የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እና በአገር ጉዳይ ላይ የመወሰን ዕድል

0
1094

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሴቶች የሚሰጠው ዕድል እና ሴቶችን ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዲገቡ የሚስብ ምቹ ሁኔታ እንደሌለው የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚነሳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የወንዶች የበላይነት የጎላበት እና የሴቶች ተሳትፎ አናሳ የሆነበት ከመሆኑ በላይ፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዳይመጡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንባዜ የተዛባ መሆኑ ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ በተለያዩ ምክንያቶች የተገደበ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ዋና ተዋናያን የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በፖለቲካ አመራርነት ቀርቶ በአባልነት እንኳን ማካተት እምብዛም የለመዱት አይመስልም። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢያሳይም፣ የሴቶች የመሪነት ሚና፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ከወንዶች እኩል በፖለቲካ መሳተፍ ይችላሉ የሚለው ግንባዜ የሚፈለገውን ያክል እንዳልሆነም ይገለጻል።

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የተገደበ መሆኑ የሴቶች በአገር ጉዳይ የመወሰን እና አስተዋጽኦ የማድረግ አቅምና ዕድል ላይ ገድብ የጣለ መሆኑም ይነሳል። ሴቶች በመሪነት ወይም በፖለቲካ ከወንዶች እኩል የመሳተፍ ዕድል ቢኖራቸውና የማኀበረሰቡ ግንባቤ ቢቀየር የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁን ካለበት ከኃይል ፍትጊያና እርስ በእረስ የመጠላለፍ ፖለቲካ ሊወጣ እንደሚችል ብዙዎች ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ሴቶች ካላቸው የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ችሎታቸው አንጻር የአመራርነት መርሃቸው ከኃይል ይልቅ በሥልት የታገዘ መሆኑን በማንሳት ነው።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳድግ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የግንዛቤ ችግር መፍታት እና ሴቶች ለፖለቲካ ያላቸውን አመለካከት መቀየር ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ይነገራል። “ፖለቲካ ለሴቶች ሳይሆን ለወንዶች የተፈጠረ ነው” የሚለውን ከማኀበረሰቡ የሚመነጨውን የተዛባ አመለካከት መቀየር ላይ መሥራት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶችና በሴቶች እና በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው Action for Social Development and Environmental Protection Organization (ASDEPO) የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት ላይ እየሠራ ይገኛል።

ድርጅቱ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት፣ ከኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ግንዛቤ መፍጠር ላይ እየሠራ መሆኑን የድርጅቱ የሥርዓት ጾታ አማካሪ ፍቅር ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የሴቶችን ፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እንቅፋት የሆነውን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ “አክሽን ፎር ሶሻል ደቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫሮመንታል ፕሮቴክሽን ኦርጋናይዜሽን” ወንዶች የበላይነት ያየለበትን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመቀየር ከሲቪል ማኅበረስብ አደረጃጀቶች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።

የድርጅቱ የሥርዓተ ጾታ አማካሪ ፍቅር እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች የሰጠው ዕድል አናሳ መሆኑን ተከትሎ፣ ሴቶች አገራቸው ጉዳይ የመወሰንና የመሪነት ሚና የመጫወት ዕድል አላገኙም ይላሉ። በኢትዮጵያ የሴቶች ፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ የሆነው ከማኅበረሰቡ በሚመነጩ የታሪክ፣ የባህል፣ የፖለቲካ አመለካከት መዛባት እና ከማኅበራዊ ተጽዕኖዎች መሆኑን ፍቅር ይገልጻሉ።

ሴቶች በኢትዮጵያ ታሪክ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ያላቸው ተሳትፎ እና አቅም የተገደበ መሆኑን የሚያነሱት አማካሪዋ፣ ሴቶች በርካታ ኃላፊነቶች የሚሸከሙ ሆነው ሳለ የሚገባቸውን የመሪነት ሚና አላገኙም ይላሉ። በተፈጥሮ ሴቶች ከወንዶች እኩል በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ የመሳተፍና የመፈጸም ብቃት እያላቸው በግንዛቤ ክፍተት የተነሳ ሴቶች ከወንዶች እኩል በፖለቲካ የመሳተፍ መብታቸውን በሚገባ አለማስከበራቸውን ይገልጻሉ።

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ሴቶች በአገር ጉዳይ የመወሰን ዕድላቸው የተገደበ ነው የሚሉት አማካሪዋ፣ አሁን የሚታዩትን መነቃቃቶች አጠናክሮ ለመቀጠል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ተከትሎ ፖለቲካው በወንዶች የበላይነት ከመመራቱ ባሻገር፣ ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈጥረው የተዛባ አመለካከት እንዳለ ይገለጻል።

ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሴቶች የተፈቀደ ሳይሆን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የተገደበ መሆኑን ለመታዘብ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች የሰጡትን ቦታ መመልከት በቂ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። የሥርዓተ ጾታ አማካሪዋ ፍቅር፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ከአባልነት እስከ አመራርነት የማምጣት ችግር እንዳለባችው ይስማማሉ።

አሁን ላይ ቀድሞ ከነበረው የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል መሻሻል ቢያሳይም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባላት እስከ አመራርነት ያለውን በበላይነት የተቆጣጠሩት ወንዶች መሆናቸውን ይገልጻሉ። በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚታየው ሴቶችን በአባልነትና በአመራርነት ያለማካተት ችግር የሚመነጨው ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ውጤታማ ይሆናሉ የሚል ግንዛቤ ባለመኖሩ ሲሆን፣ የችግሩ መሠረት ግን አጠቃላይ ካለው የግንዛቤ ክፍተት ነው።

በዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ኹኔታም ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ መሆኑ ዓለም የሚያቀው ጉዳይ ነው። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማነስ የሴቶች የመፈጸም ወይም የአመራርነት አቅም ማነስ አለመሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ይልቁንም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የገደበው የፖለቲካ መድረኩ ለወንዶች ያደላ በመሆኑ እንደሆነ ይገለጻል።

የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ጎልቶ ሲፈተሸ፣ በዓለም ዐቀፍም ሆነ በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ተሳትፎቸው በቅደም ተከተላቸው እየቀነሰ ይመጣል። በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች ብቻ በፖለቲካ ተሳትፏቸውና በአመራር ብቃታቸው ሚዛን ደፍተው ወደ ፊት ብቅ ሲሉ ያታያሉ። ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የሴቶች የመሪነት ሚና ከስር ከመሠረቱ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያማከለ እንዳልሆነ ይገለጻል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቀደሙት ጊዜያት ሲታወስ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሲነሳ “የሴቶች የመሪነት ተሳትፎ ወርቃማ ዘመን” ተብሎ የሚወሳው 100 ዓመታትን ወደ ኋላ መጓዙ ግድ ይላል። ለ100 ዓመታት ወደ ኋላ ተጉዘን የምናገኘው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና መሪነት የኢትዮጵያ ሴቶች አርአያ ሆነው ለዘላለም የሚታወሱትን እቴጌ ጣይቱንና ንግስተ ነገሥታት ዘውዲቱን ነው። የሴቶችን የመሪነት ብቃት ያስመሰከሩት እነ እቴጌ ጣይቱ ሲታወሱ፣ ሴቶች ከወንዶች እኩል የመሪነት ጥበብ እንዳላቸው የሚያመላክት መሆኑን የሚገልጹት ፍቅር፣ አሁን ላይ የእነ አቴጌ ጣይቱ የመሪነት ብቃት በታሪክ ከመወሳት ባለፈ በዚያን ጊዜ ሴቶች የነበራቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የተጽዕኖ ፈጣሪነት ዐቅም አሁን ላይ አይታይም ይላሉ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ የሆነበት ምክንያት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው “ሴት የቤት እመቤት ናት” የሚለው ግንዛቤ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዳይወጡ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቃሳል። በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ፍቅር፣ በታሪክ እና በባህል በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ሴቶች የቤት ውስጥ እንጅ የአደባባይ አመራርነት እንዳይለማመዱ በመድረግ ረገድ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል።

አሁን ለይ በፖለቲካው እየተሳተፉ ያሉ ሴት ፖለቲኮኞች፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ውስንነት በኢትዮጵያ የቀነጨረ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ቆንጅት፣ በዓለምም ይሁን በአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ነው የሚያነሱት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና የመሪነት ሚና ውስን የሆነው ከቀደሙት ዘመናት ጀምሮ የባህል፣ የእምነት፣ የሥነ ልቦና ጫና ስለነበር እና ሴቶች የአደባባይ ሰው ከመሆን ይልቅ የቤት ሥራ ከዋኞች በመሆናቸው እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

