የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው 28 የቁንድዶ ፈረሶች ዝርያ ውስጥ ሦስቱ መሞታቸው ተነገረ

0
1366

የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከሚገኙ 28 የቁንድዶ ፈረስ ዝርያዎች መካከል ሦስት ፈረሶች የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት መሞታቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ካሉ ስምንት የፈረስ ዝርያዎች መካከል የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት የቁንዱዶ የፈረስ ዝርያ አንዱ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥ በአካባቢው ባስከተለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ሦስት ፈረሶች ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ መሞታቸውን የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን የብዝኃ ሕይወት ባለሙያ ወርቃለኝ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከአዳስ አበባ ከተማ በ628 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በጃርሱና እና ጉርሱም ወረዳዎች መሀል በቁንዱዶ ተራራ ላይ 28 የቁንዱዶ የፈረስ ዝርያዎች እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ወርቃለኝ ገለጻ፣ የቁንድዶ ዝርያ ያላቸው ፈረሶች በማኅበረሰቡ በመወሰዳቸው እና በሚመለከተው አካል ጥበቃ ባለመደረጉ ምክንያት በ2007 ዘጠኝ ብቻ እንደነበሩ አንስተው፣ በመንግሥት በተደረገ ጥበቃ እና ክትትል አሁን ላይ 28 ደርሰው እንደነበር አመልክተዋል።
በቁንዱዶ ተራራ ላይ የሚገኙ ፈረሶችን ዝርያ ለማብዛት የውኃ፣ የምግብና የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መደረጉን አንስተዋል። በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ቅዝቃዜ በመኖሩ ይህም የሚወለዱ ግልገል ፈረሶችን ለማትረፍ ቤቶች መሠራታቸውን ፣ እንዲሁም አካባቢውን ከአውሬ የሚጠብቁ የጥበቃ ሠራተኞች መቀጠራቸውን ጠቅሰዋል።

የቁንዱዶ ፈረሶች ላይ የተጋረጠውን የዝርያ መጥፋት አደጋ ለማስቀረት የፈረሶቹን ዝርያ የማባዛት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በቁንዱዶ ፈረሶች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራ በስፋት እንደሚከናወን፣ እንዲሁም ፈረሶቹ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ለቱሪዝም የገቢ ምንጭ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሠራ እንደሆነም ባለሙያው ገልጸዋል።

የቁንዱዶ ፈረሶች ላይ የተጋረጠውን የመጥፋት አደጋ ለመቀልበስ እና ለመንከባከብ የሚያስችል የጋራ ሥምምነት ሠነድ የሐረማያ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይውት ኢንስትቲዩት፣ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ነሐሴ 21፣2013 መፈራረማቸውን በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስትቲዮት የእንስሳት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክተር ተስፉ ፈከንሳ(ዶ/ር) ገልጸዋል። ሥምምነቱ በቀጣይ ዐስር ዓመት የሚተገበር ሲሆን፣ በቁንዱዶ ፈረሶች ላይ የተጋረጠውን የዝርያ መጥፋትን ከመቅረፍ በተጨማሪ ፈረሶቹ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም የገቢ ምንጭ እንዲሆን ጭምር ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የአንድ ዝርያ ቁጥሩ ከ250 በታች ከሆነ እና የወንዱ ቁጥር ከአምስት በታች ከሆነ ዝርያው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን ያመላክታል ብለዋል። ከቁንዱዶ ፈረሶች መካከል 16 ወንድ እና 12 ሴቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የፈረሶቹን ቁጥር ለመጨመር ከወንድ ፈረሶች ይልቅ የሴቶቹን ቁጥር መጨመር እንደሚገባም አንስተዋል።

በቦታው የአከባቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራ ባልነበረበት ጊዜ ማኅበረሰቡ የጫካ ፈረሶቹን ወስዶ በማላመድ ለጭነት፣ ለጋሪና ለሌሎች የተለያዩ ዓላማዎች ይጠቀምባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል። ይህም የቁንዱዶ ፈረሶች ዝርያ ላይ የመጥፋት አደጋ ለመጋረጡ እንደ ዋነኛው ምክንያት ነው ብለዋል።

የቁንዱዶ ፈረሶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ሰዎች እንደሚሠፍሩ፣ የእርሻ ሥራ እንደሚከናወን፣ ብሎም የመሠረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት በአካባቢዉ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የምክክር ሥራ እንደተሠራ ተናግረዋል። ይህም ከዚህ ቀደም በማኅበረሰቡ የሚከናወነውን የቁንዱዶ ዝርያ ያላቸው ፈረሶችን ወስዶ በማላመድ ለግል ዓላማ የማዋል ድርጊት ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here