‹‹ሥም ማጥፋትን ከወንጀል ዝርዝር ማውጣት መሰረታዊ ነው››

Views: 321

ከስድስት ዓመት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ልዩ ራፖርተር ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ኬይ፣ በአሜሪካን አገር በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ክሊኒካል ፕሮፌሰር ናቸው። በተለይም ሰብአዊ መብት እና የጦርነት ሕጎች ላይ በማስተማር የሚታወቁት ዴቪድ፣ ሰብአዊ መብቶች ላይ የሚደርሱ ረገጣዎች ተጠያቂነት ሊያመጡ ይገባል በሚል በሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች እና በሚያቀርቧቸው የጥናት ወረቀቶቻቸውም ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል ሪዞሉሽን መሠረት፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመታዘብ ሰኞ ኅዳር 22/2012 ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዴቪድኅ ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ኅዳር 29 አመሻሹ ላይ ወደ ጄኔቫ ከመመለሳቸው በፊት ከአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። በተለይም ከስድስት ወር በኋላ ለካውንስሉ የሚያቀርቡትን ሪፖርት የመጀመሪያ ቅድመ ሪፖርታቸውን በአዲስ አበባ ይፋ ያደረጉት ራፖርተሩ፣ በዚህ ሪፖርታቸው ላይ ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታዎ የሕግ ማሻሻያዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ስለሚኖራቸው ጫና ለመመልከት ሞክረዋል?
በአጠቃላይ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫወዎች በተለይም በሕግ ማሻሻያዎች ረገድ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ላይ እየተጓዘ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህም የሲቪል ማኅበራት ሕግን፣ የሚዲያ አዋጅ ረቂቅን፣ የኮምፕዩተር ወንጀል ረቂቅ ሕግን እና የመሳሰሉትን ተመልክቻለሁ። እነዚህ ሕጎች ትልልቅ ከመሆናቸው አንጻር መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ ብዬ ባስብም፣ በአጠቃላይ ግን በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተዋል ብዬ አስባለሁ።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር ሕግ ብዙ ችግር ያለበት እና በተቻለ ፍጥነት መሻር ያለበት ነው ብዬ አስባለሁ። ከመንግሥት በኩልም ይህንን ሕግ ላለመጠቀም ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። መንግሥት የጸረ ሽብር ሕግ ያስፈልገኛል ብሎ ያመነ ይመስለኛል፤ ስለዚህ ይህ ሕግ ያስፈልገኛል ብሎ ካመነ ደግሞ ከሰብአዊ መብቶች ጋር የማይጣረስ መሆን ይገባዋል። በዚህ ላይም ዝርዝር አስተያየቴን በቅድመ ትዝብት ዘገባዬ (Preliminary Report) ላይ አካትቼዋለሁ።
ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ዓለማቀፍ መብት እንደመሆኑ እና ኢትዮጵያም የውጪ ባለሃብቶች በመገናኛ ብዙኀኑ ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ ክልክላ መቆየቷ፣ እንዲሁም አሁን እስከ 25 በመቶ ድረስ መፍቀዷን እንዴት ገመገሙት፤ የሚቀር ነገር አለ?
በመላው ዓለም ባሉ እንዲሁም በሠለጠኑ አና ዴሞክራሲያዊ ናቸው በምንላቸው አገራት ጭምር በሚድያ ባለቤትነት ላይ ገደብ መጣል የተለመደ ነው። ምንም አንኳን ይህንን ማድረግ የራሱ የሆነ ችግር ቢኖረውም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የመገናኛ ብዙኀኑን ፍላጎት በመመልከት እነዚህን ሕጎች የማሻሻል እና የመቀየር አማራጮች ሊኖሩ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታም የባለቤትነት ጥያቄ፣ ሐሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ጉዳይ ሳይሆን ነፃ የመገናኛ ብዙኀንን ለመፍጠር ምን ዓይነት የኢንቨስትመነት አማራጮችን እና የፋይናንስ ድጋፎች ያስፈልጋሉ የሚል ነው መሆን አለበት።
ምን አልባት ጠንካራ የሆነ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኀን ለመፍጠር ከ 25 በመቶ በላይ የሚሆን የውጪ ባለቤትነትን ሊፈልጉ ይችላሉ። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ሊሻሻል ይቻላል። ምንም እንኳን የሚድያ ባለቤቶችን አግኝቼ ባላነጋግርም፣ በአጠቃላይ ሚዲያዎች በጣም ትንሽ የሆነ የሃብት ምንጭ እንዳላቸው እገነዘባለሁ። ጋዜጠኞች የሚከፈላቸው ክፍያ በጣም ትንሽ ነው፣ ለሚዲያ ሥራ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን ማግኘትም ቀላል አይደለም። ስለዚህ የተለያዩ ድጋፎች ያስፈልጋቸዋል፣ ከውጪ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባሻገር የለጋሾችን ድጋፍ በመጠየቅም አማራጭ መውሰድ ይቻላል።
የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕጉን ተቃውመውታል። አገሪቱን እየገጠማት ያለው እና በዋናነት በጥላቻ ንግግር ምክንያት እየተባባሱ የሚገኙ ግጭቶችን መቆጣጠር አስፈላጊ አይደለም፤ ይህንን በሕግ መከልከል አይገባም ካሉ፤ ሌላ የሚጠቁሙት አማራጭ አለ?
