመስጠታቸው እነሱ እየተጠቀሙ ማኅበረሰቡ ጋር መድረስ የሚገባውን የዳቦ መጠን እያደረሱ አይደለም በማለት ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አክለውም፣ “የአንዱ ዳቦ መሸጫ ዋጋ 1 ብር ከ25 ሳንቲም ቢሆንም፣ በአቅራቢያ በሚሠሯቸው መሸጫዎች ያንኑ ዳቦ እስከ ሦስት ብር ከኃምሳ ድረስ ይሸጡታል” በማለት ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ዳቦውን ለማግኘት በጠዋት ወጥተው የሚሰለፉ አቅመ ደካሞች እና ነብሰ ጡሮች ላይ የኑሮ ጫናው እንዲበረታ እያደረጉ ነው፡፡
ከሸገር ዳቦ ጋር በተገናኘ የሚቀርበውን ስሞታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጉዳዩን እንደማያውቀው የተናገሩት የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል ሜላ፣ በእንደዚ አይነት ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩትን ለማጣራት እና አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚሠራም አክለው ገልጸዋል፡፡
የሸገር ዳቦን ለሕብረተሰቡ እንዲያሰራጩ ኢንተርፕራይዞቹን የሚያደራጀው የአዲስ አበባ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በበኩሉ፣ ድርሻው ማደራጀት እና ወደሥራ እንዲገቡ ማድረግ ብቻ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋሙ፣ “የሸገር ዳቦ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ” በሚል ጥናት ማስጠናቱን ገልጾ፣ በዚህም ጥናት ግኝት የሸገር ዳቦ ማከፋፈያ ተብለው የተሠሩ አውቶብሶች መጀመሪያ በነበሩበት ቁጥር ላይ እንደማይገኙ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም የሆነው የዳቦ አምራቹ አቀርበዋለሁ ባለው የዳቦ መጠን ልክ እያቀረበ ባለመሆኑ የተደራጁት ኢንተርፕራይዞች ሥራውን በማቆም እና የሥራ ዘርፍ በመቀየር ላይ በመሆናቸው እንደሆነ ታውቋል፡፡
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ወደሥራ ሲገባ አቀርበዋለሁ ያለውን 1.5 ሚሊዮን ዳቦ ባለማቅረቡ በሥራው ላይ ተደራጅተው የተሠማሩት ወጣቶች ሥራው ላይ በአግባቡ እንዳይሳተፉ ሁኗል ተብሏል፡፡
የዳቦ ማምረት ሒደቱ እንደተጀመረ ከ400 በላይ ያገለገሉ አውቶብሶችን ተጠቅሞ ዳቦውን ለማከፋፈል ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም፣ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት የማከፋፈያ አውቶብሶች ቁጥር መቀነሱ ተገልጿል፡፡
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በሰዓት 80 ሺሕ ዳቦ እንዲያመርት ታስቦ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ፈብሪካ ነው፡፡
ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ከማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ በሚፈጠረው የገበያ ትስስር ሒደት እሰከ 20 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ የታሰበ ነው፡፡ ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል በላይ፣ 116 ወረዳዎች ላይ ዳቦ በማከፋፈል ለማኀበረሰቡ በአቅራቢያው እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ ማቅረብ ያስችላል በሚል በ2012 ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ማለዳ ፋብሪካው የምርት መጠኑን ቀንሷል ስለመባሉም ሆነ ዕጥረት ስለመፈጠሩ ለማረጋገጥ ያደረገችው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ምክንያት አልተሳካላትም፡፡




