በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማስተር እና ፒኤችዲ ለመማር የሚመዘገቡ ተማሪዎች ለምዝገባ የሚከፍሉት 600 ብር ከመጠን በላይ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።
ቅሬታችን ክፍያ ብቻ አይደለም የሚሉት ፈተናውን የወሰዱት ጌትነት ታደሰ፣ የፈተና ውጤት አሠራሩ ትክክል አይደለም ብለዋል። የአንድ ሰው የማስተር ማለፊያ ነጥብ 30 በመቶ ቢሆንም፣ ከተፈተኑበት የክፍል ተማሪዎች ጋር በማስተያያት ውጤቱ ካነሰ የሚወድቅ ይሆናል ብለዋል።
አንድ ክፍል ውስጥ 120 ተማሪዎች ከተፈተኑ ከእነሱ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ብቻ ነው የሚያልፉት ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል። ይህ ደግሞ የማለፊያ ውጤት 30 በመቶ ቢሆንም፣ ከክፍል ውስጥ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ ካለ የሚወድቅ ነው ብለዋል። ጌትነት ያመጣው ውጤት 40 በመቶ ቢሆንም አብረውት ከተፈተኑት ተማሪዎች አንጻር መውደቁን ገልጸውለታል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ የመጀመሪያውን ፈተና ማለትም (General Aptitude Test -GAT) ለመውሰድ 600 ብር ከፍለው ፈተናውን ያለፉ ደግሞ ለዲፓርትመንት ፈተና 200 ብር ተጨማሪ ይከፍላሉ።
ኹለተኛውን ዙር ፈተና ለመውሰድ ካለፍን ለምን ተጨማሪ እንከፍላለን ሲሉም ነው ቅሬታ ያቀረቡት። በአንድ ክፍያ ማጠቃለል እና እንደ መንግሥት ተቋም ክፍያውን ማሳነስ ነበረበት ሲሉ ነው ቅሬታ ያቀረቡት።
የትምህርት ክፍያ መጨመር አግባብ አለመሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እየገለጹ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ይህን ያህል ማስከፈል ተገቢ ነው ወይ ሲሉም ጠይቀዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለ2014 ለድኅረ ምረቃ ትምህርት በቀን መርሃ ግብር በኹለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም በማታ መርሃ ግብር በኹለተኛ ዲግሪ ለማስተማር በርካታ ተማሪዎችን ሲመዘግብ ቆይቷል። ለድኅረ ምረቃ ትምህርት ለማመልከት የዩኒቨርስቲዉን የድኅረ ምረቃ የመግቢያ ፈተና ቀድሞ መዉሰድ እና ፈተናዉን ማለፍ ግዴታ ሲሆን፣ ለዚህም ደግሞ የመፈተኛ ክፍያ ብር 600 መክፈል እንዳለባቸው የዩኒቨርስቲው ድረ-ገጽ መረጃ ያሳያል።
ዩኒቨርስቲው የማመልከቻና መፈተኛ ቀን ብሎ ያወጣው ከ ሐምሌ 12 እስከ ነሐሴ 12/2013 ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት እስከ ነሐሴ 28/2013 ድረስ አራዝሞት ነበር። በነዚህ የምዘገባ እና የመፈተኛ ቀናት የተመዘገቡት ሰዎች ቁጥር በጣም በርካታ መሆኑን ፈተናውን የወሰዱ ግለሰቦች ገልጸዋል።
በአንድ ቀን ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ከ300 እስከ 600 የሚደርስ መሆኑን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የምዝገባ ቀን መራዘሙ ለምንድነው ሲሉም ጥያቄ አንስተዋል። የምዝገባ ቀኑን ወደ ነሐሴ 28 ያራዘመው ዩኒቨርስቲው ፈተናውን የሰጠው ለ30 ቀን እንኳን ቢሆን በድምሩ 18 ሺሕ የሚደርሱ ተማሪዎች እንደተፈተኑ ያሳያል።
አነዚህ ተፈታኞች ለፈተና የከፈሉት ገንዘብ 600 ብር በመሆኑ በአጠቃላይ ወደ10 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ዩኒቨርስቲው ማግኘቱን ይገምታል። አዲስ ማለዳ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በተደጋጋሚ ብትደውልም በቅሬታው ላይ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።
ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014



