ቻምፕየን ኮምዩኒኬሽንስ የሚያሳትመውና በየወሩ ለአንባቢያን የሚያደርሰው ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› መጽሔት 100ኛ ልዩ ዕትሙን በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ለንባብ አብቅቷል፡፡
ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው (ኢ.ቢ.አር.) ወርሐዊ መጽሔት፣ በምጣኔ ሀብት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን፣ በተለይም የግሉ ዘርፍን ለማበረታታት የሚሠራ ነው። የዘጠነኛ ዓመት መዳረሻው ላይ የሚገኘው መጽሔቱ፣ በኢትዮጵያ አንቱ የተባሉ ምሁራንን በዓምደኝነት በማሳተፍ እንዲሁም በእንግድነት በማቅረብ፣ በተለይም ከምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ ሙያዊ ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉ በማድረግ ያለማቋረጥ በኅትመት ላይ ቆይቷል።
መጽሔቱ ከአንባቢያን ጋር በቆየባቸው ዓመታት አምስት (አንድ ሴት እና አራት ወንድ) ዋና አዘጋጆች መርተዉታል። መጽሔቱ ዋነኛ ትኩረቱን በምጣኔ ሀብት ዙሪያ የሕዝብ አመለካከትን መቅረጽ፣ ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና የግሉን ዘርፍ ማገዝ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ዓምዶች ስላሉት በማኅበረሰብ፣ በሕይወትና ጥበብ፣ በስፖርታዊና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ለአንባብያን እያደረሰ ይገኛል።
የመጽሔቱን 100ኛ ዕትም በይፋ ለማክበር በአዲሱ ዓመት ወርሐ-መስከረም ማክሰኞ በአራተኛው ቀን (04/01/2014) ላይ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ደማቅ መሰናዶ ተዘጋጅቷል። በዚህ ዝግጅት ላይ የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የመጽሔቱ አንባቢዎች፣ ጽሑፍ አቅራቢና ሐሳብ ሰጪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የግል ባለሀብቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ በመጽሔቱ ማስታወቂያ አቅራቢዎች እንዲሁም የቻምፕየን ኮምዩኒኬሽንስ ሠራተኞች ይገኛሉ።
በዚህ መሰናዶ ቻምፕየን ኮምዩኒኬሽንስ የዕውቅና እና የምስጋና ሽልማቶችን የሚያበረክት ሲሆን፣ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተያያዙ ነጥቦችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችም በመድረኩ ይቀርባሉ። በዕለቱ የመጽሔቱ ያለፈ ጉዞ ይዳሰሳል እንዲሁም ቀጣይ ዕርምጃና ዕቅድ ይቃኛል።
በዚህ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት (EBS) የኢትዮ-ቢዝነስ ዝግጅት የሚድያ አጋር እንደሆነና፣ በርካታ መገናኛ ብዙኃን ኹነቱን እንደሚዘግቡት ይጠበቃል።
ቻምፕየንስ ኮምዩኒኬሽንስ ከኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው በመቀጠል ኹለት የኅትመት ውጤቶችን ለአንባብያን ያደርሳል። ኹለት ዓመት ተኩል የተሻገረችው ሳምንታዊዋ የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ አንዷ ስትሆን፣ በማኅበራዊ ሕይወት ለውጥ ለማምጣት ቤተሰብና ማኅበረሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው አዲስ ማለዳ ወርሃዊ መጽሔትም የቻምፕየንስ ሌላኛው የኅትመት ውጤት ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014



