አሳሳቢው የወሎ ረሃብ!

0
1172

በኢትዮጵያ የቀድሞ የረሃብ ታሪክን በሚያስታውስ መልኩ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን የሰሜን ወሎ ረሃብ ተከትሎ መንግሥት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት በሚፈጸመው ጥቃት ዕርዳታ በሚፈልገው ደረጃ እያደረሰ አለመሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡
ወደ አማራ ክልል የተስፋፋውን ጦርነትና መፈናቀል ተከትሎ የተከሰተውን ረሃብ እና መደረግ የሚገባውን ድጋፍ በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላትን በማነጋገር የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ በሐተታ ዘማለደ ተመልክታዋለች፡፡

በኢትዮጵያ የቀድሞ የረሃብ ታሪክን በሚያስታውስ መልኩ ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨው አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል የተከሰተው ረሃብ አሳሳቢ እየሆነ ነው። መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክርም ህዋሓት እያደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት በሚፈልገው ደረጃ ዕርዳታውን እያደረሰ አለመሆኑን እየገለጸ ይገኛል።

‹ድምጻችን ለኢትዮጵያችን› የሚል መሪ ቃል ያነገበ ቡድን ወደ አማራ ክልል እስከ ውጫሌ ግንባር ድረስ በመጓዝ ለአንድ ሳምንት የቆየ ሲሆን፣ የዚህ ቡድን አባል ከሆኑት ውስጥ የኢትዮ 251 ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ አንዱ ናቸው።

በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ቡድን አማራ ክልልን መውረር ከጀመረ ኹለት ወራት አስቆጥሯል የሚሉት አራጋው አላማጣ፣ ቆቦ፣ ኮረም እና ዋግኽምራ በቡድኑ ከተያዙ አካባቢዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ወልድያ፣ ጋይንት፣ ጋሸና እና ዋጃ በቅርብ የተያዙ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ መግባታቸውን አራጋው አረጋግጠዋል።

በከተማዎቹም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በመኖራቸው ለማስተናገድ ከባድ በመሆኑ ወደ አዲስ የሚገቡ ተፈናቃዮች አማራጭ መጠለያዎችን በመፈለግ በመንከራተት ላይ እንደሚገኙ አራጋው ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው የነበሩ ወሎ ላይ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ለዳግም መፈናቀል እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ራያ ቆቦ የነበሩት የቀድሞ ተፈናቃዮች አሁንም እንደገና ተፈናቅለው ወደ ደሴ የገቡ ሲሆን፣ ደሴ ከተማ ከአቅሟ በላይ በመሆኑ ወደ ኮምቦልቻ እየሔዱ ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው ነው ሲሉ አራጋው ጠቁመዋል።
በተለይ ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው የቀሩ ዜጎች ኹሉም መሠረተ ልማት በመቋረጡ ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል ብለዋል።

ቤታቸው የቀራቸውን ጥሪት እንዳይጠቀሙ እየተዘረፉ፣ ቤታቸው እየተቃጠለ፣ እየተተኮሰባቸው ይገኛሉ ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ዜጎች በጣም ከፍተኛ ረሃብ ላይ በመሆናቸው አቅራቢያቸው የሚገኙ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች ምግብ እያቀረቡላቸው የሚገኙ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ረሃብ ላይ መሆናቸውን አራጋው አረጋግጠዋል።

በተለይ ቆቦ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በፍርሃት አካባቢውን ለቀው እየወጡ ስለሆነ አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች በየቤቱ እየተገደሉ ነው ብለዋል።
ከዚህ ኹሉ በላይ ከተማውን ለቅቀን አንሔድም ያሉ ነዋሪዎች ውስጥ የስኳር፣ ደም ግፊት፣ ኤች አይ ቪ እና ካንሰር ታማሚዎች ይገኛሉ። እነዚህ ታማሚዎች ክትትል የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ የሆስፒታሎች አገልግሎት በመቋረጡ እና ይህ ችግር ይመጣል ብሎ በቂ መድኃኒት የገዛ ግለሰብ ባለመኖሩ በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ አራጋው ጠቁመዋል።