ኢትዮጵያ ጥቃቶችን የሚሰነዝሩ ወይም የሚያነሳሱ የጥላቻ ንግግሮችን የመከልከል ግዴታ አለባት። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ እየተካሔደ የሚገኘውን ነገር ለተመለከተ ሰው፣ የጥላቻ ንግግር ሕግን ለመግታት ሕግ መውጣቱ ስሜት ይሰጣል። በመርህ ደረጃ እንዲህ ዓይነት ሕግ መውጣቱ ላይ ተቃውሞ የለኝም፤ ነገር ግን ሕጉ ምንድነው፣ በውስጡ ምን ምን ይዟል የሚለው ነው ጥያቄው። አሁን ያለው ረቂቅ የጥላቻ ንግግርን በሰፊው በመተርጎም እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሰራጨት ወንጀል እንዲሆን ማድረጉ አግባብ አይደለም።
ይህ ጋዜጠኞች ላይ በቀላሉ ሊተገበር ይችላል ወይም የውይይት መድረኮች ላይ የሚነሱ ሐሳቦቸን ወንጀል አድርጎ እስከመፈረጅ ሊያደርስ ይችላል። ይህም ፖለቲካው በብሔር በተቃኘበት አገር ላይ፣ ይህ እጅግ አደገኛ ሊሆን ይችላል። እና የእኔ ስጋቶች እነዚህ ናቸው። በዓለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች መሠረትም መንግሥት በተለይ ጥቃቶችን የሚያነሳሱ የጥላቻ ንግግሮችን የሚከላከሉ ሕጎችን ማፅደቅ ይችላል። የእኔም አስተያየት ከሰብአዊ መብቶች መርሆዎች ጋር አብሮ የሚሔድ ሕግ ያስፈልጋል የሚል ነው።
የሥም ማጥፋት ወንጀል ለመገናኛ ብዙኀን በፍትኀ ብሔር ብቻ እንዲታይ አሁን ያለው ረቂቅ ቢደነግግም ዜጎች አሁንም ሥም ማጥፋትን ተከትሎ በወንጀል እንዲጠየቁ የሚያደርግ ሕግ አለ። ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን አይገድብም?
የሥም ማጥፋት ድርጊትን ከወንጀል ዝርዝር ማውጣትን በጣም አጥብቄ እደግፋለሁ። ይህ በእድገት ላይ ላለ የመገናኛ ብዙኀን ኢንዱስትሪ መሠረታዊ ነው ብዬም አምናለሁ። አንድ ጋዜጠኛ በሚሠራው ሥራ ምክንያት መንግሥት ደስተኛ ባይሆን ሊያስረኝ ይችላል ብሎ በስጋት ውስጥ ሆኖ መሥራት የለበትም። ስለዚህ ይህንን ማስወገድ በጣም አስፈላጊ ነው።
በዓለም ላይ ሥም ማጥፋት በፍትኀ ብሔር ያስቀጣል። ነገር ግን በፍትኀ ብሔርም ቢሆን ቅጣቱን መገደብ ያስፈልጋል። ከወንጀል ቅጣት የማይተናነስ ከፍተኛ ቅጣት አለመጣሉን ከግመት ውስጥ መክተት ያስፈልጋል። በተመሳሳይም የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ታዋቂ ሰዎችን እና የሕዝብ ተወካዮችን ግን ማጠቃለል የለበትም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሕጎችን ብዙ ጊዜ የሚጠመዝዙት እነዚህ አካላት ስለሆኑ።
የመንግሥት ሚድያ ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ ውስጥ የመንግሥት ሚድያዎች የሚኖራቸው ሚና እና በኢትዮጵያ ያሉትን የሕዝብ ሚድያዎች ሚና እንዴት ተመለከቱት?
በረጅም ጊዜ እቅድ በመያዝ መንግሥት ሚድያዎቹን ወደ ሕዝብ መገናኛ ብዙኀን ስለመቀየር ማስብ ይኖርበታል። በዚህም መንግሥትን መተቸት የሚችል እና ሕዝቡም አግባብ ያለው መረጃ የሚያገኝበት እንዲሆን የሚያስችለውን አቅም መስጠት ያስፈልጋል። የሕዝብ መገናኛ ብዙኀን የንግድ ተቋማት ሳይሆኑ ለሕዝብ ፍለጎት ሲባል የሚቀረጹም መሆን አለባቸው። ምንም እንኳን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀንን ባልጎበኝም፣ እንዲህ ዓይነት ነፃነት እንደሌላቸው ግን መረዳት ችያለሁ። ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር በነበረኝ ቆይታ እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን ይቀበላሉ፤ እኔም ይህ ሊፈታ የሚገባው ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ።
የመንግሥት ተቋማትን የመረጃ አሰጣጥ እና ግልጽነትን በተመለከተስ?
