ፖለቲካ ፓርቲዎች ለኹለተኛው ዙር ምርጫ ወኪል እንዲያቀርቡ ቦርዱ ጠየቀ

0
849

መስከረም 20/2014 ለሚካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ የፓርቲ ወኪል ዕውቅና መታወቂያ ፍቃድ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ወኪላቸውን እንዲያቀርቡ ቦርዱ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ቦርዱን ባቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎች ፈቃድ ለመስጠት እና ለመከታተል የሚያስችለውን መመሪያ አርቅቆ ማጽደቁ ይታወሳል።
በዚህ መሠረት ለኹለተኛው ዙር ምርጫ የሚያከናውነውን የመራጮች ምዝገባ ሒደትን ለመታዘብ የፓርቲ ወኪል ማቅረብ የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከተሉትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ወኪሎችን እንዲያቀርቡ ጠይቋል። ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ/ች፣ ዕድሜ 21 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ/ች፣ የመምረጥ እና መመረጥ መብቱ/ቷ በሕግ ያልተገደበ፣ የታወቀ ብልሹ ሥነ-ምግባር የሌለበት/ባት፣ ማንበብ እና መፃፍ የሚችል/የምትችል እና በዕጩ ተወዳዳሪነት ያልተመዘገበ/ች።
አንድ ተወዳዳሪ ፓርቲ የፓርቲ ወኪሎችን ማቅረብ የሚችለው ዕጩ ባቀረበበት የምርጫ ክልል ብቻ ሲሆን፣ በአንድ ምርጫ ክልል እስከ ሰባት ተዘዋዋሪ እና ኹለት ተቀማጭ ወኪሎችን ማቅረብ ይችላል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here