‹‹እኔ በግሌ የደረሰኝ መረጃ ከቆቦ ተፈናቅለው የመጡት ሰዎችን አስጠልለው የነበሩ የደም ግፊት የነበረባቸው አዛውንት በአሁኑ ሰዓት መድኃኒት ባለማግኘታቸው መሞታቸው ሰምቻለው›› ብለዋል።
በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ተልኳል የተባለው ዕርዳታ ተፈጻሚነቱ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት አራጋው፣ በአማራ ክልል ከፍተኛ ድጋፍ መከናወን አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የተመሠረተው ‹ወሎ ቤተ አምሐራ በጎ አድራጎት ማኅበር› ራያ ቆቦ፣ ደቡብ ወሎ፣ አርጎባ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ ወረርሽኝ የመከላከል ሥራ የሠራ ማኅበር ሲሆን፣ ለተከሰተው ረሃብ ድጋፍ ሊማድረግ ማቀዱን አራጋው ገልጸዋል።
ከማኅበሩ አባል አንዱ የሆኑት አራጋው፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር እንጠቀም በሚል ማኅበረሰቡን በማስተባበር የውጭ እና የአገር ውስጥ አባላት መሰብሠባቸውን ጠቁመዋል።
ይህ ማኅበር ቀድሞ በሠራቸው ሥራዎች ትኩረት ባላገኙ አካባቢዎች ዕርዳታዎችን ተደራሽ በማድረግ የሚታወቅ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ማኅበሩ ጦርነቱን ሸሽተው የተፈናቀሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ዓላማ አድርጎ የተነሳ ሲሆን፣ ከዕለት ወደ ዕለት ችግሩ በመባባሱ የዕርዳታ ማሰባሰቡን በማጠናከር የጋራ የሒሳብ ደብተር (አካውንት) በመክፈት ረሃቡን ለመቅረፍ ማሰቡን አራጋው ገልጸዋል።
የተፈናቃዮችን ችግር በዓይኔ ተመልክቻለሁ የሚሉት አራጋው፣ በርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ በምግብ ዕጦት እየተሰቃየ መሆኑን አንስተዋል።

የሰው ልጅ በረሃብ ወቅት ቶሎ እንዲያገግም የሚረዳው መደበኛ የሥርዓተ ምግብ ነው የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ከፍተኛ አማካሪ ቴዎድሮስ ግርማ ናቸው፡
የሰው ልጅ በየዕለቱ የሚፈልጋቸው ንጥረ ነገሮች አሉ። በዋናነት የኃይል ሰጪ(ካርቦሃይድሬት)፣ ገንቢ ምግቦች (ፕሮቲን)፣ የቅባት አይነቶች፣ የማዕድናት እና የቫይታሚኖች መኖር አስፈላጊ ነው።
ጤናማ አካላዊ እና አእምሮአዊ ዕድገት እንዲኖር ደግሞ የምግብ ዕጥረት ያላጋጠመው መደበኛ ሰውም መመገብ አለበት።

በምግብ ደረጃ በመደበኛነት አንድ ሰው የእህል ውጤት ስንዴ፣በቆሎ፣ ጤፍ፣የተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬ በየቀኑ 400 ግራም ያህል ያስፈልገዋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማዕድናት እና ቫይታሚን ማግኘት ይገባዋል።
የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤት እንደ ሥጋና ወተት እንዲሁም በቀን አንድ ሺሕ ሚሊ ግራም ካልሲየም ስለሚያስፈልግ ያንን ለማሟላት በቀን አንድ ብርጭቆ ወተት መጠጣት አለበት።

እንደ ብረት(አይረን) ለማግኘት ደግሞ ባቄላ፣ ሽንብራ እና ቀይ ስጋ መመገብ ያስፈልጋል። በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ በሚፈጠር የረሃብ ወቅት ከመደበኛው የበለጠ ንጥረ ነገሮች ያስፈልጉታል ሲሉ ቴድሮስ ገልጸዋል።
አንደነዚህ አይነት ንጥረነገር የተሞላባቸው ምግቦች አለማግኘት ለመቀንጨር ችግር ያጋልጣል። በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ የመሥራት እና የመፍጠር አቅሙም ቢሆን ደካማ ይሆናል።

በአገር ደረጃ እንደሚታየው ከሆነ ደግሞ 16 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ከክፍል ክፍል መዘዋወር የማይችሉ ናቸው። ይህ ጥናት ከአጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ 16 በመቶዎቹ የትምህርት አቀባበል ደረጃቸው ደካማ መሆኑን ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ 28 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት በመቀንጨር (የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገብ) ምክንያት ይሞታሉ። እንዲሁም የአገሪቷ የማምረት አቅም 17 በመቶ ይቀንሳል ።

የእነዚህ ኹሉ ድምር ውጤት አገሪቷ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና በማሳደር 55.5 ቢሊዮን ብር በየዓመቱ እናጣለን። ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ከዜጎቿ ማግኘት የሚገባትን ያህል እያገኘች አለመሆኑን ነው።
አንድ ሰው አድጎ፣ ተምሮ ለአገር ማበርከት የሚገባውን እንዳያበረክት የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያች መኖራቸውን ቴዎድሮስ አንስተዋል።

