አንቲሳይኮቲክ እና አንቲዲፕሬሽን የአእምሮ ሕክምና መድኃኒቶች ዋጋ በዕጥፍ ጨመረ

ለአእምሮ ሕክምና የሚያገለግሉ አንቲሳይኮቲክ እና አንቲዲፕሬሽን የተባሉ ኹለት መድኃኒቶች ዋጋ በአዲስ አበባ በዕጥፍ መጨመሩን የመድኃኒቱ ተጠቃሚዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ለደኅንነታችዉ በመሥጋት ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት እና ለአዲስ ማለዳ መረጃውን የጠቆሙት የመድኃኒቱ ተጠቃሚ እንደተናገሩት፣ ለአእምሮ ሕክምና የሚውሉ እና በእንግሊዝኛው አጠራራቸው Antipsychotic እና Antidepression የሚባሉ መድኃኒቶች፣ 500 ብር ይሸጥ የነበረው አንዱ እስከ 1000 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩ ሥር እየሰደደ መሆኑን የተናገሩት የመድኃኒቶቹ ተጠቃሚዎች፣ በተለይም ከአእምሮ ሕክምና እና ሌሎች ተከታታይ ክትትል ከሚሹ መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ ያለው የዋጋ ጭማሪ ያልተገባ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም አንዳንድ መድኃኒት ቤቶች መድኃኒት የለም እስከማለትም ይደርሳሉ ነው ያሉት። በዚህም የመድኃኒቱ ተጠቃሚዎች የመግዛት አቅማቸው እየተዳከመ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ መድኃኒት ቤቶች ከዕጥፍ በላይ ከማስከፍላቸዉም በተጨማሪ፣ አንዳንዶቹ መድኃኒቶች የሉም በማለት ወደ ሌላ ቦታ ይጠቁማሉ። መድኃኒቶች አሉ የተባሉበት ቦታ ሲሄዱ ደግሞ ዋጋቸዉ በዕጥፍ ጨምሮ እንደሚያገኙት ነው የገለጹት። ሌላው በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳው የተለያዩ የግል መድኃኒት ቤት ባለቤቶች ይህንን ጉዳይ ከመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ጋር በማገናኘት፣ ችግሩ በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ከመንገር ባለፈ የመድኃኒት ዋጋ ስለመጨመሩ ያሉት ነገር አለመኖሩ ነው የተገለጸው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ከነማ መድኃኒት ቤቶች በመሄድ ያነጋገረቻቸው የከነማ መድኃኒት ቤት ሠራተኛ የሆኑት ግለሰብ እንደገለጹት፣ አሁን ያለው የመድኃኒቶች ዋጋ ከዚህ በፊት ከነበረው ጭማሪ እንዳለው ይገልጻሉ። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደንበኛ እንደሚያስተናግዱ እና ማንኛውንም መድኃኒት ዋጋው ተመጣጣኝ እና የደንበኞችን አቅምና የኢኮኖሚ ኹኔታ ያገናዘበ እንዲሆን ከኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር በትብብር እየሠራን ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ፈንድ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወል ሐሰን፣ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጋር እንደማይገናኝ እና የድርጅቱ ኃላፊነት መድኃኒቶችን ለመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና መድኃኒት ቤቶች ማከፋፈል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ኃላፊው አያይዘውም ድርጅቱ ማንኛውንም አይነት መድኃኒት ከ300 እስከ 400 ፐርሰንት ባነሰ ዋጋ እንደሚያከፋፍልም ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል፣ ከመድኃኒቶች ውድነት እና ዕጥረት ጋር በተገናኘ አዲስ ማለዳ የሸማቾች ማኅበርን ብታነጋግርም፣ ማኅበሩ ከማሕበረሰቡ ወደ እኔ የመጣ ቅሬታ የለም በማለት ጉዳዩን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና ከኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና የጤና አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር አያይዞታል። የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን በበኩሉ፣ መስሪያ ቤቱ የመድኃኒቶችን ፈዋሽነት እና ጥራት እንጂ የዋጋ ተመን ማዉጣትም ሆነ የአቅርቦት ጉዳይ እኔን አይመለከተኝም ብሏል። የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዳንኤል ሜላ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ “ይህ ጉዳይ በጥቆማም ይሁን በሌላ መንገድ ወደ ተቋማችን አልመጣም፣ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ማጣራት ይፈልጋሉ” በማለት ተቋሙ ክትትል እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጥቆማ የሰጡን ግለሰቦች እንደሚሉት፣ መንግሥትም ሆነ የግል መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ መድኃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገቡ በመጠቆም፣ በተለይ ግለሰቦች የራሳቸውን ትርፍ ብቻ በማሰብ አንዳንድ በጣም ተፈላጊ እና ተከታታይ ክትትል ለሚጠይቁ የሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ላይ አለአግባብ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር በኹሉም ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ የገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ መንግሥት በተለይ በመድኃኒቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ ችላ ማለት የለበትም ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here