ከቀደሙት ጀምሮ እስካሁኑ ዘመን ድረስ የፖለቲካ ድርጅቶች በወንዶች የበላይነት የሚመሩ መሆናቸው ሴቶች የመሪነት ዐቅም እንዳላቸው ለማሳየት ዕድሉን እንዳያገኙ ያደረጋቸው ሲሆን፣ የቀደሙትም ይሁን የአሁኖቹ የፖለቲካ መሪዎች ሴት አደባባይ ወጥታ እንድትሳተፍ ከመፍቀድ ይልቅ የቤታቸውና የእነሱ ተንከባካቢ የማድረግ አባዜ እንዳለባቸው ይገለጻል።

በሌላ በኩል ሴቶች በፖለቲካ መድረክ ጎልተው እንዳይታዩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል፣ የፖለቲካ ዘርፉ ለወንዶች ያደላ መሆኑን ተከትሎ ሴቶች ለመረጃ እና ለፖለቲካዊ ጉዳዮች ቅርብ አለመሆናቸውን ፍቅር ያነሳሉ። ፍቅር እንደሚሉት ሴቶች ወደ ፖለቲካው ለመግባት የመጀመሪያ መንደርደሪያ የሆነውን ለመረጃ ቅርብ መሆንና መንቃት፣ ፖለቲካን መከታተል፣ ወደ ፖለቲካው ለመግባት ፍላጎት እና ግንዛቤን ማሳደግ ነው።

በመሆኑም ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፏቸው ከወንዶች ዕኩል ጎልቶ እንዲወጣ ከስር ከመሰረቱ ለመረጃ ቅርብ መሆንና ባሉበት ደረጃ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ማሳየት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በትምህርትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ ሲያድግ ወደ ፖለቲካው የመሣብ ዕድል ይኖራቸዋል የሚሉት ፍቅር፣ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ መጀመሪያ ሴቶች በትምህርትና በኢኮኖሚ ዐቅም ካላገኙ ወደ ፖለቲካ የመግባት ዕድላቸው አናሳ መሆኑን ይግልጻሉ። እንደ ማሳያነት የሚያነሱትም በትምህርት ደረጃቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶች እንኳን ወደ ፖለቲካው ለመግባት ይፈራሉ ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ውጤታማ ባልሆን የሚል ሥጋት እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሐሳበቸውን ስለማይደግፉት መሆኑን ይገልጻሉ።

አሁን አሁን ሴቶች በፖለቲካው ጎልተው ባይወጡም በትምህርታቸው ከወንዶች ዕኩል ጎልተው የሚታዩበት ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም፣ ፖለቲካ ለወንዶች የተተወ እስኪመስል ድረስ ፖለቲካ የሚፈሩ ሴቶች ቁጥር ይበዛል። ይህን አመለካከት ለመቀየር እየሠራ ያለው ድርጅት፣ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሚዲያዎችና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች በዘርፉ የሚታየውን የግንዛቤ ክፍተት መሙላት እንደ አንድ ዕርምጃ ነው።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የመጀመሪያው ሥራ ማኅበረሰብን ማንቃት ነው የሚሉት ፍቅር፣ ማኅበረሰቡን ለማንቃትና ግንዛቤ ለመፍጠር ለማኅበረሰቡ በተለያየ መንገድ ቅርብ የሆኑት ሲቪል ማኅበራት እና ሚዲያ ትልቁን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ማኅበረሰብ ማንቃት እንደ አንድ መሰረት ሲወሰድ፣ ከቤተሰብ እና ከትምህርት ቤት መጀመር እንዳለበት ፍቅር ይጠቁማሉ። አሁን ላይ የሚታየው የሴቶች ፖለቲካ መነቃቃት በከተሞች እና በትምህርታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱ ሴቶች የተገደበ እንዳይሆን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከታችኛው የማኀበረሰብ ከፍል ጋር መሥራት እንዳለባቸው ከድርጀቱ ባገኙት ግንዛቤ መሰረት አሁን ላይ ፕሮፖዛሎችን ቀርጸው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ያሉ ማኅበራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የሚዲያውን ዘርፍ ስንመለከት ሚዲያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ቢኖረውም፣ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሚዲያው ድርሻ አናሳ መሆኑን ፍቅር ይገልጻሉ። ሚዲያው ለሥርዓተ ጾታ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ተከትሎ የሚሠሩ ፕሮግራሞችና ዘገባዎች የሴቶችን ፖለቲካ ተሳትፎ የሚያበረታቱ ባለመሆነቸው በሚዲያው ዘርፍ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ድርጅቱ ለሚያከናውነው የማንቃት ሥራ የተለያዩ መልዕክቶችን እና ጽሑፎችን በሚዲያዎች የማሰራጭት ሥራ እየሠራም መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here