እነዚህም በተፈጥሮ ድህነት መኖሩ፣ የሰዎች ግንዛቤ ዕጥረትና የመግዛት አቅም ማነስ ናቸው። ድህነት እና የመግዛት ዓቅም ማነስ በአገሪቷ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኑሮ ውድነት የፈጠረው ስለሆነ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ቢያውቁም አይጠቀሙም። ገበያ ላይ ያሉትን ምርቶች ተጠቃሚው እንዲገዛ የሕብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል አስፈላጊ ነው።

ግንዛቤ ዕጥረት ማለት ደግሞ ሰው በቀን ሦስት ጊዜ መብላት እንጂ ምን አይነት ምግብ እንደተመገበ የሚገነዘብ አለመሆኑ ነው። ገንዘብ እያለም ቢሆን ግንዛቤው ባለመኖሩ የተመጣጠነ ምግብ የማይመገቡት ላይ ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር ጥናት መሠረትም የተማሩ ወይም ስለ ሥርዓተ-ምግብ እውቀት ያላቸው እናቶች ልጆቻቸው ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ያሳያል። በዚህ የስርዓት-ምግብ ኢንቨስትመንት አማካይነት አንድ ዶላር ቢያወጡ በምለሹ 16 ዶላር ማግኘት የሚቻልበት ነው።
የአማራ ክልል ረሃብ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። እንደ ትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ለአማራ ክልል ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ሲሉ አራጋው ጠቅሰዋል።

አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት ቡድን ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ። እነዚህን ዜጎች ለመታደግ የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋር አካላት በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ደበበ በአማራ ክልል ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ከሰሜን ወሎ 13 ወረዳዎችና ስምንት ከተማ አስተዳደሮች ከዋግኸምራ፣ ከሰቆጣ እና አካባቢው እንዲሁም በአፋር ክልል ከአሎ ወረዳ፣ ከሰሜንና ደቡብ ወሎ አጎራባች ከሆኑ ወረዳዎች የተፈናቀሉ 270ሺሕ 318 ዜጎች ያሉ ሲሆን፣ ዕርዳታ ለማድረስ መንግሥትና አጋር አካላት እየሠሩ እንደሚገኙ ደበበ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል የሚገኙ የተፈናቃዮች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ደርሷል የሚሉት አራጋው በበኩላቸው፣ መንግሥት ዕርዳታዎችን እያቀረበ ባለመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል ሲሉ ተናግረዋል። በዚህም በረሃብ ለተጎዱ ነዋሪዎች ዕርዳታ በሦስት ቀን ውስጥ የማይደርስ ከሆነ በርካታ ሰው እንደሚሞት ገልጸው ነበር። ነገር ግን ሦስት ቀኑም አልፎ አሁን ከባድ ኹኔታ ላይ ናቸው ሲሉ አራጋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮምቦልቻ እና ደሴ ላይ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ደበበ፣ ለ118ሺሕ ሰዎች በመንግሥት እና 60ሺሕዎችን ደግሞ በአጋር አካላት ተደራሽ ተደርገዋል ብለዋል።

በመንግሥትና በአጋር አካላት ድጋፍ የተደረገው 27ሺሕ ኩንታል እህል መሆኑን የጠቆሙት ደበበ፣ ድጋፎችን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የህወሓት ቡድን በመንግሥት ንብረት ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት ከፍተኛ ችግር ሆኖብናል ብለዋል።
የዕለት ዕርዳታ በማቅረብ ይታወቅ የነበረው የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ድርጅት በጦርነቱ ምክንያት ስራ በማቆሙ መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት እንዳይሳካ አድርጎታል ሲሉ ደበበ ተናግረዋል።

ይህ ተቋም ሥራውን ባለመሥራቱ የሰላም ሚኒስቴር እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በተነጋገሩት መሠረት የዓለም ምግብ ፕግራም (WFP)በራሱ አርማ (ሎጎ) እና ባንዲራ ተጠቅሞ እርዳታ እንዲያደርስ ተደርጓል።
“በኢትዮጵያ ዕርዳታ አጥተው ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎች የሉም” ሲሉ የገለጹት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን፣ ችግሮች ባሉባቸው የአገራችን አካባቢዎች መንግሥት ኮማንድ ፖስት በማቋቋም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደአንድ እያመጣ አስፈላጊውን ኹሉ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ነው ብለዋል።

ረሃብ ገብቷል ሊባል የሚችለው መንግሥት የዘነጋቸው ወይንም ሊደርስላቸው ያልቻሉ አካላት ሲኖሩ ብቻ ነው ሲሉ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ አሁን ላይ በተቻለ መጠን ኹሉንም ለችግር የተጋለጡ ዜጎች አስፈላጊ በሆነው መንገድ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እንዲያገኙ እየተደረገ ከመሆኑ አንጻር ወደ ረሃብ የተሸጋገረ ችግር የለም ማለታቸው ተሰምቷል።