የመንግሥትን የመረጃ አሰጣጥ እና የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያዎችን አቅም ለማሻሻል መሞከርም አስፈለጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህም ፕሮፖጋንዳን እንደ መረጃ መስጠት ማለት ሳይሆን፣ ሊረጋገጥ የሚችል እውነተኛ መረጃን ማካፈል ማለቴ ነው። በዚህ ረገድ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ አምናለሁ። በመንግሥት አንዳንዴ የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ መዘገብ የሚቻል እና የማይቻል ብሎ መለየት ሊኖር ይችላል፤ ይህ ግን እጅግ ያልተለመደ ድርጊት ነው።
የጋዜጠኝነት ሞያ ላይ የሥልጠና ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፤ የጎበኙት የትምህርት ተቋም አለ?
የጎበኘሁት ተቋም ባይኖርም የተወሰኑ ሰዎች ስላለው ክፍተት ሲያስረዱኝ ነበር። ማንም ሰው ስለ ሃሰተኛ መረጃ መብዛት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኀን የሙያዊ ተወዳዳሪነት ካሰበ፣ የጋዜጠኞችን የሥልጠና እድሎች ማስፋት አማራጭ የለውም። ይህም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች ማለቴ ነው።
በአንድ ሳምንት ቆይታዎ ከአዲስ አበባ በተጨማሪም ባህር ዳር እንደነበሩ ነግረውኛል። በባህር ዳር ምን ታዘቡ?
ባህርዳር ፀጥ ያለች ከተማ ነች፤ ወድጄዋለሁ። በባህርዳር በተለይ ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ነው የተወያየሁት። ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጋር ተወያይተናል። በጣም አስተዋዮች ናቸው ማለት እችላለሁ። ማስተዋል ስል ሐሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን የማክበር እና ካላግባብ ክልከላዎች የመጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተረድቻለሁ። በሌላ በኩል ግን ጥላቻን፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን እንዲሁም የሃሰት መረጃዎቸን የመከላከል ፍላጎት አላቸው።
እንደተረዳሁት፣ ሰዎችን ለዚህ ብለው የማሰር እና የመቅጣት ፍላጎት ባይኖራቸውም፣ ይህንን ለመቆጣጠር በሕግ እና በሰብአዊ መብት መርሆዎች መሰረት ማድረግ ግን ይፈልጋሉ። በጣም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ማለት እችላለሁ፤ ግልጽ የሆነ አእምሮ ያላቸው ነበሩ ማለትም እችላለሁ። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ያየሁት ይህንኑ ነው። በጣም ግሩም ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ተማሪዎቹም ፋክሊቲውም የለውጥ ሥራውን ለመጠበቅ እና ለማስቀጠል ክፍተኛ ጉጉት አይቼባቸዋለሁ።
ለመጨረሻ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ራፖርተር ወደ ኢትዮጰያ የመጣው ከ 14 ዓመት በኋላ ነው። የቀደመውን ሪፖርት ይመለከቱታል ብዬ አምናለሁ፣ ማነፃፀር እንችላለን?
ወደ ኋላ ተመልሼ አልተመለከትኩም፤ በዛ ላይ አሁን ያለው ሁኔታ እና ያኔ የነበረው ይለያያል። ወደ ምእተ ዓመቱ መጀመሪያ መመልከት ያን ያህል ለሪፖርቴ ይረዳኛል ብዬ አላስብም። በእርግጥ ታሪክ ሁሌም ይጠቅማል። በዛ ላይ ደግሞ ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ ላይ ብቻ ነው የኔ ትኩረት፣ ያኔ እንደዛ አልነበረም። ስለዚህ ብዙም አይጠቅመኝም። ለፕሬስ ነጻነት ቀን ግን መጥቼ ነበር፤ ያንን ዓለማቀፍ ጉባኤ ኢትዮጵያ ማዘጋጀቷ በራሱ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ።
በእስር ላይ ያለውን ጋዜጠኛ ወይም ታስረው የተፈቱትን አነጋግረዋል?
አይ አልጎበኘሁም። ታስረው የተፈቱ ጋዜጠኞች መኖራቸውን ግን ተረድቻለሁ። እንደ ሲፒጄ ሪፖርት ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ አሁንም በእስር ቤት መኖሩን አውቄአለሁ። ነገር ግን ምንም እስረኛ አልጎበኘሁም። ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ ሪፖርቴን ጁን ላይ እስካቀርብ ድረስ ሰዎችን ማግኘቴን እቀጥላለሁ። ሪፖርታችንም እየተነሱ ያሉ ስጋቶችን ያካተተ እንዲሆን ለማድረግ ጥረታችን ይቀጥላል።
በደቦ ፍርድ የተጎዱ ጋዜጠኞችን ጉዳይ ግን ተመልክተዋል?
በተለይ በኢንተርኔት ጋዜጠኞች ላይ ስለሚደርሰው ጥቃት ተረድቻለሁ፣ አካላዊ ጥቃት ስለደረሰባቸው ጋዜጠኞች ግን ማንም አልነገረኝም።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com