ረሃብ ማለት መንግሥት መድረስ በሚገባው አካባቢ መድረስ ሳይችል ሲቀር የሚፈጠር ነው ያሉት አይዱሩስ፣ ነገር ግን መንግሥት በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱን ሕብረተሰብ በተለይም በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕርዳታዎች ማጓጓዝ ምቹ ሳይሆን ሊቀርና መዘግየቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብለዋል።

እንደ ቀይ መስቀል ያሉ ድርጅቶች በትግራይ ክልል በተደጋጋሚ እንደሚደርጉት እገዛ በአማራ ክልል እያደረጉ አይደለም ሲሉ አራጋው እያነጻጸሩ ተናግረዋል።
ረሃብ የሚባለው መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ለተጎዱ ወይንም ደግሞ ለተፈናቀሉ ሰዎች ማድረስ ሳይቻል ሲቀር ነው ያሉት አይዱሩስ፣ መንግሥት ቀን በቀን እየተከታተለ ዕለት በዕለት ድጋፎች እንዲካሄዱ እያደረገ፣ ቡድን አዋቅሮ እየሠራና እዚህ ቦታ ሩዝ አንሷል ሌላው ጋር ደግሞ ዱቄት በቂ አይደለም እየተባለ ሪፖርት በምንለዋወጥበት ኹኔታ ረሃብ አለ ብሎ ማንሳት የጁንታው አፈቀላጤዎች የሚፈጥሩት ዜና መሆኑን ኹሉም ሊረዳው እንደሚገባ አብራርተዋል።

በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ለተፈናቃዮች ባለመድረሱ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪወች ቤታቸውን በማጋራት እና እህሎቻቸውን በማካፈል፣ በተለያየ አደረጃጀት የሚገኙ የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ የግል ባለሃብቶች እና ዩኒቨርስቲዎች እርዳታ እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉ አራጋው ጠቅሰዋል።

እነዚህ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ በቂ ባይሆንም መንግሥት መድረስ ያልቻለውን እያዳረሱ ይገኛሉ ብለዋል።
ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ አካባቢያችን ለቅቀን አንሄድም ያሉት በየቤታቸው የሚገኙ ሰዎች ከኹሉም በላይ ችግር እየደረሰባቸው ነው ሲሉ አራጋው ነግረውናል። በአካባቢው የስልክ፣ የመብራት እና የውኃ አገልግሎት ባለመኖሩ ዕርዳታ እያገኙ አይደለም።ለምሳሌ ‹‹የኔ ቤተሰቦች በምን አይነት ሁኔታ እንዳሉ ማወቅ አልቻልኩም›› ሲሉ አራጋው ገልጸዋል።

የመንግሥት መኪና ወደ ክልሎቹ የሚገባ ከሆነ የህወሓት ቡድኖች ጥቃት ስለሚያደርሱበት በአጋር አካላት መኪናዎች በመጠቀም በመንግሥት መደረግ የሚገባው ተደርጎ የመላክ ሥራ መከናወኑን ነው ደበበ የገለጹት።
በዚህም በኩል እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ኮምቦልቻ በሚገኝ መጋዘን እህል እየተጫነ እየደረሰ ይገኛል። በመሆኑም በአምስት መኪናዎች አማካይነት 1940 ኩንታል እህል ለዳውንት ወረዳ እየተጓጓዘ ነው ሲሉ ደበበ ገልጸዋል።
መንግሥት ምንም እንደማይሠራ በማድረግ ረሃብ እየተባለ ማጋነን የመንግሥትን ድጋፍ ለመቀልበስ ነው ሲሉ ደበበ ገልጸዋል።

መንግሥት ቢገባ እህሉንም መኪናውንም ያቃጥሉበታል እየተባለ ችግር መኖሩ እየተገለጸ፣ መንግሥት ግድ እንደማይሰጠው እየተደረገ እየተነገረ ነው ሲሉ ደበበ ገልጸዋል።
በአንድ ቤተሰብ እስከ 15 ኪሎ እና አጠቃላይ የተቸገረውን የወሎ ሕዝብ ለማዳረስ ታቅዷል ብለዋል። በ1966 አና 1977 የተከሰተውን ደርቅ ተከትሎ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተራበበት ወቅት ነው እንጂ፣ አሁን ያለው ረሃብ መባል የለበትም ብለዋል።
‹‹የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ዋና ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በምክትል ኮምሽነሩ አማካይነት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተሠጠው መግለጫ ኮሚሽኑ ካለዉ መረጃ ጋር እጅግ የሚቃረን ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ እንደሚሉት ከሆነ ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ በሙሉ አቅማቸው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንና ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጠው መግለጫ ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸው ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here